“ሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ የሚባሉትን ትዕቢት፣ ስስት እና ፍቅረ ነዋይን ድል ማድረግ ያስፈልጋል”

0
505

በፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ የሆኑት መምህር ቃለ ጽድቅ አየነው  የዐብይ ጾምን በተመለከተ ለአሚኮ የሰጡትን ሰፋ ያለ መረጃ እንደሚከተለው አቅርበናል::

ጾም ምን እንደሆነ እስኪ ያብራሩልን?

ጾም ማለት የሕግ መጀመሪያ ነው:: የሕግ ፍጻሜው ፍቅር ከሆነ የሕግ መጀመሪያው ጾም ይሆናል ማለት ነው:: ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ ሳይውል ሳያድር በገዳመ ቆሮንጦስ የገባው ሥራውን በጾም ለመጀመር ነው:: ጾም ማለት ላልተወሰነ ጊዜ ከሚበላ ከሚጠጣ ነገር መከልከል መሆኑን ፍትሃ ነገሥቱ አንቀጽ 15 ላይ ተጽፏል:: ሰዎች ላልተወሰነ ጊዜ ከምግብ እና ከመጠጥ የሚከለከሉበት ጊዜ ነው ማለት ነው:: ጾም ለነገሮች ሁሉ መሠረት ነው::

ጾም ማለት ሰውነትን ከሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ መከልከል፣ ለሥጋ የሚመቸውን ነገር መተው  ነው:: ጌታችን መጾም ሳያስፈልገው የጾመው በጾም መሣሪያነት “ዲያቢሎስን ድል ታደርጋላችሁ” ሲለን ነው:: እርሱ ድል አድርጎታል፤ ካልጾሙ ካልጸለዩ ሰይጣንን ድል ማድረግ እንደማይቻል ጌታ አስተምሮናል:: ወደ እግዚአብሔር በጾም በጸሎት የተመለሱ ድኅነትን እንዳገኙ ሁሉ ያልተመለሱ ደግሞ ጠፍተዋል:: ለምሳሌ ሰብአ ሰዶም ገሞራ እንደ ነነዌ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ባለመመለሳቸዉ እሳት ከሰማይ ወርዶ አቃጥሎ አጥፍቷቸዋል:: ጾም ሥጋችንን ለነፍሳችን የምናስገዛበት፣ ከፈጣሪ ጋር የምንገናኝበት የጽድቅ መንገድ፣ ለሥጋ ጤንነትም ቢሆን አስፈላጊያችን ነዉ::

ስለ ጾም በቅዱስ መጽሐፍ የተጠቀሱ ጥቂት ታረኮችን ይንገሩን?

ጾም በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናየው በመጽሐፈ አስቴር ላይ ንግሥት አስቴር ዘመዶቿ የመስቀል ሞት ተፈርዶባቸው እያለ ወገኖቿ ከተፈረደባቸው ክፉ ፍርድ ለማዳን ባሰበች ጊዜ የወሰነችው መጾም ነው:: እሷ እና ደንገጡሮቿ ጾሙ:: በሃማ ምክንያት በወገኖቿ ላይ የታወጀው የሞት አዋጅ ተሻረ:: በሦስት ቀን ጾም ፈቃዷ ተፈጽሞላታል:: ስለዚህ ጾም በእኛ ሕይወት ላይ የታዘዘውን ክፉ ነገር በሙሉ ማስተካከያ ነው::

የነነዌ ሰዎችን ታሪክ ስንመለከት የጾምን ፋይዳ እናገኛለን:: የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔርን በመበደላቸው በነብዩ ዮናስ በኩል እንደሚጠፉ ትምቢት ተነገራቸው:: በዚህም ሕዝቡ ለሦስት ቀናት ጾሞ ንስሃ ስለገባ ሊደርስባቸው የነበረው መዓት ተገለበጠላቸው፤ ከ12 ሺህ በላይ የሚሆኑት የነነዌ ነዋሪዎች ምህረት ወረደላቸው::

እነ ዳንኤል በስደት ፋርስ ባቢሎን እያሉ እየበሉ እየጠጡ ትምህርት እንዲማሩ ተፈቀደ፤ የኮከብ ቆጠራ፣ አስማት መሥራት እና ህልም መፍታት በኮሌጁ ይማሩ ነበር:: ለሦስት ዓመታት ጥሬ እየበሉ ተማሩ፤ ከሌላው ይልቅ እነዚህ ናቸው በትምህርት በስለው የተገኙ:: ዓላማቸውን ያሳኩት በጥሬ የተማሩት ናቸው::

ቀለብ እየሰፈረ ያስተማራቸው ንጉሥ ህልም አየ:: ህልሙን ግን ማስታወስ አልቻለም፤ ጮማ እየቆረጡ ብርዝ እየጠጡ የተማሩትን ያየሁትን ህልም እወቁ እና ፍቱልኝ አላቸው:: እነሱም ማወቅና መፍታት አልቻሉም፤ በመሆኑም እንዲገደሉ ተወሰነባቸው፤ ዳንኤል ግን ለእኔ “ሦስት ቀን ስጡኝ እና ህልሙን አውቄ ልፍታ” አለ:: “ሦስት ቀን ምንድን ነው?” ሲባል “ከአምላኩ ጋር በጾም በጸሎት የሚነጋገርባት መሆኑን ተናገረ::

ዳንኤል ሦስት ቀናት ከአምላኩ ጋር በጾም በጸሎት ተነጋግሮ ንጉሡ ዓይቶ ያጠፋውን ህልም አውቆ ፈታው:: ስለዚህ በጾም የተማሩት ዳንኤል እና ሠለስቱ ደቂቅ ሌሎችን ከሞት አድነዋል:: ስለዚህ ጾም ሊደርስ የሚችልን አደጋ የሚቀለብስ ነው፤ በእኛ ላይ የታዘዙ የሥጋ መቅሰፍቶችን እና እያንዳንዳቸው ክፉ ነገሮችን እንዳይከሰቱ የሚያደርግም ነው፤ እንደ ሀገርም፣ እንደ ቤተሰብ እንዲሁም እንደ ግለሰብ ለችግሮች መፍትሔ መስጠት የሚችል እነደሆነ ከላይ ያየናቸው ምሳሌዎች ማስረጃ ናቸው:: መቅሰፍትን ከመቀልበስ በተጨማሪ ወደፊት የሚከሰቱ ጉዳዮችን ለመተንበይ እና እግዚአብሔር በህልም ያሳየን ምስጢር ለመፍታት ጾም ቁልፍ ነው::

የዐብይ ጾም ምንድን ነው?

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአዋጅ ከሚጾሙት ሰባቱ አጽዋማት አንዱ እና ትልቁ ዐብይ ጾም ይባላል:: ይህ ጾም ዐብይ ጾም፣ ጾመ ኢየሱስ፣ ጾመ ሁዳዴ እና 40 ጾም በመባል ይታወቃል:: ዐብይ ጾም መባሉ ታላቅ ጾም መሆኑን ለማሳወቅና አምላካችን ለሰዎች በመጀመሪያ አብነት ለመሆን የጾመዉ ስለሆነ እና በቁጥርም ከሌሎች አጽዋማት ከፍ ስለሚል ነዉ:: ጾመ ኢየሱስ መባሉ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጠቀሰ ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው በመሆኑ ጾመ ኢየሱስ ተብሏል::

ሁዳዴ ጾም መባሉ ደግሞ ሁዳድ ከሚለዉ ሲሆን ሁዳድ ማለት ሰፊ የእርሻ ቦታ ማለት ነው:: ዐብይ ጾምም የሥላሴን ልጅነት ያገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ ሰፊ እና ትልቅ ወደሆነዉ ካገኙት የማያጡት ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያደርስ ሁሉም ምዕመን የሚጾመዉ ጾም በመሆኑ አባቶቻችን ጾመ ሁዳዴ ብለዉ ሰይመዉታል::

ዐብይ ጾም ሦስት ክፍሎች እና ስምንት ሳምንታት አሉት:: ሦስቱ ክፍሎች የተባሉት ዘወረደ፣ የጌታ ጾም እና ሕማማት ናቸዉ:: ዘወረደ (ጾመ ሕርቃል) ጾሙ ከሚገባበት ሰኞ ጀምሮ እስከ እሁድ ድረስ ያለዉ ቀን ነዉ:: የጌታ ጾም ከቅድስት ሰኞ እስከ ሆሣእና ዋዜማ ዓርብ ድረስ ያለዉ 40 ቀን ነዉ:: ሕማማት ጌታችን በአልአዛር ቤት ለማዕድ ከተቀመጠበት የሆሣዕና ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ሥዑር ያለዉ መከራን የተቀበለበት ስምንት ቀን ሕማማት ነዉ::

ሕርቃል የአንድ ንጉሥ ስም ነው፤ ይህ ታላቅ ንጉሥ በመስቀል ጦርነት ጊዜ ለክርስቲያኖች ተዋግቶ የጌታችንን መስቀል ከአህዛብ እጅ ስላስመለሰ ለዚህ ውለታው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ከዘወረደ እስከ ቅድስት ያለው የፆም ክፍል በእርሱ ስም ተሰይሞ እንዲፆም ሊቃውንት ደንግገዋል። በተመሳሳይ በዓብይ ፆም ከሆሳዕና በኋላ ያለው የመጨረሻውን ሳምንት የጌታችን እና የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ መስቀል የምናስብበት ጊዜ ነው እና ሰሞነ ህማማት ተብሎ እንዲታወስ እና እንዲፆም አድርገዋል።

የዐብይ ጾም ሳምንታት ስያሜ እና ትርጓሜን  ያብራሩልን?

የመጀመሪያው ዘወረደ ይባላል፤ ትርጕሙ ‹ከሰማየ ሰማያት የወረደ› ማለት ነው:: ከሰማየ ሰማያት የወረደውን፣ ከድንግል ማርያም የተወለደውን በጥንት ስሙ ወልድ፣ ቃል በኋላ ስሙ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አማኑኤል የተባለውን ሰው የኾነውን አምላክ ለማመስገን ርደቱን (ከሰማየ ሰማያት መውረዱን) ለመዘከር የሚጾም ጾም ነው:: ጌታችን ጾመ ከማለት አስቀድሞ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም መወለዱን መናገር አስፈላጊ ነው እና የመጀመሪያው ሳምንት ‹ዘወረደ› ተብሏል::  “አንተ በሰማይ አለህ፤ በምድር በባሕርም በየብስም አለህ” የተባለውን በሰማይ በምድር ምሉዕ የሆነውን አምላክ “ወረደ፤ መጣ” ብሎ መናገር ሰው ሆነ” ማለት ነው:: ሰው ሆኖ መገለጡን ለማስረዳት ነው እንጂ መውረድ መውጣት የሚባሉ ቃላት በሁሉ ምሉዕ ለሆነው መለኮት አይስማሙትም:: ቃላቱ ሰውኛ አነጋገርን የሚያመለክቱ ናቸውና::

መተርጎማን አበው “ዘወረደ” ማለት “ሰው የሆነ” ማለት ነው” ብለው ይተረጉማሉ:: አምላካችን ሰው ከሆነ በኋላ “መጣ፤ ሔደ፤ ወረደ፤ ዐረገ” የሚሉ ቃላት ይስማሙታል:: ምልዓቱን ሳይለቅ በሰው አካል ተወስኖ ታይቷልና:: ስለዚህ “ወረደ” እግዚአብሔር ሰው ሆኖ መገለጡን፤ “ዐረገ” ደግሞ የሰውነቱን ሥራ መፈጸሙን ያሳያል:: ዐረገ ስንልም ቀድሞ በሰማይ የለም ለማለት አይደለም፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ በዓለሙ ሁሉ ምሉዕ ነውና::

ጾሙን ሐዋርያት፣ ስያሜውን እና የምስጋናውን ሥርዓት ቅዱስ ያሬድ አዘጋጅተዋል:: ቅዱስ ያሬድ ነቢያትን በንባብ፤ ሐዋርያትን በስብከት፤ ሊቃውንትን በትርጓሜ፤ መላእክትን በዜማ ይመስላቸዋል:: ቅዱስ ያሬድ የመላእክትን የምስጋና ሥርዓት ወደ ምድር አምጥቷል:: የነቢያትን ትንቢት፣ የሐዋርያትን ትምህርት በሚገባ ተርጉሞ፣ አብራርቶ እና አመሥጥሮ አዘጋጅቶታል:: ሐዋርያት ጾሙን ጾመው የጾም ሕግ ደንግገዋል፤ ቅዱስ ያሬድም ለጾሙ ስያሜ ሰጥቶ ምስጋና ከነሥርዓቱ አዘጋጅቶ አቅርቧል::

ቤተ ክርስቲያናችን የመጀመሪያው የዐቢይ ጾም ሳምንትን (ዘወረደን) ስያሜ እንደ ቅዱስ ያሬድ ከሐዋርያት ተቀብላ ታስተምራለች:: ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ‹ጾመ ሕርቃል› እየተባለም ይጠራል:: ሕርቃል (ኤራቅሊዮስ) በ614 ዓ.ም የነበረ የቤዛንታይን ንጉሥ ነው:: ለክርስቲያኖች ባደረገው ርዳታ ምክንያት አንድ ሳምንት ጾመውለት ነበር:: ያላወቁ ‹ጾመ ሕርቃል› ብለው አንድ ጊዜ ጾመው ትተውታል:: ጥንቱን የቅዱሳን ሐዋርያት መሆኑን ያወቁ ምእመናን ግን ሁልጊዜ በየዓመቱ ይጾሙት ነበር:: ዛሬም ድረስ ጾመ ሕርቃል እየተባለ ይጠራል:: ሙሉ ታሪኩ በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ አንቀጽ  15 ላይ ይገኛል::

ሁለተኛው ቅድስት ይባላል፤ “ቅድስት” ማለት “የተለየች፣ የነጻች፣ የከበረች” ማለት ነው:: ይኸውም ጌታችን ጾም የጀመረባት፣ ልዩ፤ የተቀደሰች፤ የከበረች፤ ልዩ፣ ንጹሕ፣ ክቡር በሚሆን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጾመች መሆኗን ያመላክታል:: ይህች ጾም በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አራት የተገለጠችው የጌታችን ጾም ናት፣ ስያሜዋ እና የዕለቷ የምስጋና ሥርዓትም የቅዱስ ያሬድ ነው::

አምላካችን በገዳመ ቆሮንጦስ አርባ መዓልት እና 40 ሌሊት በጾመበት ጊዜያት እነዚህ ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ ድል አድርጓል:: ሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ የሚባሉትም፡- ትዕቢት፣ ስስት እና ፍቅረ ነዋይ ናቸው:: በእነዚህ ሦስት ኃጢአቶች ጌታችን በዲያሎስ በተፈተነ ጊዜ በትዕቢት ቢመጣበት በትሕትና፣ በስስት ቢመጣበት በትዕግሥት፣ በፍቅረ ነዋይ ቢመጣባት በጸሊዓ ነዋይ ጌታችን ዲያቢሎስን ድል አድርጎታል:: ለእኛም እነዚህን ድል ለማድረግ የምንችልበትን ጥበብ ጾምን ገልጦልናል:: ትዕቢት ያልተሰጠንን መሻት፣ ስስት አልጠግብ ባይነት ስግብግብ መሆን፣ ፍቅረ ነዋይ ለገንዘብ ሲሉ ፈጣሪን መካድ ነው:: አንደ ክርስቲያን ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ ድል ካደረገ ሌሎችን ኃጣውእ በቀላሉ ድል ማድረግ ይቻለዋል::

ይቀጥላል

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here