የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል ባዘጋጀው አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ከዐሥር የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አካላት ተሳትፈዋል:: መምህራን ደግሞ የትምህርት ዘርፉን ወክለው ተገኝተዋል:: በምክክሩ እየተሳተፉ ካገኘናቸው መምህራን እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት መካከል መምህር መላኩ በላይ አንዱ ናቸው::
መምህሩ እንደሚሉት ለዓመታት የዘለቁት ጦርነቶች እና ግጭቶች የተማረ ዜጋን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ዋነኛ ፈተናዎች እየሆኑ መጥተዋል:: በክልሉ የተከሰተው ግጭት የትምህርት አሰጣጡ ሳንካ እንዲገጥመው፣ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዳይመጡ፣ መምህራን በነጻነት የመማር ማስተማር ሂደቱን እንዳያከናውኑ በማድረግ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል::
በትምህርት ዘርፉ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና በማርገብ ትምህርት እውነትም የሀገር ዕድገት ምሰሶ መሆኑን ለማረጋገጥ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እያሳየ ያለውን የሰላም መንገድ መጠቀም እንደሚገባ አቶ መላኩ ጠቁመዋል:: ሀገራዊ ምክክሩ የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ለማስተካከል እና ትምህርቱም ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል:: ለዚህም በምክክር ኮሚሽኑ የሚነሱ እያንዳንዱን ሐሳቦች እና ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ እንደሚገባ ጠቁመዋል:: ይህ ሲሆን ደግሞ ብዙ ምሁራንን ማፍራት እንደሚቻልም ያምናሉ::
“ግጭቱ ቀኝ እጅ ከግራ ነው” ያሉት መምህሩ፣ መስዋዕትነቱ ለሰላም መስፈን እንዲሆን ጠይቀዋል:: በምክክሩ ላይ እየተሳተፉ ያሉ የትምህርት ባለድርሻ አካላትም ሐሳባቸውን በነጻነት መግለጻቸውን ጠቁመዋል::
ሰላም የሚያስፈልገው የትምህርት ዘርፉን ውጤታማ አድርጎ ለማስቀጠል ብቻ ሳይሆን የዘላቂ ሰላም መሠረት በመሆኑም ጭምር ነው:: በመሆኑም እየጠፋ ያለውን የሕጻናትን የነገ ተስፋ ብሩህ ለማድረግ ታጥቀው በጫካ ውስጥ የሚገኙ ወገኖች በሀገራዊ ምክክሩ ሐሳባቸውን በማዋጣት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል::
የአማራ ክልል የተማሪ ወላጆች ማኅበር ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ተማሪ ወላጆች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አዱኛው እሸቴ በበኩላቸው ለአንድ ሀገር የወደፊት መዳረሻ መንገድ በሆነው የትምህርት ዘርፍ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል::
እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ሐብት ሰዎች ሲፈጠሩ ብቻ የሚፈጥሩት ነገር ነው:: ሰዎች ሲፈጠሩ ሊፈጥሩት የሚችሉት በትምህርት (ሲማሩ) ብቻ ነው:: ለዚህም ትምህርት በግጭት ወቅት ሰለባ እንዳይሆን ቀይ መስመር ሊበጅለት ይገባ ነበር ብለው ያምናሉ:: ይህ ባለመሆኑ ግጭቶች የትምህርት ዘርፉ ክፉኛ እንዲጎዳ አድርጎታል ባይ ናቸው::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠሙ የመጡ የጸጥታ ችግሮች ክልሉም ሆነ ሀገሪቱ የተማረ ዜጋ እንዲያጡ እያደረገ እንደሆነ አቶ አዱኛው ያምናሉ:: የትውልድ ኪሳራ እንዲያጋጥም አድርጓል:: በትምህርቱ ላይ የደረሰው ተጽእኖ ተተኪ ለማግኘት አስቸጋሪ ሊያደርገው እንደሚችልም ስጋታቸው መሆኑን ገልጸዋል::
እንደ አቶ አዱኛው ማብራሪያ ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ተማሪዎች ቁጥር እንደ ሀገር 7 ሚሊዮን 937 ሺህ 902 ናቸው:: ይህም በሂደት ከፍተኛ ኪሳራን ይዞ እንደሚመጣ ነው ያስታወቁት::
አቶ አዱኛው “የአማራ ዶክተር፣ ኢንጅነር፣ ዳኛ … የኢትዮጵያ ብሎም የዓለም ምሁር ነው” ብለው ያምናሉ:: በመሆኑም በትምህርት ዘርፉ ላይ የተደቀነውን መዘዝ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ለመፍታት ግጭት እንዲቀጥል ከሚያደርግ አስተሳሰብ መውጣት ዋናው መፍትሔ መሆኑን አመላክተዋል:: በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ወገኖችን ጨምሮ መንግሥት ትውልድ እየተበላ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል::
“የልጆቻችን የነገ እጣ ፋንታ ከመጨለም ወጥቶ የተሻለ እንዲሆን ትልቁ መድኃኒት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ይዞት የመጣው ዕድል ነው” በማለትም የምክክር ኮሚሽኑ ለትምህርቱ ዘርፍ መፍትሔ እንደሚያስገኝ ተስፋ ሰንቀዋል:: ምክክሩ የጥል እና ያለመግባባት ምክንያቶችን በሰከነ መንገድ በመፍታት አሁንም ድረስ የቀጠሉ የሰላም እና ደኅንነት ችግሮች ለነገ እርሾ ሆነው አዲስ ግጭት እንዳይቀሰቅሱ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመዋል::
ማኅበሩ ከትምህርት ውጪ የሆኑ ተማሪዎች እንዲመለሱ፣ ትምህርት በተጀመረባቸው አካባቢዎችም ሳይቋረጥ ተጠናክሮ እንዲቀጠል፣ የትምህርት ተቋማት ደኅንነት እንዲረጋገጥ፣ ሕዝቡም ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ ጀምሮ የሰላም ዘብ እንዲሆን በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል::
ያደጉት ሀገራት ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ሳይሆን ቀድመው መፍትሄው ላይ እንደሚሠሩ አቶ አዱኛው አስታውቀዋል:: “በእኛ ሀገር ደግሞ የዚች ሀገር መፍረሻ ትምህርት መሆኑን አውቀው ዘርፉ እንዳይጎዳ መጠንቀቅ ይገባቸዋል” በማለት አቶ አዱኛው አስገንዝበዋል::
“ትምህርት የፖለቲካ መሳሪያ መሆን የለበትም:: ትምህርትን የመታገያ መንገድ አድርጎ መጠቀም ነገ መሪ ሆኖ ለሚመጣው አካል የተማረ የሰው ኀይል ክፍተትን የሚፈጥር በመሆኑ ለትምህርት ከለላ መሆንን ማስቀደም ይገባዋል:: ወላጆችም የትምህርትን ጉዳይ አጥብቀው መያዝ አለባቸው” በማለት ጠይቀዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም