ሞትን የረታዉ

0
149

የ46 ዓመቱ ጐልማሳ ታላቅ ወንድሙን እና የወንድሙን ልጅ በአነስተኛ ጀልባ አሳፍሮ በሩሲያ በስተምሥራቅ በሚገኘው ውቅያኖስ ላይ ዓሳነባሪ ፍለጋ ከቤት ከወጡ ከ67 ቀናት በኋላ በህይወት መገኘቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ሰሞኑን ለአንባብ አብቅቶታል::
የ46 ዓመቱ ሚካኤል ፒቹጊን፣ የ49 ዓመቱን ታላቅ ወንድሙን ከ15 ዓመቱ ልጁ ጋር ዓየር በሚነፋ ጀልባ አሳፍሮ ወደ ካብሮቭስክ ግዛት ሳክሃሊን ደሴት ያመሩት ከወራት በፊት ነበር:: ከተወሰኑ ቀናት በኋላም የተጓዦቹ ቤተሰቦች ግንኙነታቸው መቋረጡን እና መጥፋታቸውን ለአካባቢው ባለስልጣናት አስታውቀዋል::
የአካባቢው ባለስልጣናት በአነስተኛ አውሮኘላን እና በሄሊኮኘተር ፍለጋ ቢያደርጉም ማግኘት አልቻሉም:: ቀናት ቀናትን እየወለዱ አንድ ወር አልፎ ሁለተኛው ወር ተደገመ:: የመስከረም ወርም የጠፉትን ቤተሰባማቾች የማግኘት እድል ወደ ዜሮ የተቃረበበት ነበር:: በዚሁ መካከል ጥቅምት 14 በ67ኛው ቀን በአሳ አጥማጆች ጀልባ ሚካኤል ፒቹጊን በተነፈሰችው ጀልባው ላይ ተኝቶ ተገኘ::
ተጐጂውን ያገኙት ወደ ሚካኤል ጀልባ ገመድ ቢወረወሩለትም መያዝ አልቻለም- በእጅጉ በርሀብ፣ በጥም ድክሞ ነበርና:: በተአምር ህይወቱ የተረፈውን ጐልማሳ በሚያጣጥርበት ደርሰው ወደ ጀልባቸው አውጥተው ርዳታ ወደ ሚያገኝበት ቦታ ማድረስ ቻሉ – ዓሣ አጥማጆቹ::
ድረ ገጹ የፒቹጊን ወንድም እና የወንድሙ ልጅ እድለኞች አለመሆናቸውንም አስነብቧል:: የ15 ዓመቱ የወንድሙ ልጅ በመስከረም ወር መጀመሪያ ህይወቱን አጥቷል:: ለሁለት ሳምንት ወንድማማቾቹ አብረው ቆይተው ታላቅዬው የሚቀመጥበት፣ የሚተኛበት አካሉ በመቁሰሉ ህይወቱ ማለፉን ተናግሯል- ሚካኤል ፒቹጊን::
በማእበል እንዳይወሰዱ የሁለቱን አባትና ልጅ አስከሬን ከተነፈሰው ጀልባ ጋር አስሮ ተስፋ ቆርጦ በተጋደመበት በዓሣ አስጋሪዎች ጀልባ እይታ ውስጥ በመግባቱ ህይወቱ ሊተርፍ መቻሉን ድረ ገጹ አስነብቧል::
ሚካሂል ፒቹጊን ከ67 ቀናት በኋላ ህይወቱ በተአምር ለመትረፉ በአንድ በኩል ወደባህሩ ከመግባቱ በፊት ክብደቱ ከ90 ኪሎ ግራም በላይ እንደነበር ሲገኝ ግን ክብደቱ በግማሽ መቀነሱ በምክንያትነት ተጠቅሷል::
በማጠቃለያነት ዘመዳማቾቹ ተሳፍረው ወደ ባህር የገቡበት ጀልባ በርቀት መጓጓዣነት ማዋል የማይቻል – በህግም የሚያስቀጣ መሆኑ ተጠቁሟል:: በመሆኑም ሚካኤል ፒቹጊን እስከ ሰባት ዓመት እስራት እንደሚጠብቀው ነው ጽሁፉ ያደማደመው::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here