ያቺ መጥፎ ቀን ከመድረሷ ከሁለት ወር በፊት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አንስቷል፤ ከአንድ ወር በፊት የአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ዋንጫን ከፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን ጋር አሳክቷል። ከአምስት ቀናት በፊት ደግሞ ከአብሮ አደጉ ሩት ካርዶስ ጋር በትዳር ተጣምሮ ነበር። ታዲያ ከዚህ ሁሉ ፌሽታ እና ደስታ በኋላ “እኔ ዕድለኛ ሰው ነኝ” በማለት ለተለያዩ የአውሮፓ መገናኛ ብዙኃን መናገሩ አይዘነጋም- ዲያጎ ጆዜ ቴዤራ ዳ ሲልቫ።
ዲያጎ ጆታ ከወንድሙ ጋር ህይወቱን ያሳጣችው ቀን እስከምትመጣ ድረስ በእርግጥም ዕድለኛ ነበር። ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ግን የሚወደውን እግር ኳስ፣ ባለቤቱን እና ሦስቱን ልጆቹን ትቶ ላይመለስ እስከ ወዲያኛው አሸልቧል። የትዳር ታሪኩም ገና ሳይጀመር ተቋጭቷል። ሁለት ልጆች ብቻ የነበሯቸው አባቱ ጆአኪም ሲልቫ እና እናቱ ኢዛቤል ሲልቫ ሁለቱንም በአንድ መጥፎ አጋጣሚ አጥተዋቸዋል።
ዲያጎ ጆታ እ.አ.አ ታህሳስ አራት ቀን 1996 በፖርቹጋል ፖርቶ ከተማ ነው የተወለደው። የጆታ ትክክለኛ ስም “ሲልቫ” ነበር፤ ይሁን እንጂ በወጣት አካዳሚ ተጫዋች እያለ “ሲልቫ” ተብለው ከሚጠሩት ከብዙ ሌሎች ተጫዋቾች ራሱን ለመለየት “ጆታ” ወደሚለው ስም እንደቀየረው መረጃዎች አመልክተዋል።
በተፈጥሮው የቀኝ እግር ተጫዋች ቢሆንም ሁለቱም እግሮቹ ጠንካራ ስለመሆናቸው ይነገራል። ከኳስ ውጪ ያለው እንቅስቃሴ እና ቦታ አያያዙ፣ የኳስ ቁጥጥር እና የመልሶ ማጥቃት ክህሎቱ ልዩ ተጫዋች ያደርገው ነበር። ጆታ የተዋጣለት ጨራሽ አጥቂ የነበረ ሲሆን ከእግሮቹ ጭንቅላቱን እኩል የሚጠቅም ምርጥ አጥቂ ነበር። እ.አ.አ 2019 ጀምሮ በፖርቹጋል ዋናው ቡድን መሰለፍ እንደጀመረ የግል የታሪክ ማህደሩ ያሳያል። ታናሽ ወንድሙ አንድሪ ሲልቫ ደግሞ የግራ ክንፍ እና የጨዋታ አቀጣጣይ እንደነበር የግል የታሪክ ማህደሩ ያሳያል። ተጫዋቹ ሙሉ የእግር ኳስ ህይወቱን በፖርቹጋል ሊግ ነው ያሳለፈው።
ጆታ ከወንድሙ አንድሪ ሲልቫ ጋር በመሆን ላምቦርጊኒ መኪና እያሽከረከሩ እያለ ጎማው በመፈንዳቱ ወንድማማቾች በሚያሳዝን ሁኔታ ህይወታቸው አልፏል። በሰሜን ምዕራብ ስፔን በሚገኘው የዛሞራ ከተማ የከፍተኛ መንገድ አደጋው መድረሱን የስፔን መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ የዘገበው ዘ አትሌቲክ ነው። ህይወት አጭር ናት ሲል ሀዘኑን ገልጿል። ጆታ በቅርቡ የሳንባ ቀዶ ጥገና ማድረጉን ይታወቃል። ታዲያ በዚህ ምክንያት ዶክተሮች በአውሮፕላን እንዳይጓዝ በመከልከላቸው እንቅስቃሴውን በመኪና ለማድረግ ተገዶ እንደነበረ አይዘነጋም። እንደ በርካታ መገናኛ ብዙኃን መረጃዎች ከሆነ መኪናውን ሲያሽከረክር የነበረው ዲያጎ ጆታ እንደነበር ተገልጿል። በፍጥነት ማሽከርከሩ ደግሞ ህይወቱን ነጥቆታል።
ጆታ ገና የስድስት ዓመት ታዳጊ እያለ ነው ወኃ ዋና እና ሌሎች የተለያዩ ስፖርቶችን ማዘወተር የጀመረው። የሀገሩ ልጅ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እግር ኳስ ተጫዋች እንዲሆን ተጽእኖ እንዳሳደረበት ዘ ኢንድፔንደንት አስነብቧል። ጆታ ከፓኮስ ዴ ፌሬራ ክለብ ተነስቶ በአትሌቲኮ ማድሪድ እና ወልቭስ ጎልብቶ በሊቨርፑል ቤት ራሱን ያገኘ ተጫዋች ነበር። በ2020 እ.አ.አ ነበር ሊቨርፑል 45 ሚሊዬን ፓውንድ ገንዘብ በማውጣት ከወልቭስ ያስፈረመው፤ ዝውውሩም ከውድ ዝውውሮች መካከል ሆኖ እስካሁን ይጠቀሳል።
በአንፊልድ ሮድ በቆየባቸው አምስት ዓመታትም 182 ጨዋታዎችን አድርጎ 65 ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። 26 ግብ የሆኑ ኳሶችን ደግሞ ማቀበል ችሏል። ቀዮች በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ እንዲያነሱም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ከመርሲሳይዱ ክለብ ጋር በአጠቃላይ የኤፍ ኤ ዋንጫ እና ሁለት የካራባዋ ዋንጫም አሳክቷል። ጆታ የፊት መስመር እና የክንፍ ስፍራ መጫወት የሚችል ሁለገብ አጥቂ ነው። ከ2019 እ.አ.አ ጀምሮ በብሄራዊ ቡድኑ ተካቶ ያገለገለ ሲሆን በተሰለፈባቸው 49 ጨዋታዎች 14 ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። በ2018/19 እና 2024/ 25 እ.አ.አ የአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ውድድር ዋንጫ ከሀገሩ ጋር ማንሳቱን ዘ አትሌቲክ አስነብቧል።
በ2017/18 እ.አ.አ ወልቭስ ከሻምፒዮንሽፑ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ሲመለስ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን የዘ አትሌቲክስ መረጃ አመልክቷል። በ2017/18 እ.አ.አ የውድድር ዘመን ከአትሌቲኮ ማድሪድ ወደ ወልቨር አምፕተን ባቀናበት የመጀመሪያው ዓመት ለእንግሊዙ ክለብ 17 ግቦችን በማስቆጠር ድንቅ እንቅስቃሴ አድርጓል። በሞሊኔክስ ስቴዲየም በቆየባቸው ሦስት ዓመታትም በ131 ጨዋታዎች ተሰልፎ 44 ግቦችን እና 19 ግብ የሆኑ ኳሶችን ለቡድን ጓደኞቹ አመቻችቶ አቀብሏል።
በ2020 እ.አ.አ አንፊልድ ከደረሰ በኋላ ቀዮች በሜዳቸው ባከናወኗቸው ተከታታይ አራት ጨዋታዎች ግቦችን ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋች ነው። ዲያጎ ጆታ የሊቨርፑልን ዐስር ሺህኛዋን ግብ ከመረብ በማገናኘት የታሪኩ አካል መሆኑን ዘ አትሌቲክ ዘግቦታል። ሊቨርፑል ዲያጎ ጆታ ግብ ባስቆጠረባቸው ጨዋታዎች አንድም ጊዜ ተሸንፎ አይውቅም። በ52 ጨዋታዎች 43ቱን ሲያሸንፍ በዘጠኙ ነጥብ ተጋርቷል። ባሳለፍነው ጥር ወር በ2025 እ.አ.አ ጆታ ከኖቲንግሀም ፎረስት ጋር በነበረው መርሀግብር ጆታ ተቀይሮ ገብቶ በ21 ሴኮንድ ግብ አስቆጥሯል። ይህም በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ተቀይሮ ገብቶ ፈጣን ግብ በማስቆጠር የመጀመሪያ ተጫዋች ሆኗል።
አስደናቂ ብቃት እያሳየ ባለበት አፍላ የእግር ኳስ እድሜ ላይ ነው ጆታ ህይወቱ ያለፈው። ፖርቹጋላዊው ባለተሰጥኦ ምርጥ ብቃቱን ለዓለም እግር ኳስ በሚያበረክትበት ወቅት በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱን አጥቷል። ለቀዩ መለያ ያደረገው ተጋድሎ በሊቨርፑላውያን ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፎለታል። የመርሲሳይዱ ክለብ ደጋፊዎቹም ታታሪነቱን ፣ጠንካራ የሥራ ባህሉን እና ለእግር ኳስ ያለውን ፍቅር ይወዱለታል። የመርሲሳይዱ ክለብም የዲያጎ ጆታን መለያ ቁጥር በክብር እንዲቀመጥ አድርጓል። አርኔ ስሎት ሊቨርፑልን ከተቀላቀሉ በኋላ በፊት መስመሩ የመጀመሪያ ምርጫቸው እረሱ ነበር። ባለቀ እና በወሳኝ ሰዓት ግብ ማስቆጠር መቻሉ የአርኔ ስሎት በፊት መስመሩ የመጀመሪያ ተመራጭ አድርጎት እንደነበር ይነገራል።
የቀድሞው የሊቨረፑሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ “የሚወደድ ሰው ነበር” ሲል ተናግሯል”። የፖርቹጋሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሊዊስ ሞንቴኔግሮ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው “የጆታን እና የወንድሙን ሞት መስማታችን አስደንጋጭ ዜና ነው” ነው በማለት ለወዳጆቹ እና ቤተሰቦቹ መጽናናትን ተመኝተዋል። የሊቨርፑሉ ኮከብ ሞሀመድ ሳላህ “ሀዘኔን ለመግለጽ ቃላት የለኝም” ብሏል። ጆታ ግለኛ የሚባል ሰው እንደነበር ዘ አትሌቲክ አስነብቧል። ቨርጅል ቫንዳይክን ጨምሮ ብዙ ተጫዋቾች የቀን ተቀን ውሎውን አለመጠየቃቸው የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል ነው የተባለው። በርካታ የአውሮፓ እግር ኳስ ተጫዋቾች፣ ክለቦች፣ የእግር ኳስ ባለሙያዎች፣ አሰልጣኞች እና ደጋፊዎች በወንድማማቾቹ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
ሜዳ ላይ አንድ የማይሆኑት ከፍተኛ የተቀናቃኝ ስሜት ያላቸው እና አንደኛው የአንደኛውን ስኬት የማይመኙት ሁለቱ የከተማ ተቀናቃኝ ክለቦች ኤቨርተን እና ሊቨርፑል በጆታ ሞት እኩል አዝነዋል፤ ተከፍተዋል። ጆታ በአዕምሮ እና በአካል ብቃት የዳበረ እና ብርቱ ተጫዋች እንደነበር ብዙዎች ይመሰክሩለታል። ታዲያ የእርሱን ሞት ተከትሎ ብዙ ስፖርተኞች በመልካም ነገር ራሳቸውን እንዲገነቡ ከተኙበት አንቅቷቸዋል።
ለታላላቅ ስፖርተኞች በህክምና ባለሙያ የሚሰጣቸውን ምክር እና ትዕዛዝ ማክበር እንደሚገባቸው መረጃው አስነብቧል። ዝነኞች እና ስፖርተኞች ብዙ ኅላፊነት ያለባቸው በርካታ ተከታይ ያላቸው በመሆኑ እያንዳንዷ እንቅስቃሴያቸው እና ተግባራቸው ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን እንደሚገባ ያስረዳል። ህይወት አጭር በመሆኗ ሰዎች በዘመናት የማይደበዝዝ የራሳቸውን አሻራ ማስቀመጥ እንዳለባቸው የጆታ ሞት ያስተምራል ይላል መረጃወ።
ስፖርተኞች የህክምና ክትትል እያደረጉ ማሽከርከር እና መሰል ትኩረት የሚጠይቀውን ሥራ መሥራት እንደሌለባቸው መረጃዎች አመልክተዋል። በርካታ በስፖርት እና መዝናኛው ኢንዱስትሪ ያሉ ዝነኞች “በኅላፊነት ማሽከርከር” እንዳለባቸው ማስታወሻዎችን በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው እየለጠፉ ናቸው። የዲያጎ ጆታ ሞት ለሁሉም ስፖርተኛ የማንቂያ ደወል ሆኗል።
የሞት ጥሪያችንን ለማዘግየት በጥበብ መኖር፣ የግል ጤንነታችንን ማስቀደም እና የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ የሚደረጉ ተገቢ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን መቀነስ እና ከሰዎች ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ማሳደግ ተገቢ ነው ይላል መረጃው። የሰው ልጅ ትልቁ ሌጋሲ እና መታሰቢያው ሰዎች ያላቸው የእርስ በእርስ ግንኙነት እና ባህሪ እንጂ የሚያሸንፉት ዋንጫ እንዳልሆነም ጭምር መረጃው ያስነብባል፡፡ ።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም