ሁለት ጓደኛማቾች ሦስተኛ ጓደኛቸው እናቱን በድንገተኛ አደጋ በሞት መነጠቁን ይሰሙና በጣም ያዝናሉ፤ በኢትዮጵያዊያን ባሕል መሰረት የሞተን መቅበር ባይቻል እንኳን ለቅሶ ደርሶ ማስተዛዘን የግድ ነው:: እነዚህ ሁለት ጓደኛማቾችም የሌላው ጓደኛቸውን እናት መሞት የሰሙት ዘግየት ብለው ቢሆንም ቀብር አልደረስንም ብለው ከጓደኛቸው ሀዘን አልቀሩም::
ጓደኛቸው እናቱ ያለ አባት ያሳደጉት ብቸኛ ልጃቸው በመሆኑ በሀዘን በጣም ተጐድቶ ያገኙታል፤ የሰው ልጅ ምንም ያህል የሚወደውን ሰው በሞት ቢያጣ ከማዘን ባለፈ አብሮት ሊቀበር አይችልም:: የዚህም ልጅ ሀዘን እጅግ የከፋ ቢሆንም ከእናቱ ጋር አብሮ መቀበር ስለማይችል “ይብላኝ እንጂ ለሟች፣ ቀሪማ ምን ይሆናል?” በሚለው አባባላችን ውስጥ ተሸሽጐ ቀሪ ህይወቱን ይቀጥላል::
የልጁ ጓደኞች እናቱንም ጭምር ከነ ማንነታቸው ያውቋቸው ስለነበር ለቅሶ የደረሱት ለቅሶ ለመድረስ ሲሉ ብቻ አልነበረም:: የሟቿን ደግነት እና ለልጃቸው የነበራቸውን ፍቅር እያስታወሱ እንባቸውን አፍስሰዋል:: በተለይ ደግሞ የጓደኛቸው ሀዘን ውስጣቸውን ጠልቆ ስለተሰማቸው የእነሱም ሀዘን የመረረ ሆኖ ታይቷል::
የሥነ ልቦና ባለሙያዎች የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎች ሀዘናቸውን በበዛ እንባ እንዲገልፁ ይመክራሉ:: ለሞተባቸው ሰው ሀዘናቸውን በበዛ እንባ የገለፁ ሰዎች በውስጣቸው ተዳፍኖ የሚቀር ሀዘን ስለማይኖር ማልቀሳቸው በጠቃሚነቱ ይመከራል:: ይሁን እንጂ የእኛ ሀገር የለቅሶ አደራረስ ድንኳን እስኪፈርስ፣ እስከ ሰልስቱ፣ እስከ ሰባቱ፣ የቀጠሮ ለቅሶ እና ሌላም እየተባለ ስለሚራዘም ለቀስተኞች እርማቸውን ከማውጣት አልፈው በለቅሶ ሰበብ እንዲጐዱ የምናደርግበት የሀዘን ሥርዓት ነው ያለን::
ከላይ ወደ ጀመርኩት ታሪክ ልመልሳችሁ እና የልጁ ጓደኞች ልጁን ከማስተዛዘንም ባለፈ የራሳቸውንም ሀዘን በተገቢው መልኩ ገልፀዋል:: በሀዘን ቤቱ ከተዘጋጀው የእዝን ንፍሮ እና እንጀራ በልተውም ከሀዘኑ ቤት ወጥተዋል፤ የዚህ ሀሳቤ ወይም ትዝብቴ መነሻ የሆነው ነገርም ማጠንጠኛው እዚህ ጋር ነው:: አንደኛው ልጅ የለቅሶ ቤቱን ንፍሮ እና እንጀራ በሽሮ ከበላ በኋላ ሀዘንተኞቹን ተሰናብቶ ሊወጣ ሲል “እግዚያብሔር ይስልጥን” በማለት ያመሰግናል::
በኢትዮጵያዊያን ልማድ መሰረት ለሀዘን ቤት መስተንግዶ እግዚያብሔር ይስጥልን አይባልም፤ የሚባለው “እግዚያብሔር ያጽናችሁ” ነው:: ልጁ በሌላኛው ጓደኛው ስህተቱ ከተነገረው በኋላ በስህተቱ በጣም ተፀጽቷል፤ በልጁ አስተሳሰብ ያንን ሁሉ ሀዘንተኛ ምሳ ላበሉት ሀዘንተኞች ምስጋና ማቅረብ አለብኝ ብሎ በስህተት እግዚያብሔር ይስጥልን ብሏል::
ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም ሀብታም ነን በሚሉ ሰዎች ዘንድ እየታየ ያለው የሀዘን ቤት መስተንግዶ ግን ከላይ የገለጽኩትን ልጅ ስህተት ላለመድገማችን እርግጠኛ አያደርገንም:: በለቅሶ ቤቱ የሚዘጋጀው ድግስ ስለ ሟች እያብሰለሰሉ ጥሬ ከመቆርጠም ጋር በፍፁም የተቃረነ ነው:: በዚያ ሁሉ የምግብ ዓይነት /ቡፌ/ መሀል ስለ ሟች ማሰብ ባልተፃፈ ሕግ የተከለከለ ሁሉ ይመስላል::
በጠረጴዛ ላይ የሚደረደረው የወጥ ብዛት እንኳንስ ለመብላት ለመቁጠር የሚያታክት ነው፤ በቢራ ሳጥን /ካሳ/ ውስጥ የተደረደሩት የቢራ ዓይነቶችም ቢሆኑ የጠጪዎችን ዐይን እና ጉሮሮ የሚያማልሉ ናቸው:: ይሄ ሁሉ የምግብ እና የመጠጥ ድግስ ለሟች አንዳችም ነገር እንደማይፈጥርለት ቢታወቅም አዛኝ መሳዮች ግን በደገሱት ድግስ ልክ ያዘኑ መሆናቸው እንዲታወቅላቸው ይፈልጋሉ::
በለቅሶ ቤት ያ ሁሉ ምግብ ተበልቶ እና ያ ሁሉ አልኮል ተጠጥቶ ሲያበቃ የሚያለቅስ ሰው ድምጽ ሲሰማ “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” ከሚለው ሀሜታችን የሚያድነው አይሆንም:: ለመሆኑ በሀዘን ስም ደግሶ የመዝናናት ልምድ ከየት የመጣ ነው? ጥሬ እየቆረጠሙ እና እህህ… እያበዙ የሟችን ደግነት ማውሳቱ ተዘንግቶ ለታይታ የሚሆን ድግስ በመደገስ፣ ያንኑ ድግስ እና ተመጋቢዎቹን በቪዲዮ እየቀረጹ ምስል ማስቀረቱስ ቢሆን ሟችን ለማስታወስ ወይስ ድግሱን ለማስታወስ ይረዳል?
እኛ ኢትዮጵያዊያን “ሠርግ እና ሞት አንድ ነው” ስንል የሰሙ የዋሆች ይመስሉኛል የሠርግ ሥነ ሥርዓታችንን እና የሀዘን ሥርዓታችንን አንድ ዓይነት ለማድረግ እየጣሩ ያሉት። በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ሠርግ እና ሞት አንድ ነው መባሉ ደስታንም ሆነ ሀዘንን ብዙ ሰው ይጋራዋል ለማለት እንጂ በሀዘን ቀን ደግሶ ብሉልኝ እና ጠጡልኝ ማለት ፈጽሞ ኢትዮጵያዊ ባህላችንም ሆነ ልማዳችን አይደለም::
ሀገራችን ብዙ ብሔር እና የማኅበረሰብ ሥሪቶች ያሏት ሀገር እንደመሆኗ መጠን የሠርግም ሆነ የሀዘን ሥርዓቶቻችን የተለያዩ ናቸው፤ ያም ቢሆን ግን በየትኛውም ብሔረሰብ ዘንድ ሰው ስለሞተ “ዲል” ያለ ድግስ ደግሶ በአልኮል የመራጨት የሀዘን ሥነ ሥርዓት የለም:: በሀዘን የተሰበሩ ልቦችን በሚያመጡት ጥራቱን የጠበቀ ውስኪ ማጽናናትም በኛ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ያልተለመደ እና ወደፊትም ሊለመድ የማይገባው መጥፎ ልማድ ነው::
“እስኪ እንደ ደሀ መቃብር አታካልቡኝ” የሚለው አባባላችን የደሀ ሰው ቀብር በሁሉም ነገሩ የተፋጠነ ነው ለማለት እንጂ፣ የደሀ እና የሀብታም ሟቾች ሕይወት የተለያዩ ናቸው ማለት አይደለም:: “ለቅሶው እንደ ሠርግ ደምቆ ነበር” ማለትም እኮ ለሟቹ ብዙ ሰው አዝኖለታል ማለት እንጂ የሟቹ ሞት እንደ ሠርግ የተወደደ ነው ማለት አይደለም::
በነገራችን ላይ የሀዘን ቤት ድንኳኖቻችን ውስጥ ቅጥ ያጡ የምግብ እና የመጠጥ ድግሶችን ብቻ ሳይሆን ቅጥ ያጣ ቁማርተኝነትም እየተስተዋለባቸው ነው:: የሀዘን ቤት ድንኳን ውስጥ ገብቶ ለረዥም ሰዓት ሀዘንተኞችን ለማጽናናት በሚል የተጀመረው የካርታ ጨዋታ ውሉን ስቶ በብዙ ብር ቁማር ወደ መቋመር ደረጃ አድጓል::
ሟችንም ሆነ የሟችን ቤተሰቦች ሳያውቁ የሀዘን ድንኳኖች በተጣሉባቸው ቦታዎች ሁሉ እየገቡ ቁማር የሚጫወቱ ሰዎችን ስናይ የሀዘናችን ጉዳይ ወዴት እያመራ ነው? ወደሚል ጥያቄ ይወስደናል:: በሀዘን ሰበብ ትልቅ ድግስ ደግሶ እንደ ሠርግ ድንኳን ሰባሪዎች ወይም ሳይጠሩ በሠርጉ ላይ የሚገኙ ሰዎች ዓይነት በሀዘን ቤት ሊገኙ ቢከጅሉም የማያስገርም እየሆነ ነው::
ከመጠን ያለፈ የሠርግ ድግስ የኋላ ቀርነት ምልክት ነው እያልን ባወራንበት አንደበታችን፣ ከመጠን ያለፈ የሀዘን ድግስ ስናይ ምን ልንል እንደምንችል መገመቱ ይከብደኛል:: ብዙ የተራቡ እና የተጠሙ ሰዎች ባሉባት ሀገራችን፣ ብዙ እንደ ሜቅዶኒያ ባሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥ የሚረዱ ሰዎች ባሉባት ሀገራችን፣ በድርቅ እና በጦርነቶች የተፈናቀሉ በርካታ ዜጐች ባሉባት ሀገራችን እና በተለያዩ ምክንያቶች የሰዎችን እጅ የሚጠብቁ ችግረኞች ባሉባት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሠርግ እና ለሀዘን የምታወጡት ቅጥ የለሸ ወጪ እንድንታዘባችሁ እንጂ እንድናወድሳችሁ እንደማያደርገን ብታውቁት ደስ ይለናል::
ሀዘን ማብዛት፣ ፊትን መቧጠጥ፣ ደረት መድቃት እና ሌሎችንም ከሀዘን ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ችግሮቻችንን በምናወግዝበት ልክ ቅጥ ያጣውን በሀዘን ስም መደገስም ልናወግዘው ይገባል:: እንባ ያጡ ዓይኖቻችሁን ከካሜራ ዓይኖች ደብቃችሁ፣ ቪዲዮ በማስቀረጽ ለሟቹ የምትጮሁ አስመሳዮችም ከአስመሳዩ ባህሪያችሁ ልትታቀቡ ይገባል::
ሟችን የመውደዳችን መገለጫው ሟች ከመሞቱ በፊት ያደረግንለት በጐ ነገሮች እንጂ ከሞተ በኋላ የደገስንለት ድግስ ወይም በሞቱ ስም ያወረድንለት ውስኪ እንዳልሆነም ልትገነዘቡ ይገባል:: በአጠቃላዩ ከልማዳችን አፈንግጦ የኛ የማይመስለውን የለቅሶ ሥርዓት ወደመጣበት ትመልሱልን ዘንድ አደራ ማለት እወዳለሁ::
በዚህ ዘመን ከምናየው የሀዘን ቤት የናጠጠ ድግስ አንፃር ለሀዘን የሄደ ሰው ደጋሾቹን “እግዚያብሔር ይስጣችሁ” ወይም “ከዓመት ዓመት ያድርሳችሁ” ቢላቸው ስህተቱ የደጋሾቹ እንጂ የታዳሚው እንዳልሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል:: በየለቅሶ ቤቶች የምናስተውላቸው የቪዲዮ ካሜራዎችም ከሙሉ የሙዚቃ ባንድ ጋር እንዳይመጡ እሰጋለሁ፤ ለሁሉም ፈጣሪያችን ቅጥ ላጣው የሀዘን ቤት ድግሳችን አስተዋይ ልቦናን፣ ለሀገራችን እና ለሕዝቧ ደግሞ ከሀዘን የራቀ ጊዜ እንዲሰጠን እመኛለሁ::
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም