ሞት ያንዣበበባቸዉ

0
119

በቦሊቪያ በንግድ እንቅስቃሴዋ በምትታወቀው ኤልአልቶ ከተማ በስተምስራቅ በገደል ጫፍ የተገነቡ ቤቶች ለመሬት መንሸራተት አደጋ ከመጋለጣቸው አንፃር  “ገዳዮቹ ቤቶች” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው መሆኑን ኦዲት ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

በኤልአልቶ ከተማ አስደናቂ የመሬት አቀማመጥ በሚያስቃኘው ቀጣና በገደል ጫፍ የተገነቡት የመኖሪያ ቤቶች ለመንሸራተት የተጋለጡ፣ በአደገኛ ሁኔታ ላይ በመገኘታቸው ነው ስያሜው የተሰጣቸው፡፡

በቅርብ ጊዜያት በቀጣናው ከፍተኛ ዝናብ እየጣለ መሆኑ አደጋውን የከፋ ሊያደርገው እንደሚችልም ነው የተጠቆመው፡፡

ስጋት ባንዣበበባቸው መኖሪያ ቤቶች የሚገኙ ኗሪዎች ምንም ዓይነት ፍርሃት እና ስጋት እንዳልታየባቸው ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡ ለዚህ አብነቱ አንድም ኗሪ ቦታውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሆኖ አለመገኘቱ ነው የተጠቀሰው፡፡

የመንሸራተት ስጋት ባየለበት፣ ሞት ባንዥበበበት የገደል ጫፍ የከተሙት “ሻማን” ወይም  “ያታሪ” በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ነጋዴዎች ቦታው የንግድ ስራ ማእከል በመሆኑ ንቅንቅ እንደማይሉ ነው አስረግጠው የተናገሩት፡፡

በገደል አፋፍ ለሚገኙት ኗሪዎች የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ከፍተኛ ባለሙያ ለውኃ፣ ለአካባቢ ፅዳት እና ንፅህና ለመሳሰሉ አገልግሎቶች ተደራሽነትም አስቸጋሪ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡

ከኗሪዎቹ አንዱ ለሮይተርስ የዜና ማእከል በሰጠው አስተያየት በአካባቢው በሚጥለው ዝናብ ገደሉ እንዳይሸረሸርና ተደርምሶ አደጋ እንዳያስከትል የተፋሰሱን አቅጣጫ ለማስቀየር እንደሚተጉ ነው ያስታወቁት፡፡

የከተማዋ ኃላፊዎች መኖሪያ ቤቶቹ ከሚገኙበት የገደል አፋፍ መናዳቸው አይቀሬ መሆኑን ጠቁመው ፈጥነው ለቀው እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ገደሉ 90 ዲግሪ ወይም ቀጥ ያለ ተዳፉት በመሆኑ መናዱ እንደማይቀር ያሰመሩበት የከተማዋ ኃላፊዎች ኗሪዎቹ በእምቢተኝነታቸው የሚገፉ ከሆነ በኃይል እንደሚያሰነሷቸው ነው ያሰጠነቀቁት፡፡

በኗሪዎቹ በኩል ከኃላፊዎቹ ሊደርስ ይችላል ከሚል ስጋት በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ከመልቀቅ ይልቅ በሚያምኑበት እምነት መሰረት ለሚያመልኩት ጣኦት ክፉውን እንዲያርቅላቸው መስዋእት ማቅረብ መፍትሄ እንደሚያስገኝላቸው ነው ያረጋገጡት፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የታኅሳስ 14  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here