“ሥራ ከተባለ አልችልም ብዬ ወደኋላ አልመለስም”

0
149

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

ባሕላዊ የውበት መጠበቂያ ዘዴዎች ዛሬ ላይ በዋና ዋና ከተሞች ሳይቀር እየተለመዱና እየተስፋፉ ይገኛል፤ ከእነዚህ መካከል የወይባ ጭስ መሞቅ ዋነኛው ነው::

በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚነገርለት የወይባ ጭስ በተለይ ለአራስ ሴቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው:: ከጠቀሜታዎቹ መካከል ሰውነትን ማጠንከር፣ መጠገን፣ ጤንነትን  እና ውበትን መጠበቅ  ይጠቀሳሉ::

ወ/ሮ መዓዛ አብዱ በባሕር ዳር ከተማ ዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ በተለምዶ መስጊድ ኮንዶሚኒየም አካባቢ ነዋሪ ስትሆን በዚሁ የሥራ ዘርፍ ተሰማርታ ትገኛለች፤ ተወልዳ ባደገችበት ደቡብ ወሎ ኩታበር አካባቢ በሁሉም ቤት የተለመደ የውበት መጠበቂያ መሆኑን ታስታውሳለች:: በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም በጊዜ ሂደት እየተለመደ የመጣ የውበት መጠበቂያ እንደሆነ ተናግራለች::

ወ/ሮ መዓዛ ኑሮዋን በባሕር ዳር ከተማ ካደረገች 16 ዓመታት እንደተቆጠሩ በማስታወስ ወደ ባሕር ዳር እንደገባች አካባቢውን ካለማወቅ፣ ከቤተሰብ በመለያየቷ እና ባለቤቷም በሥራ ምክንያት ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ኑሮ ትልቅ ፈተና ሆኖባት እንደነበረ ትገልፃለች::

በተወለደችበት አካባቢ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ልጅ ከማሳደግ ባሻገር ሁሉም ሰው ያገኘውን ነግዶ የሚያድርበት እንደነበረ የምታነሳው ወ/ሮ መዓዛ ኑሮዋን ለማሻሻል የንግድ ሥራን ለመሥራት ፍላጎት እንደነበራት ታስታውሳለች። ቢሆንም ግን ሥራውን ለመሥራት የሚያስችል ገንዘብ ስላልነበራት የቤት ኪራይ መክፈል አለመቻል፣ አለፍ ሲልም ሳትመገብ የማደር ፈተናን እንዳሳለፈች ታስታውሳለች::

የኑሮ ፈተናን ለመፍታት ታዲያ ባለቤቷ ከሚሰጣት ብር ላይ በመቀናነስ ያስቀመጠችውን 300 ብር በተከራየችው ቤት በር ላይ ከሰል እና ሳሙና መሸጥ ጀመረች::

በዚህም ማትረፍ ጀመረች፤ ለቤቷ የሚያስፈልጋትን ፍጆታ (በዋናነት ሽንኩርት) ማሟላት፣ ከዚያም የምትሸጠውን ነገር በመጨመር የንግድ ሥራዋን ቀጠለች፤ በዚህም እስከ 700 ብር ትርፍ አገኘች:: ትርፋማ እየሆነች ስትመጣም ባለቤቷ (አሽከርካሪ መሆኑን ልብ ይሏል) ከሚሄድበት አካባቢ እንጨት ስለሚያመጣላት ፊኖ ዱቄት በመግዛት እዚያው ቤቷ በር ላይ የውኃ ዳቦ በመጋገር መሸጥ በመጀመር ሥራዋን አጠናከረችው::

እንደ ወ/ሮ መዓዛ ማብራሪያ የችርቻሮ ንግድ ሥራው ትርፋማ ቢሆንም ዳቦ መሸጡ ደግሞ የተሻለ ገቢ አስገኘላት፤ በአንድ ቀን እስከ 12 ሙሉ ዳቦ በመጋገር እስከ መሸጥ በመድረሷም ይህም የእሷን እና የልጆቿን ፍላጎት መሟላት አስቻላት::

የሥራዋን ውጤታማነት ድጋፍ የተረዳው ባለቤቷ በሚሄድበት አካባቢ የሚያስፈልጋትን ነገር በማምጣት እንደሚያግዛት ትገልፃለች:: ሥራው ያለውን ጫናም  “ልጆቼ አባታቸው ብዙ ጊዜ ከጎናቸው ስለማይኖር የእሱን ሚና ሸፍኖ ማስተዳደር፣ ሥርዓት ማስያዝ እና ጥሩ ውጤት እንዲኖራቸው አድርጎ ማሳደግ ጫና ቢኖረውም ሥራዬ እንቅፋት እንዳይሆን ተጠንቅቄ  ነው የምመራው” ብላለች::

በሥራዋ የዳቦ መሸጥ ሥራው ጥሩ ውጤት እያመጣ ሲሄድ የሴቶች ፀጉር ቤት በመክፈት ሥራዋን አስፋፋች:: ከዚህ ጎን ለጎንም የድለላ ሥራ (ቤት ማከራየት፣ ማሻሻጥ) መሥራት መጀመሯን ነው የምትናገረው::  ይህም ተጨማሪ ገቢን እንድታገኝ ስላስቻላት ኮንደሚኒየም ቤት ገዛች፤ ከዚያም “ተጨማሪ የንግድ ሐሳብ በውስጤ ተመላለሰ” ትላለች:: ይም በተወለደችበት አካባቢ ሲዘወተር የምትመለከተው የወይባ ጭስ ነበር:: የሥራ ሐሳቡንም (በወይባ ውበትን የመጠበቅ ሥራ) በ2015 ዓ.ም መጨረሻ በ50 ሺህ ብር ካፒታል  በተግባር ወደ ሥራ ቀየረችው::

“ሥራ ከተባለ አልችልም ብዬ ወደኋላ የምመለስበት አንድም ነገር የለም፤ ይህም ኑሮ ሳይከብደኝ እንድኖር አስችሎኛል፤ ለነገም የተሻለ ነገር ለመሥራት ሐሳብ ይዤ ነው የምሄደው” የምትለው ወ/ሮ መዓዛ የወይባ እንጨቱን ከቤተሰብ አካባቢ (ኩታበር እና ባቲ አካባቢ) ታስመጣለች፤ የተጠቃሚው ሰው ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የምትናገረው ወ/ሮ መዓዛ  ሥራውንም በባሕር ዳር ከተማ የተለያዩ ክፍለ ከተማዎች ለማስፋፋት ሐሳብ እንዳላትም ነው የገለጸቸው::

ባለትዳር እና የአራት ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮዋ  የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ልጆቿ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው፤ ቀሪዎቹ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መሆናቸውን ነግራናለች::

ወ/ሮ መዓዛ እንዳለችው ወደ ትዳር ከገባች 22 ዓመታትን አስቆጥራለች:: አራት ልጆችንም አፍርተዋል።

ሥራ ስትጀምር 300 ብር ብቻ ካፒታል የነበራት ወ/ሮ መዓዛ ዛሬ ልጆቿ ምንም ነገር ሳይጎድልባቸው ከመኖራቸው ባሻገር ቤት ገዝቶ ሌላ ሥራ መሥራት የሚያስችል አቅም እንዳላት ገልፃ ወደ ፊትም ካለችበት የተሻለ ደረጃ የመድረስ ሕልምን ሰንቃ እንደምትሠራ ነው የተናገረችው::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here