ምኞት ሲሳካ …

0
41

በኔ ቀየ መንደር ገና ልጅ እያለሁ፣

ባንተ ሲገዘቱ ሲምሉ እሰማለሁ፡፡

የወገንን ነገር አንተም ታውቀዋለህ፣

አነገሡህ እንጅ መች ሠርቶ በላብህ፡፡

ዓባይ ሥመ መልካም ዓባይ ሥመ ጥሩ፣

አንተን ሲሳይ ይዘው ስንቶች ጦም አደሩ፡፡ በማለት ነበር የታላቁ ሕዳሴ ግድብን መጠናቀቅ አስመልክተው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው ሀምሳ አለቃ መንበሩ አንዷለም በፊት የነበራቸውን ቁጭት   በግጥም የገለፁልን፡፡

ዓባይ የፈለቀበትን ምድር ሳያረሰርስ፣ ሀገሩን ሳያለማ ስለትልቅነቱ ከወሬ የዘለለ ጥቅም ሳይሰጥ መቆየቱንም በቁጭት ነው አስተያየታቸውን ለበኵር የተናገሩት፡፡

ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለባለቤታቸው እና ለአራት ልጆቻቸው ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን እንዲያስቀምጡ ማድረጋቸውንም ሀምሳ አለቃ መንበሩ አስታውሰዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓባይ ወንዝ ላይ የነበረው የዘመናት ቁዘማ ተጠናቆ ለሀገሩ ልማትን ሊሰጥ ጊዜው ደርሶ የታላቁ ግድብ መጠናቀቅ ተበስሯል፤ ዓባይንም ፦

ቁመህ ስትጠየቅ ሌት ከቀን ስትጓዝ፣

አሁን ምን ተሰማህ ጉባ ላይ ስትያዝ፡፡ በማለት ነው ስሜታቸውን የገለጹት፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች ከደመወዛቸው፣ ነጋዴዎች ከወረታቸው፣ ጡረተኞች ከአበላቸው፣ የሕግ ታራሚዎች ከምግብ በጀታቸው፣ ተማሪዎች ከቁርሳቸው… በማዋጣት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጅማሮው የተበሰረለት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታው መጠናቀቅ ተበስሯል፡፡ ኢትዮጵያውያንን አንድ ያደረገው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከገንዘብ፣ ከጉልበት፣ ከዕውቀት አበርክቶ ባለፈ ድምፃውያን ሕዝቡ በዓባይ ላይ የነበረውን ቁጭት፣ ግንባታው ሲጀመር የሰነቀውን ተስፋ በዜማ ቀስቅሰውበታል፣ አነሳስተዋል፡፡ አንጋፋዋ የባሕል ሙዚቃ አቀንቃኝ ገነት ማስረሻ፤ “እኔ ሀሳቤን እያንጐራጉርሁ ብገልጽ ይሻላኛል” በማለት ስሜቷን እንደሚከተለው ገልጻለች፡-

ዓባይ ነጋ ጠባ ሀብቱን ያፈሰሰው፣

ጭስ አልባው ነዳጄ ብለው ምን ያንሰዋል፡፡

እንኳን ለኛ ቀርቶ ለሰውም ይተርፋል፣

ጭሽ አልባው ነዳጅ ብለው ምን ያንሰዋል፡፡

ዓባይ አንተ እያለህ ታላቁ ወንዛችን፣

መሳለቂያ አንሆንም በድህነታችን፡፡

ዓባይ ጉልበት ሆኖ ብርታት ይሰጠን እንጅ፣

በሚዲያ ቀርበን አንሆንም ተረጅ፡፡

ዓባይ ወርዶ ወርዶ ወርዶ ሲሰለቸው፣

ዛሬስ ለወገኑ  ስላገሩ ቆጨው፡፡

ዘመን ቢያስታርቀን ከዓባይ ብንስማማ፣

ይዘን ተጠጋነው አካፋ እና ዶማ፡፡

ዓባይ አንተ እያለህ ጭስ አልባው ነዳጅ

አልመለከትም እኔስ የሰው እጅ፡፡

የግድቡን ግንባታ ይፋ መሆን ተከትሎ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ አርሶ አደሮች፣ የሕግ ታራሚዎች… ለስኬታማነቱ ድጋፋቸውን በሰልፍ፣ በገንዘብ፣ በአይነት /በሬ፣ ቤት፣ ደሮ/ ካላቸው አነስተኛ ገቢ ለመለገስ ቃል ገቡ፡፡ የገቡትን ቃልም በተግባር ፈፀሙ፡፡ ይህን አስመልክቶ በአማራ ሚዲያ ኮርፓሬሽን በኵር ጋዜጣ ከሚያዝያ 03 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ተከታታይ ዘገባ ሠርታለች፡፡

በኵር በሚያዚያ 03 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትሟ በባሕር ዳር ከተማ የጣና ኃይቅ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ እና የግዮን አጠቃላይ መሰናዶ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተወያዩ በኋላ ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን በቦታው ተገኝተው ከጉልበት ጀምሮ ለታክስ እና ለሻይ ከሚሰጣቸው ገንዘብ  ከ10 ብር ጀምረው ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገቡ፡፡

ተማሪዎቹ የገቡትን ቃል ለመፈፀም ከታክሲ ይልቅ በእግራቸው በመሄድ እና ቁርሳቸውን በመተው አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የፋሲሎ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ተማሪዎች ከ20 ሺህ ብር በላይ ማበርከታቸውን በኵር መዘገቧ ይታወሳል፡፡

 

በደብረታቦር ከተማ፣ በላይ ጋይንት እና በአዲስ ዘመን ማረሚያ ቤቶች የነበሩ የሕግ ታራሚዎችም ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከቀለባቸው በመቀነስ 81 ሺህ 392 ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን በኵር ዘግባለች፡፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለልማት እንዲውል በወቅቱ ደስታቸውን ከገለፁት፣ የገንዝብ እና የአይነት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ከገቡት ወገኖች መካከል በይልማና ዴንሳ ወረዳ የይዞራ ቀበሌ ነዋሪው ቄስ ላቀው ዳግም  ይገኙበታል፡፡ “የግድቡ ግንባታ አጀማመር ይፋ መሆንን አስመልክቶ ሲነገር በጣም ደስታ ተሰማኝ፡፡ ምክንያቱም ብዙ አምርተን ብዙ እንድናፍስ የሚያስችል በመሆኑ ነው፡፡ ለግንባታው መሳካትም አራት ኩንታል እህል እንዲሁም በቤተሰብ ስም አንድ ከብት ሽጨ ቦንድ ገዛሁ” በማለት ለበኵር ገልፀው ነበር፡፡

ከ13 ዓመት በፊት የግንባታው አጀማመር ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሕዝቡ መሀንዲስ ሆኖ በራሱ ገንዘብ አስገንብቶ እነሆ ጳጉሜን 04 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ሊመረቅ ተበስሯል፡፡

ካላቸው አዋጥተው ግንባታውን ያስፈፀሙ ኢትዮጵያዊያን ታዲያ ዛሬስ ምን ተሰምቷቸው ይሆን?    በደቡብ ወሎ ዞን ከለላ ከተማ 01 ቀበሌ የተወለደችው የትናንቷ ሕጻን የዛሬዋ ወጣት ሰሚራ ኢብራሂም አንደኛ ክፍል የገባችው በ2007 ዓ.ም ነው፡፡ ያኔ ሰሚራ ኢብራሂም የሰባት ዓመት ሕጻን ነበረች፡፡ ወቅቱ ደግሞ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስፈጸሚያ ገንዘብ የሚሠበሠብበት  ነበር።  ሁሉም ኅብረተሰብ በተቻለው አቅም ድጋፉን ለማድረግ ይረባረባል። ተማሪዎች ሳይቀር ገንዘብ ከወላጆቻቸው ተቀብለው ቦንድ ይገዛሉ፤ ይለግሳሉ።

ሕጻን ሰሚራ እና አቻዎቿም በትምህርት ቤታቸው፣ በሠፈሩ እና በቤተሰቡ ስለ ሕዳሴው ግድብ በጋለ ስሜት ውይይት ሲደረግ ይከታተላሉ። መዝሙር ይዘመራል፣ ስንኝ ይቋጠራል፣ ይፎከራል፣ ቃል ይገባል፤ ገንዘብ ይዋጣል፤ ድጋፍ ይደረጋል። በያኔዋ ሕጻን ሰሚራ አዕምሮ ውስጥም አንዳች መነሳሳት ተፈጠረ። ነገር ግን ሕጻን ስለሆነች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምትሰጠው ገንዘብ የላትም። ለሀገሯ ባላት መልካም ምኞት ቦንድ የምትገዛበት ገንዘብ ማግኘት የምትችልበትን መንገድ አወጣች፤ አወረደች።

አንድ ሀሳብ መጣላት፤ ቤተሰቦቿ ብር ሲሰጧት  አጠራቅማ ከምታረባቸው ሦስት ዶሮዎች መካከል አንዱን ለመስጠት ወሰነች፡፡ ይህንንም ለወላጆቿ ስታማክራቸው በደስታ ተቀበሏት፡፡

ሀሳቧ እውን ያደረገ በከለላ ከተማ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አስተዋጽኦ የሚደረግበት ውይይት እና የገንዘብ መሠብሠቢያ መድረክ ተዘጋጀ። ዶሮውንም ለግድቡ የድጋፍ ገንዘብ ወደ ሚሠበሠብበት ወስዳ አበረከተች። ሕዝቡም በደስታ ተቀብሎ ዶሮውን ለጨረታ ቀርቦ 17 ሺህ ብር ተሽጦ ቦንድ እንደተገዛላት ሰሚራ ታስታውሳለች። ሌሎች ተማሪዎችም ታሪኳን ሰምተው በመነሳሳት የእሷን ፈለግ ተከትለው ድጋፋቸውን አበረከቱ፡፡

አሁን በሳዑዲ አረቢያ የምትኖረው ሰሚራ ለአሚኮ በሰጠችው አስተያየት አሻራዋ ያለበት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አልቆ ሊመረቅ እንደሆነ ስትሰማ መደሰቷን ተናግራለች።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ “የሁላችንም ርብርብ እና አሻራ ነው” ያለችው ወጣት ሰሚራ ሀገሯ ከዚህም በላይ እንድታድግ ፍላጎቷ እና ምኞቷ መሆኑን ገልጻለች።

ለወደፊትም ለሀገሯ ሌላ አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት እንዳላት ቃል ገብታለች፡፡

የ80 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋው በኩረ ምዕመናን ኪዳኔ ኀይሌ የደብረ ብርሐን ከተማ ነዋሪ ናቸው። በራሳቸው ስም የ170 ሺህ ብር ቦንድ፣ ለ20 ልጆቻቸው እና ለ20 የልጅ ልጆቻቸው ደግሞ ለእያንዳንዳቸው የሁለት ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸዋል።

የዘመናት ቁጭት የሆነው ዓባይ ሊገደብ እንደሆነ ሲሰሙ የተሰማቸው ደስታ እንደ ትናንት እንደሚታወሳቸው ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። የሕዳሴ ግድቡ የአንድነት ኀይል የተገለጠበት ታሪክ በመሆኑ ለልጆቻቸው እና ለልጅ ልጆቻቸው ቦንድ መግዛታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ለዓመታት በንግድ ሥራ የተሠማሩት  አባት “ለልጆቼ የገዛሁት ፎቅ ሳይሆን የዚህ ታላቅ ታሪክ አካል እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ቦንድ ነው፡፡  እኔም ዕድሜ ሰጥቶኝ ግድቡ ሲጠናቀቅ በማየቴ ደስተኛ ነኝ!” ብለዋል።

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የነጳጉሜን 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here