“ሥርዓተ ትምህርታችን ዐይነ ስውራንን ያማከለ የማስተማር ሥነ ዘዴ የለውም”

0
223

በደቡብ ጎንድር ዞን ሙጃ ወረዳ ነው የተወለዱት፤ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በሰዴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል:: ከዘጠኝ እስከ 12 በስማዳ ወረዳ በሚገኘው ታገል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናቸውንም በማለፍ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ እና አካባቢ ጥበቃ ትምህርት ክፍልን ተቀላቅለዋል:: ከዚያም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡- አቶ አወቀ ጌትነት::

አቶ አወቀ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበሩበት ጊዜ የጀመሩትን የበጎ አድራጎት ተግባር እስከ አሁኑ ጊዜ ድረስም አስቀጥለዋል:: በእሳቸው ምክንያት እጣ ፋንታቸው ጎዳና ላይ ወይም ልመና ይሆን የነበሩ የዐይነ ስውራንን ሕይወት ቀይረዋል:: ከአቶ አወቀ ጋር የነበረን ቆይታ ተከታዩ ነው፤

መልካም ንባብ!

በጎነት ለእርስዎ ምን ማለት ነው?

በጎነት እንግዲህ በቃላት ዝም ብሎ የሚገለጽ አይመስለኝም:: በጎነት በተግባር የሚገለጽ ነው:: አንድ ሰው ፈጣሪ በሰጠው ጸጋ ማለትም በገንዘብ፣ በዕውቀት፣ በጉልበት ይሁን በሌላ ለሰዎች የሚጠቅም ነገር ላይ አስተዋጽኦ ማበርከት ነው ብዬ ነው በአጭሩ የምገልጸው:: በጎነትህ በተፈጥሮ ሊቸርህ ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ሀይማኖትህ፣ ማሕበረሰብህ ቤተሰብህ በጎ አንድትሆን በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ::

 

የበጎነት ተግባርን እንዴት ጀመሩት?

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስማር የግቢ ጉባዔ የሚባል አለ:: በግቢ ጉባዔ የተለያዩ በጎ ተግባራት ይከወናሉ:: በጊዜው ተማሪዎች ስለነበርን በገንዘብ ሳይሆን በጉልበት ነበር አብዛኛውን ድጋፍ የምናደርገው:: በዛ ምክንያት በተለያዩ አገልግሎቶች እሳተፍ ነበር:: ለምሳሌ እሁድ እሁድ ሆስፒታል እየሄዱ ህሙማንን መጠየቅ ሊሆን ይችላል፤ እንዲሁም አልጋ ላይ የወደቁ ህሙማንን ገላቸውን እና  ልብሳቸውን ማጠብ የመሳሰሉት ተግባራትን እንፈጽም ነበር::

ሦስተኛ ዓመት ስንሆን የልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፍ ለመሥራት ወደ ሠርጸ ድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይመጣሉ:: እኔም በአጋጣሚ አብሬ ሄጄ ነበር:: በወቅቱ ለዐይነ ስውራን ተማሪዎች የሚሆን ቁሳቁስም ሆነ የመማሪያ መጽሐፍ አልነበረም:: ልጆቹ እጅግ ሲቸገሩ ተመለከትኩ:: በዚያውም የመማሪያ መጽሐፍትን ለዐይነ ስውራን ተማሪዎች ማንበብ ጀመርኩ:: ልጆቹ የትምህርት አቀባበላቸው በጣም ፈጣን ነው፣ ስርዓት አላቸው፤ በዚህ ምክንያት እጅግ ተግባባን፤ ፍቅራቸውም ሳበኝ::

ትምህርት ከጨረሱ በኋላስ?

ትምህርት ጨርሼ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መኝታ ተቆጣጣሪ ሆኜ ተመደብኩ፤ ሥራው የሚከወነው በፈረቃ በመሆኑ ለልጆቹ ለማንበብ ትርፍ ጊዜ እንዳገኝ አስቻለኝ:: ቼሻየር አክሽን ፋውንዴሽን የተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት ቀደም ሲል የሻይ እየከፈለ ያስነብብላቸው ነበር:: ልጆቹ እኔን ካዩኝ ከወደዱኝ በኋላ ቼሻየር አክሽን  ፋውንዴሽን የታክሲ እየሰጠኝ ማንበብ ቀጥያለሁ::

ንባቡ እንዴት ይከወናል?

በቀድሞውም ሆነ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ዐይነ ስውራንን ያማከለ የመማሪያ መጽሐፍም ሆነ የማስተማር ስነ ዘዴ በስፋት የለም:: የብሬል(ዐይነ ስውራን ማንበቢያ) የተወሰኑ መጽሐፍት ያሉት እስከ ስድስተኛ ከፍል ብቻ ነው:: ይህን ታሳቢ በማድረግ ንባቡ ፕሮግራም ወጥቶለት የእነሱን የትምህርት ክፍለ ጊዜያቸውን በማይሻማ መልኩ ነው የሚደረገው፤ ንባቡ በስልክ ይቀረጻል፤ ወደ አማርኛ የሚተረጎመው ይተረጎማል፤ ማብራሪያ ይሰጣል:: በዚህ ሂደት ለሁለት ሰዓታት ሁለት የተለያዩ የትምህርት ዓይቶችን እንሸፍናለን:: እንደፈለጉ ጥያቄ ይጠይቃሉ፤ ውይይትም ይኖረናል:: ልጆቹ የተቀረጸውን ድምጽ ቤታቸው ሆነው ዐይናማው መጽሐፉን እንደሚያነበው እንደገና ማጥናት ይችላሉ፤ የቤት ሥራቸውን ይሠራሉ፤ ለፈተና ይዘጋጃሉ፤ ይህ የመማር  ማስተማር ሂደት ውጤት አይሰጥበትም እንዲሁም የቀረ ተማሪ አይቀጣበትም እንጂ ከመደበኛው ትምህርት የተለየ አይደለም::

የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ቁጥርን ጨምሮ ምልከታን የሚፈልጉ ትምህርቶችን ለመስጠት አስቸጋሪ ነው:: ቁጥሮችን ትተን ግን ምልከታ የሚያስፈልጋቸውን በመዳሰስ በማሳየት አስተምራቸዋለሁ:: ለምሳሌ በስነ ሕይወት ትምህርት የቅጠል ክፍሎችን ለማስተማር ቅጠሉን በእጅ እያስዳሰስኩ ምን ምን እንደሚባሉ እነግራቸዋልሁ ቢያደክምም ይይዙታል::

የማንበቢያ ክፍላችን ድምጽ ሲቀረጽ እንዳይበላሽ በጥንቃቄ የተዘጋጀ ነው:: ድምጹን ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎች ላሉ ዐይነ ስውራን ተማሪዎችም ያጋሩታል:: ለምሳሌ በደብረ ማርቆስ፣ ሞጣ፣ ደብረ ታቦር እና ሌሎች አካባቢዎች ተልኮላቸው ይጠቀሙበታል:: አንድን ዐይነ ስውር ተማሪ መንገድ ላይ እያደመጠ ያለውን ብትሰማው የእኔ ድምጽ ነው::

ድጋፍ ስላደረጉላቸው እና ጥሩ ደረጃ ስለደረሱ ተማሪዎች ይንገሩን?

በጣም ጎበዝ ልጆች ናቸው፤ እኔንም አስተምረውኛል:: የተማርኩት ጂኦግራፊ ነው፤ ነገር ግን የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርቶችን እንዳነብ አስችለውኛል:: ወደዚህ ማዕከል ከፋሲሎ፣ ጣና ሀይቅ፣ መሰናዶ እና ሌሎች ትምህርት ቤቶች ይመጣሉ:: በአጠቃላይ ከአራት እስከ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ነው ያሉት::

በውጤት ደረጃ በየክፍሉ ማየት ይቻላል፤ ደረጃውን የሚይዙት የምረዳቸው ልጆች ናቸው:: ሁሉም ማለት ይቻላል ከ90 በላይ አማካኝ ውጤት ያላቸው ናቸው:: በሌላ ከተማ የሚገኙ የእኔን ድምጽ አድምጠው የሚማሩ ጥሩ ውጤት እንደሚያመጡ ሰምቻለሁ::

ከዚህ ባሻገር ዩኒቨርሲቲ ገብተው ተመርቀው መምህር፣ የመንግሥት ሠራተኛ፣ የሕግ ባለሙያ የሆኑ ብዙ ናቸው:: ሠርጸ ድንግል ትምህርት ቤት እንኳ ሁለት መምህራን አሉ:: በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጥምረት የሚሰጥ ስኮላርሺፕ በየዓመቱ ቢያንስ አራት ዐይነ ስውራን ተማሪዎች ያገኛሉ::

ዐይናማ ተማሪዎችን እና ዐይነ ስውራንን እንዴት ይመዝኗቸዋል?

ዐይናማ ተማሪዎችን እንዲሁ እመለከታቸዋለሁ፤ 40 ደቂቃ በትዕግስት ለመቀመጥ እንኳ አይችሉም፤ ይቁነጠነጣሉ፤ ይነሳሉ፤ ይቀመጣሉ፤ መምህር ሲወጣ ተከትለው ይወጣሉ፤ በግቢው ይዞራሉ፤ ይህን ስል ሁሉን  ማለቴ አይደለም:: የትምህርት ፍላጎታቸውም በአብዛኛው የወረደ ነው:: አዲስ ነገር ለማወቅ ተነሳሽ አይደሉም::

ዐይነ ስውራን ግን ትዕግስተኞች ናቸው:: ጉዳቱ እንዳለ ሆኖ ጥሩ አዳማጭ እና የተረጋጉ ትዕግስተኞች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል:: እነሱ የሚመለከቱት በጆሯቸው ነው:: እያንዳንዷን ነገር ያደምጣሉ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ መሠረተ ልማት እና ሌሎች ችግሮች እንደሌላው ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ አያስችለቸውም፤ ስለሆነም የወደፊት ተስፋቸውን በትምህርት ላይ ስለሚጥሉት በታላቅ ፍላጎት እና ትኩረት ነው የሚከታተሉት:: በዚህ ምክንያት አጋዥ ካገኙ ውጤታማ ይሆናሉ:: በሥራው ዓለምም ሕዝባቸውን ያለ አድሎ፣ ያለ ስርቆት እና ቸልተኝነት ያገለግላሉ::

በበጎነት ምን አገኙበት?

ተማሪዎቹ የአኗኗራቸው ሁኔታ ያሳዝናል፤ አብዛኞቹ ከቤተሰብ ርቀው ነው የሚኖሩት፤ የዕለት ጉርሳቸውን እንኳ ተቸግረው ነው የሚያገኙት፤ ይሄን ሁሉ ዓመት አብሬያቸው ስቆይ የእነሱን ሕይወት እያየሁ እያዘንኩም እየተጽናናሁም ነው የቆየሁት:: ከዚህ ችግር ወጥተው ግን ደህና ነገር ላይ ሆነው ሳያቸው ክፍያዬ ይህ ነው::

በግል ሕይወቴ ግን ጎድቶኛል፤ በፊት ኑሮው እንዲህ ሳይከብድ፤ ደሞዜ ለሌላ ባትሆን ወር ከወር ሳልቸገር ለመድረስ ይሆን ነበር፤ ኮቪድ ከመጣ በኋላ ግን አስቸጋሪ ሆኗል፤ በትርፍ ሰዓቴ ሰርቼ ኑሮዬን እንዳልደጉም ለእነዚህ ልጆች የማደረገው ሊቆም ነው:: በአሁኑ ሰዓት የታክሲ ማውጣት እንኳ ከባድ ሆኗል፤ በዚህ ረገድ አቅም ያላቸው ሰዎች ቢያግዙ መልካም ነው እላለሁ::

የሚያመሰግኗቸው አካላት ካሉ

በመጀመሪያ ቤተሰቤን ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ሠርጸ ድንግል ትምህርት ቤት፣ ቼሻየር አክሽን ፋውንዴሽን፣ እንደ ግለሰብ እንዲሁም ጋሽ መሐመድ እና በስሩ ያሉ ሰዎችን አመሰግናለሁ::

ወደፊት በበጎ ተግባሩ ያሰቡት ነገር ካለ?

እውነቱን ለመናገር “በሬ በአንገቱ ነው በአንጀቱ የሚስብ” ይባላል፤ አሁን ባለበት ሁኔታ የሚያግዝ አካል ከሌለ ድጋፉን ለማስቀጠል ከባድ ነው:: ፈጣሪ አምላክ የሚያግዝ አካል ከሰጠኝ ለማስቀጠል ቁጥራቸውንም ለመጨመር ሀሳብ አለኝ:: ፈጣሪ እስከረዳኝ ድረስ የሚያግዘኝ የለም  ብዬ ልጆቹን በትኜ የመተው ሀሳብ ግን የለኝም::

እጅግ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here