ምዕራባዊያን እና ሩሲያ

0
157

የሩሲያዉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ዲሞክራሲያዊ አይደሉም፤  ሕጋዊነትም የጎደላቸው ናቸው” በሚል በምዕራባዊያን ዘንድ ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረባቸው ቢገኝም ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት  ስልጣናቸውን አጠናክረዋል። ፑቲን ወደ ሩብ ክፍለ ዘመን የሚጠጋውን የስልጣን ጊዜያቸውን ለስድስት ዓመታት አራዝመዋል።

ከሰሞኑ የሩሲያዉ መሪ ቭላድሚር ፑቲን ለአምስተኛ ጊዜ ፕሬዚዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል:: እ.አ.አ. ከ1999 ጀምሮ በፕሬዚዳንትነት ወይም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ላይ የሚገኙት ፑቲን አዲሱን ተልእኳቸውን የጀመሩት ከሁለት ዓመት በላይ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ ዩክሬን ካዘመቱ በኋላ ነው::

በታላቁ ክሬምሊን ቤተመንግሥት ለአምስተኛ ጊዜ በተካሄደው የፕሬዚዳንትነት በዓለ ሲመታቸው ላይ ፑቲን ሩሲያ አሁን ያለውን አስቸጋሪ ጊዜ በጠንካራ ሁኔታ በማለፍ በድል አድራጊነት እንደምትወጣ ተናግረዋል ። ፑቲን በመጋቢት ወር በድጋሚ የተመረጡት የምዕራባውያን ሀገራት የይስሙላ ነው ብለው ባጣጣሉት ምርጫ ነው::

“የተባበርን እና ታላቅ ሀገር ነን፤ እናም ሁሉንም መሰናክሎች እናሸንፋለን፤ ያቀድነውን ሁሉ እውን እናደርጋለን፤ በአንድነት እናሸንፋለን”፤ ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል::

የ71 ዓመቱ ፑቲን የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ምህዳርን ተቆጣጥረዋል። በዓለም አቀፍ መድረክ ዩክሬንን እንደ መሳሪያ ተጠቅመው ሩሲያን ለመበታተን ከከሰሷቸው ምዕራባውያን ሀገራት ጋርም ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን እንዳስታወቀችው ቭላድሚር ፑቲንን ለተጨማሪ ስድስት ዓመታት  እንደ ሩሲያ ፕሬዚዳንትነት እውቅና ለመስጠት ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሰረት እንደሌላት  አስታውቃለች።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ እንደሚለው “የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በቭላድሚር ፑቲን ላይ የሰጠውን የእስር ማዘዣ መሰረት በማድረግ ዩክሬን በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ እና ሕጋዊ የሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት መሆኑን እውቅና ለመስጠት ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሰረት አይታይባትም” ብሏል።

ዩክሬን እ.አ.አ. በ 2022 ሩሲያ በግዛቷ የድምጽ መስጫ ሂደቶችን በማደራጀት – ዶኔትስክ ፣ ሉሃንስክ ፣ ዛፖሪዝሂያን እና ኬርሰንን እንዲሁም በ2014 ሞስኮን የተቀላቀለችውን የክራይሚያ ባሕረ ገብ መሬትን ጨምሮ ሩሲያ በመጋቢት ወር በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት በርካታ ዓለም አቀፍ ሰነዶችን ጥሳለች ስትል ከሳታለች::

በእነዚህ ግዛቶች የተካሄደው የምርጫ ሂደት “በአጠቃላይ ተቀባይነት ያላቸውን የዓለም አቀፍ ሕግ፣ ደንቦች እና መርሆዎችን የጣሰ ነው ማለቷን አናዶሉ ዘግቧል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በናዚ ጀርመን እና በተባባሪዎቿ ላይ ድል የተቀዳጀችበትን 79 ኛ ዓመት አክብራለች። ክብረ በዓሉ የሞስኮን ወታደራዊ ኃይል ለማሳየት ብዙ ርቀት ሄዷል:: የተለያዩ አህጉር አቀፍ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ከባድ መሳሪያዎች እና የታንክ ክፍሎች ከክሬምሊን አልፈው ሲወጡ ታይተዋል።

ምንም እንኳን የዘንድሮው ሰልፍ ካለፉት የድል ቀን መታሰቢያ በዓላት ጋር በንፅፅር ሲታይ ወታደራዊ ሃርድዌር (ዋና ዋና የጦር መሳሪያ) የጎደለው ቢሆንም ፑቲን ከቤላሩሱ አጋራቸው እና የምንጊዜም ወዳጃቸው ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ጋር በመሆን በቀዩ አደባባይ አንድ ላይ በኩራት ቆመው ታይተዋል:: እንደሚታወቀው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሶቪየት ኅብረት 27 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን አጥታለች፤ ይህም እያንዳንዱ ቤተሰብ ጠባሳ አለው ማለት ይቻላል።

በተያያዘም ፑቲን ሰሞኑን የድል ቀን አከባበር ላይ ባደረጉት ንግግር የኒዩክሌር ኃይላቸውን ለዓለም አቀፍ ጦርነት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል። በየዓመቱ ግንቦት 9 የሚከበረው የሩሲያዊያን የድል ቀን በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ሩሲያ ናዚ ጀርመንን ያሸነፈችበት በዓል ነው::

ፑቲን ባደረጉት ንግግር “የድል ቀን ሁሉንም ትውልድ አንድ ያደርጋል” ብለዋል። “ለዘመናት በቆዩት ባህሎቻችን ላይ በመተማመን ወደፊት ሩሲያ ነፃ እና ደኅንነቷ  የተጠበቀ እንደሚሆን እርግጠኞች ነን” ብለዋል::

ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰው የራሺያ-ምዕራብ ውጥረት ፑቲን ስለ ሩሲያ የኒውክሌር ኃይል ሌላ ትልቅ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። “ሩሲያ ዓለም አቀፍ ግጭትን ለመከላከል ሁሉንም ነገር ታደርጋለች፤ ነገር ግን ማንም ሰው እንዲያስፈራራን አንፈቅድም” ሲሉ ተናግረዋል:: “የስትራቴጂካዊ ኃይላችን ለውጊያ ዝግጁ ነው”ም ብለዋል።

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ለከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣናት፣  የጦር ኃይል አባላት እና በሀገር ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሩሲያውያን  የሚመለከቱትን ንግግር ባደረጉበት ወቅት  የክሬምሊን ፍርድ ቤት ዓለም አቀፍ ግጭትን ለማስወገድ ሁሉንም ነገር እንደሚያደርግ ገልጸው ነገር ግን ወታደራቸው በሀገራቸው ደኅንነት ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ስጋት ለመቋቋም ዝግጁ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ  ዓለም በአደገኛ የኒዩክሌር ጦርነት አፋፍ ላይ እንደምትገኝ አሳውቀዋል::

አናዶሉ እንደዘገበው ከሩሲያ፣ ኢራን፣ ሰሜን ኮሪያ እና ቻይና ጋር በተያያዘ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት ተከትሎ ሱናክ ከጠላት መንግሥታት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማደናቀፍ እና ለመከላከል ጠንካራ የመከላከያ እርምጃዎች አስፈላጊ መሆናቸውን አፅንዖት ሰጥተዋል።

ሱናክ እ.አ.አ. በ1962 ከኩባ የሚሳኤል ቀውስ ወዲህ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዓለምን ወደ ኒዩክሌር ግጭት እንዲመጣ በማድረግ “ግዴለሽ ናቸው” በሚል ጣታቸውን ወደ ሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ሳምንት የሁለት ቀን የመንግሥት ጉብኝት በቻይና ማድረጋቸውን ሲጅቲኤን ዘግቧል::

ፑቲን በጉብኝታቸው ከቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በተለያዩ መስኮች ትብብር እንዲሁም ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል::

ፑቲን በፕሬዚዳንትነት ቃለ መሃላ ከፈጸሙ እና አምስተኛውን የስልጣን ጊዜያቸውን ከጀመሩ በኋላ ይህ የመጀመሪያው የውጭ ሀገር ጉዞ ይሆናል ተብሏል።

አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው ቻይና የክሬምሊንን ካዝና ሞልቶ የሚይዝ የኃይል አቅርቦቶች ዋና የኤክስፖርት ገበያ ነች። ቻይና በሩሲያ እና በዩክሬን ግጭት ውስጥ እራሷን እንደ ገለልተኛ አካል ለማቅረብ ብትፈልግም የምዕራቡ ዓለምን በመቃወም ከሩሲያ ጋር ገደብ የለሽ ግንኙነት አውጃለች:: ሁለቱ ወገኖች ቀደም ሲል ተከታታይ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን ያደረጉ ሲሆን ቻይና ከዩክሬን ጋር  ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት በሩስያ ላይ የሚጣለውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ በተከታታይ ስትቃወም ቆይታለች።

ቻይና ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ  ከምዕራቡ ዓለም የሚሰነዘርባትን ትችት በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች:: ነገር ግን ኢኮኖሚያዊ አጋርነታቸው እና ወታደራዊ ትብብራቸው በምዕራቡ ዓለም በዓይነ ቁራኛ እየታየ ነው።

በዚህ ወር ይፋ የተደረገው የዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ጊዜ የቅጣት እርምጃዎች በቻይና የተመሰረቱ 20 ኩባንያዎችን ጨምሮ የሩሲያን ወታደራዊ እና የኢንዱስትሪ አቅም ሽባ ለማድረግ በተደረገው ሙከራ ከ280 በላይ አካላትን ኢላማ አድርጓል።

አሜሪካ ቻይናን እንደ ትልቅ ተፎካካሪዋ እና ሩሲያን እንደ  ትልቅ የሀገር ስጋት ትቆጥራቸዋለች::

የቻይና-ሩሲያ የንግድ ልውውጥ በ 240 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር በ 2023 ክብረ ወሰን  ያስመዘገበ ሲሆን ይህም ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው የ26 ነጥብ ሦስት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፤ ሲል የቻይና የጉምሩክ መረጃ ያሳያል።

ከምዕራቡ ዓለም ማዕቀብ ቢጣልባትም ሩሲያ የቻይና ከፍተኛ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት አቅራቢ ሀገር  ሆናለች፤ ወደ ቻይና የምታደርገው የነዳጅ አቅርቦትም እ.አ.አ. በ2023 ብቻ ከ24 በመቶ በላይ ሆኗል።

32 ሀገራት የኔቶ አባል ሀገራት ሩሲያን አጥብቀው የሚጠሉ ሲሆን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እርዳታ በማድረግ በተዘዋዋሪ የዕጅ አዙር ጦርነት ገጥመዋት ይገኛሉ:: በሌላ በኩል ጥቂት ሀገራት ደግሞ የሞስኮ ወዳጆች እንደሆኑ ይነገራል:: ኪቭፖስት ድረገፅ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ቤላሩስ የሞስኮ ታማኝ አጋር ናት:: ኢራን ደግሞ የሩሲያን የጦር መሣሪያ ክፍተት እንደምትሞላ ይነገራል:: ሰሜን ኮሪያ – አዲስ አጋሯ ተደርጋ ትቆጠራለች:: ሶሪያ የሞስኮ የመካከለኛው ምሥራቅ ምሽግ ትባላለች:: ቻይና የክሬምሊን ትልቁ ዓለም አቀፍ አጋር ስትሆን ሕንድ ከሩሲያ ጋር ታሪካዊ ትስስር  አላት::

በተያያዘም በኪየቭ ብሊንከን ዩክሬን ከሩሲያ አዲስ ጥቃት እየደረሰባት  ባለበት ወቅት የአሜሪካ ጦር መሳሪያ ለውጥ ያመጣል ብለዋል። የአሜሪካ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሰሞኑ   አሜሪካ ለዩክሬን ያደረገችው ወታደራዊ እርዳታ በጦር ሜዳ ላይ “እውነተኛ ለውጥ” እንደሚያመጣ መናገራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል::

ከሰሞኑ በሰሜናዊ ምሥራቅ ድንበር ላይ እየጨመረ በመጣው ኃይለኛ ጥቃቶች የሞስኮ ወታደሮች ከ100 እስከ 125 ካሬ ኪሎ ሜትር (ከ40 እስከ 50 ካሬ ማይል አካባቢ) የሚሸፍነውን ሰባት መንደሮችን እንደያዙ ተነግሯል:: አብዛኞቹ መንደሮች ቀድሞውንም የተራቆቱ ቢሆንም በአካባቢው የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ግን ጦርነቱን ሸሽተው ወጥተዋል።

ብሊንከን በዩክሬን ዋና ከተማ ከዜለንስኪ ጋር በተገናኙበት ወቅት “ይህ ፈታኝ ጊዜ እንደሆነ እናውቃለን፤ ነገር ግን የአሜሪካ ወታደራዊ እርዳታ በጦር ሜዳው ላይ እየተካሄደ ባለው የሩሲያ ወረራ ላይ እውነተኛ ለውጥ ሊያመጣ ነው” ሲሉ ለዜለንስኪ ተስፋ ሰጥተዋል።

ብሊንከን መሰናክሎች ቢኖሩም ዩክሬን አሁንም ጉልህ ድሎችን ልታገኝ እንደምትችል ተናግረዋል። እነዚህም በጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ ወራት የሩሲያ ኃይሎች ከወሰዱት ግዛት 50% የሚሆነውን ማስመለስ፣ ኢኮኖሚያዊ አቋሙን ማሳደግ እና የትራንስፖርት እና የንግድ ግንኙነቱን ማሻሻል እና ቢያንስ በጥቁር ባህር ወታደራዊ ስኬቶችን ማስመዝገብን እንደሚያጠቃልል አሳውቀዋል።

ባለሥልጣኑ ዩክሬን ጠንካራ ውጊያ እንደተጋፈጠች እና በከፍተኛ ጫና ውስጥ እንዳለች አምነዋል:: ነገር ግን አዲሱ የአሜሪካ እና ሌሎች የምዕራባውያን ዕርዳታ መምጣት ሲጀምር ዩክሬናውያን የበለጠ በራስ መተማመን እንደሚኖራቸው ነው የተናገሩት ።

ቢቢሲ በበኩሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የሩሲያዉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ያወደሙትን ለመጠገን መክፈል አለባቸው ማለታቸውን  ዘግቧል:: አሜሪካ በግዛቷ ያሉ የሩሲያ ኃብት ንብረቶች ላይ ማዕቀብ የመጣል አቅም እንዳላትም ገልጸዋል። እነዚህን ኃብት ንብረቶች ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት እንደሚውሉ ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

ቢቢሲ በዘገባዉ እንዳስታወሰው ከሁለት ዓመት በፊት ሩሲያ ከዩክሬን በምታደርገው ጦርነት ምክንያት በአውሮፓ ያሉ ወደ 181 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የሩሲያ ኃብቶች ላይ ማዕቀብ ተጥሏል።

የአሜሪካ ምክር ቤት ከሦስት ሳምንታት በፊት 61 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን ለመላክ ስምምነት ላይ መድረሱ ይታወቃል:: የሩሲያ ሰራዊት በጦርነቱ ሰሞኑን እያስመዘገበው ከሚገኘው ድል ጋር ተያይዞ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚያስፈልጋት ምዕራባዊያን ተስማምተዋል::

ዜለንስኪ በበኩላቸው አሁን ላይ ሩሲያ እያስመዘገበችው ያለው ድል ምዕራባዊያን ለዩክሬን እንልካለን ያሉት የጦር መሳሪያ በመዘግየቱ ምክንያት ነው ብለዋል::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here