ሞፈር እና ቀንበር አዋዶ ለሚያርሰዉ…

0
242

በሬ፣ ፈረስ እና መሰል እንስሳትን በመጠቀም የግብርና ሥራን ይከዉን የነበርዉ የሰዉ ልጅ የኢንዱስትሪ አብዮት መከሰትን ተከትሎ ጉልበት ቆጣቢ የግብርና መሳሪያዎችን መጠቀም ችሏል:: በቀላሉ በእጅ ከሚሰሩ እስከ ዘመናዊ እና የተራቀቁ መሳሪያዎችን በመጠቀም የግብርናውን ሥራ ለማቀላጠፍ እና ምርትን ለማሳደግ ሀገራት የግብርና ሜካናይዜሽን ተግባር ላይ በብዛት እየተሰማሩ ይገኛሉ:: አርሶ አደሮቻቸው የግብርና ሜካናይዜሽን እንዲጠቀሙ ማድረግ የቻሉ ሀገራት በአነስተኛ የሰው ሀይል ከፍተኛ የግብርና ምርት እንዲያገኙ ማድረግ ችለዋል::

ላቲን አሜሪካዊት ሀገር ብራዚል ለግብርና ሜካናይዜሽን በሰጠችው ትኩረት እ.ኤ.አ ከ1960 ዎች እስከ 2018 ብቻ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን በመጠቀም በግብርናው ዘርፍ ስድስት እጥፍ እድገት ማስመዝገብ እንደቻለች የ(oawng.com ) መረጃ ያመለክታል:: እንደ ዓለም አቀፍ የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) መረጃ ከሆነ ብራዚል ለውጭ ገበያ አቅርባ ከምታገኘው ገቢ ውስጥ 20 በመቶ የግብርና ውጤቶች መሆናቸው የግብርና ሜካናይዜሽን ተሞክሮዋ ማሳያ ነው:: በተመሳሳይ አውሮፓዊት ሀገር እንግሊዝ ለግብርናው ትልቅ ትኩረት በመስጠቷ በሀገሪቱ ትራክተሮችን የሚያመርቱ የተለያዩ ድርጅቶች አሏት::

በግብርና ሜካናይዜሽን የተሻለ ተሞክሮ ያላት ሀገር ሌላዋ ቬትናም በስፋት ትራክተር እና ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎችን ትጠቀማለች:: ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ህንድ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ባደረገችው ጥረት ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርቷ (GDP) ውስጥ ከ 17 እስከ 18 በመቶ የሚሆነውን የግብርና ዘርፍ እንደሚሸፍን መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ፣ ግብፅ እና ታንዛንያ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል የግብርና ሜካናይዜሽንን በመተግበር የግብርና ምርትን ለማሳደግ የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ ሀገራት መሆናቸውን የዶቼ ቬለ መረጃ ያሳያል:: ኢትዮጵያም ዘመናዊ የግብርና ሜካናይዜሽን ለማስፋፋት በትኩረት እየሰራች ትገኛለች:: በሀገራችን የእርሻ ሥራ በስፋት የመተግበሩን ያህል በሰብል አሰባሰብ ወቅት የምርት ብክነትን ለመቀነስ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ድክመቶች ይታያሉ:: ይህን ችግር ለማቃለልም ባለፉት ሦስት ዓመታት አርሶ አደሮች ምርታማ እንዲሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እንዲያገኙ ጥረቶች ተደርገዋል::

የሀገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እና የብዙዎች መተዳደሪያ የሆነውን የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማዘመን በርካታ  ሥራዎች ይጠይቃል::  የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል:: ቢሮው የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ዘመናዊ የእርሻ ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ይገኛል:: ሆኖም በቅድመ እና ድህረ ምርት ስብሰባ ወቅት የሚባክነው ምርት ከፍተኛ ነው:: የእርሻ የፈጠራ ውጤቶችን ማበረታታት፣ የእርሻ ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ግድ ይላል:: የክልሉ የእርሻ መሬት ለሜካናይዜሽን ሥራ የተመቸ በመሆኑ ምርታማነትን ለማሳደግ በክልሉ ግብርና ቢሮ በኩል 1ሺህ 890 ትራክተሮች፣ 54 ኮምባይነሮች፣ 25 ሺህ 82 የውሃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖች፣ 3 ሺህ 350   የበቆሎ መፈልፈያ ዘመናዊ መሳሪያዎች  እና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች  ለአርሶ አደሮች እንደተሰራጩ ከቢሮዉ ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል:: ይህም ሆኖ ክልሉ ካለው የሚለማ መሬት አንፃር እስካሁን የተጠቀመው ቴክኖሎጂ  ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: ለዚህም ደግሞ በርካታ ጥራቱን የጠበቀ ቴክኖሎጂ ያስፈልገዋል::  አጋር እና ባለድርሻ አካላትም ለውጤታማነቱ በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል::

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በ2016 ዓ.ም ባለፉት 10 ወራት 148 የእርሻ ትራክተሮች እና 13 ኮምባይነሮች ለአርሶ አደሩ ተሰራጭተዋል:: ቀሪ 75 ትራክተሮች ደግሞ በጉዞ ላይ መሆናቸዉን አመላክተዋል::

የተሰራጩት የእርሻ ትራክተሮች አርሶ አደሩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሰብል ምርታማነትን ማሳደግ እንዲቻል ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል:: ሌሎች የግብርና ምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂን በማቅረብ ሥራዎች ተጠናክርዉ መቀጠል እንዳለባቸዉ አስረድተዋል:: አርሶ አደሩን ከበሬ ጫንቃ ወደ ትራክተር ለመመለስ እና ሰብልን በክላስተር ወይም በኩታ ገጠም ለማምረት ሰፊ ሥራ እየተሰራ ነዉ ብለዋል:: በክልሉ ዋነኛ ጠላት የሆነውን ድህነት ለመቀነስ ዘመናዊ የእርሻ ትራክተር በማሰራጨት ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት እንደሚቻል ተናግረዋል:: ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች 1 ሺህ 890 ትራክተሮች እንደተሰራጩ  አስረድተዋል::

ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም “ጉዞ ወደ ግብርና ሜካናይዜሽን” በሚል መሪ መልዕክት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከኢትጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ለደቡብ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች እንዲሁም ለደቡብ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች 44 ዘመናዊ ትራክተሮች ርክክብ አድርጓል:: በተረከቡት የእርሻ ትራክተር ሰብልን በአግባቡ አልምተው ተጠቃሚ ለመሆን መዘጋጀታቸውን የገለፁት ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ አቦኮኪት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብላታ እሸቴ ተሰማ ናቸው::

በአራት ሄክታር መሬታቸው ሩዝ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ሽንብራ እና ሌሎች ሰብሎችን በማምረት ከራሳቸው አልፈው ለተራበው ገበያ ያቀርባሉ:: ለረጅም ዓመታት በበሬ የእርሻ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ትራክተር እየተከራዩ ነበር የእርሻ ሥራቸውን የሚያከናውኑት:: እንዲህ ሆኖም ጥሩ ምርት እያመረቱ መሆኑን ነግረውናል:: አርሶ አደር ብላታ እሸቴ አሁን ላይ እራሳቸው የሚያርሱበት አዲስ ትራክተር ስለተሰጣቸው በተገቢው መንገድ በማረስ የተሻለ ምርት ለማምረት እንደሚያስችላቸው ለበኩር ጋዜጣ ተናግረዋል::

ዘመናዊ የእርሻ ትራክተር በማግኘታቸው የበለጠ የመለወጥ ፍላጎት እንዳደረባቸውም ገልፀዋል:: በሚኖሩበት አካባቢ የእርሻ ትራክተር እጥረት በመኖሩ ተጨማሪ ትራክተር በመግባቱ ችግሩን እንደሚያቃልለው አስረድተዋል::  በበሬ ሲያርሱ ጉልበት እና ጊዜ ይባክናል፤ እንዲሁም የሚፈልጉትን ያህል የእርሻ መሬት ማረስ እንደሚቸገሩ እና በአጭር ጊዜ ሥራን ማከናወን እንደማይችሉ ተናግረዋል::

ሌላው የደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦከምከም ወረዳ ቡራ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር በላይነህ ውቤ ናቸው:: ክረምት ከበጋ ምርትን የሚያመርቱ ጠንካራ ገበሬ ናቸው:: እንደ እርሳቸው ገለፃ በሁለት ሄክታር መሬታቸው ጤፍ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ሩዝ፣ ስንዴ እና ሌሎች ሰብሎችን ለዘመናት በበሬ በማረስ ሲያመርቱ ቆይተዋል::

የግብርና ሥራቸው ውጤታማ እንዳይሆን ከሚፈትኗቸው ችግሮች መካከል ከበሬ ትከሻ መላቀቅ አለመቻላቸው ነው:: የአማራ ክልል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለግብርና ቴክኖሎጂ በሰጠው ትኩረት ትራክተሮች እና የሰብል መሰብሰቢያ ኮምባይነሮች  ለአርሶ አደሮች እየተሰራጩ ይገኛል:: ይህ የግብርና ሜካናይዜሽን ማስፋፋት ሥራ አርሶ አደር በላይነህ ውቤንም የትራክተር ባለቤት አድርጓል:: ከባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ሙሉ ለሙሉ ተላቀው ወደ ሜካናይዜሽን እርሻ ሲሻገሩ ከድካም ከመላቀቅ ባለፈ በጥራት እና በመጠን የተሻለ ምርትን አገኛለሁ የሚል ተስፋ ሰንቀዋል::

አሁን በተሰጣቸው ትራክተር ካረሱ  ጉልበት እና ጊዜያቸውን በመቆጠብ ከፍተኛ ምርት እንደሚያገኙ ተናግረዋል:: የተሰጣቸውን ትራክተርም ለሌሎች አርሶ አደሮች በማከራየት ተሞክሮን ለማስፋት እንደሚሰሩም አክለዋል:: ባለፉት ዓመታት በበሬ ሲያርሱ ከፍተኛ ድካም እንደነበረው የሚናገሩት አርሶ አደር በላይነህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትራክተር እየተከራዩ በማረሳቸው ከብዙ ድካም ድነዋል:: ምርትን ማሳደግ ችለዋል:: ጊዜን ቆጥበዋል:: ከጉልበት ብዝበዛ ድነዋል:: አሁን ላይ ተጨማሪ ትራክተር በማግኘታቸው በፈለጉት ሰዓት የእርሻ ሥራቸውን ማከናዎን እንደሚችሉ አስረድተዋል:: መሬቱ በወቅቱ ከታረሰ እና ከተዘራ የተሻለ ምርት እንደሚሰጥም አስረድተዋል::

በበሬ እርሻ ዘልቆ መታረስ ያልተቻለውንም አዲስ አፈር በማውጣት ለምነቱን በመጨመር የተሻለ ምርት እንደሚያስገኝ አርሶ አደሩ ገልፀዋል:: ሞፈር ቀንበር ተሸክሞ ከእርሻ ቦታ ድረስ መሄዱ፣ መለመሙ፣ ማንሳት መጣሉ፣ ግባ ማለቱ፣ ከጭቃ ጋር ጅራፍ ማውጀምጀሙ፣ ተመለስ ሂድ ማለቱ፣ ፍጥነት አለመኖሩ፣ የሚፈለገውን ያህል ማሳ አለማረስ እና ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ፈታኝ ናቸው ብለዋል:: ነገር ግን ዘመናዊ እርሻ ትራክተር መምጣቱ ይህን ሁሉ ድካም ከማቃለል ባሻገር የተሻለ ምርት እንደሚያስገኝ አስረድተዋል::

የአርሶ አደር ብላታ እሸቴ እና የአርሶ አደር በላይነህን ከዚህ ቀደም ይገጥማቸዉ የነበረዉን ውጣ ውረድ ተመለከትን እንጂ አሁንም ድረስ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ዘመናዊ የእርሻ ትራክተሮች እና ኮምባይነሮች ባለማግኘታቸዉ የሚቸገሩ አርሶ አደሮች በርካታ ናቸው:: በክልሉ ከሚታረሰው 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በትራክተር ለማረስ ምቹ መሬት መኖሩን የግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል:: እስካሁን በሜካናይዜሽን እየታረሰ ያለዉ ግን 760 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ ነው:: የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ዘመናዊ የግብርና ሜካናይዜሽንን አስፋፍቶ መጠቀም ተገቢ ነው:: በክልሉ የግብርና ሜካናይዜሽን አቅርቦት እየተሻሻለ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል:: ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂን በብዛት እና በጥራት መጠቀም ይገባል:: የአርሶ አደሮችን ጊዜ እና ጉልበት ለመቆጠብ መስራትም ይጠይቃል::

በቀጣይም ሁለት መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ግብርና ቢሮ ለይቶ ወደ ሥራ የገባባቸው ጉዳዮች መኖራቸዉን ድረስ ሳህሉ አስረድተዋል:: የመጀመሪያው መዋቅራዊ ችግሩን መፍታት ነው:: በክልል ደረጃ ጥናት ተደርጎ ለሲቪል ኮሚሽን ሰርቢስ ቀርቦ እንዲፀድቅ በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል:: ይህን ዘርፍ የሚከታተል በቂ ዕውቀት ያለው የሥራ ስምሪት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል:: ሁለተኛው ችግር የጥገና  ማዕከላት ነው::  ትራክተሮች ሲበላሹ ሙሉ የጥገና አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል ሥራ መስራት ያስፈልጋል:: የጥገና መስጫ ማዕከላትም የሚሰጥባቸው ቦታዎች ተለይተዋል::

ከአጋር አካላት ጋር በመሆን እነዚህን ማዕከላት በፋይናንስ እና በክህሎት ለማገዝ ሰፊ ሥራም እንደሚሰራ አመልክተዋል:: ለአርሶ አደሮች የሚሰራጩ ቴክኖሎጂዎች በብልሽት ምክንያት እንዳይቆሙ የጥገና እና የሰርቪስ አገልግሎት በሚያገኙበት ሁኔታ ፖሊሲ ተነድፎ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል:: ድህነት የሚሸነፈው የግብርና ሥራ በሜካናይዜሽን  ሲታገዝ መሆኑን  ያነሱት ዶክተር ድረስ የተገዙ ቴክኖሎጂ ብልሽት ሲገጥማቸው የሚስተካከሉበት በየአካባቢዉ የጥገና ማዕከላት በቀጣይ እንደሚቋቋሙ ለበኩር ጋዜጣ ተናግረዋል:: በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን አለመጣጣም እና የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት የሚቻለው ለአርሶ አደሩ የግብርና ሜካናይዜሽን መጠቀም ሲችል እና ሙሉ ጊዜውን ለልማት ሲያውል ነው ብለዋል::

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here