በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚያተኩረው 30ኛው የዓለም ሀገራት ጉባኤ (ኮፕ 30) በቤለም ብራዚል ከሰሞኑ ተካሂዷል:: ለ15 ቀናት በቆየው ስብስባ የዓለም ሀገራት መሪዎች፣ ተደራዳሪዎች እና የዘርፉ ተሟጋቾች (አክቲቪስቶች) የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቅረፍ በድጋሚ ቃል ገብተዋል:: ኮፕ እ.አ.አ በ1992 የፀደቀ የባለብዙ ወገን ስምምነት ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስር የተመሠረተ ነው።
ኮፕ ሁሉም ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ የጋራ ተግዳሮት ላይ በጋራ የሚሠሩበት ብቸኛው ዓለም አቀፍ መድረክ ነው:: ይህም ቀጣይነት ያለው ዓለም አቀፋዊ ትኩረትን እና ተጠያቂነትን ያረጋግጣል::
የተባበሩት መንግሥታት ደርጅት ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያስገነዝበው የኮፕ አስተናጋጅ ሀገር በመደበኛነት በተባበሩት መንግሥታት ክልላዊ ቡድኖች (አፍሪካ፣ እስያ – ፓሲፊክ፣ ምሥራቅ አውሮፓ፣ ላቲን አሜሪካ፣ ካሪቢያን እና ምዕራባዊ አውሮፓ) መካከል በየዓመቱ ይሽከረከራል:: የየክልሉ ቡድን አባላት የትኛው ሀገር ጉባኤውን እንደሚያዘጋጅ ይወስናሉ።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት የሚደረገው ይህ ዓመታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተልዕኮው በአየር ንብረት ሥርዓት ላይ ያልተገባ (አደገኛ) ጣልቃገብነትን መከላከል ነው:: በየዓመቱም የዓለም ማሕበረሰብ አየር ንብረት ላይ ያለውን ዕድገት ለመገምገም፣ አዳዲስ ግቦችን ለማውጣት እና ዓለም አቀፍ የበካይ ጋዞችን (የግሪን ጋዝ) ልቀቶችን ለመቀነስ በተቀናጁ ተግባራት ላይ ተወያይቶ ስምምነት ላይ ይደርሳል:: በአየር ንብረት ላይ የሚወጡ ዓለም አቀፍ ፖሊሲዎችም የሚቀረጹበት መድረክም ነው::
ኮፕ የፓሪሱን ስምምነት (እ.አ.አ 2015) የዓለም ሙቀት መጨመርን በተቻለ መጠን ከቅድመ – ኢንዱስትሪ ደረጃ ወደ አንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሺየስ የመገደብ ዓላማን እና መንግሥታት ለዚህ ዕቅድ መሳካት የሚያደርጉትን ሥራ እና ዓለም አቀፍ ጥረቶችን የሚገመግሙበት ነው። ተሰብሳቢዎቹ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖዎችን ለመከላከል የሚያስችላቸውን ውሳኔዎች ያስተላልፋሉ::
በጎርፍ፣ ድርቅ እና ሌሎች የአየር ንብረት አደጋዎች ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍንም ይመለከታል:: ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን አረንጓዴ ለማድረግ እና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን (ፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የአቅም ግንባታ) መገንባት ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። ይሁንና የአየር ንብረት ተቆርቋሪ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በኋላ ጉባኤው የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመገደብ የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን እና የርምጃ ፍጥነት ማስገኘት አልቻለም ብለው ይተቹታል:: ግስጋሴው ቀርፋፋ ቢሆንም ባለፉት ዓመታት በተደረጉ ጉባኤዎች ለዓለም አቀፍ ትብብር እና አስገዳጅ ቃል ኪዳኖች የጋራ ግንዛቤ መሠረት ጥሏል።
ምንም እንኳ የለውጡ ፍጥነት ከፈተናው ስፋት ጋር ባለመጣጣም ብዙ ሥራዎች ቢቀሩም ኮፕ የዓለምን የአየር ንብረት አጀንዳ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል:: የኪዮቶ ፕሮቶኮል (እ.አ.አ በ1997) እና የፓሪሱ ስምምነት (እ.አ.አ 2015) የኮፕ ጉባኤ ውጤቶች መሆናቸውን ልብ ይሏል::
እንደሚታወቀው የኪዮቶ ፕሮቶኮል እ.አ.አ በ1997 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ (UNFCCC) ሲሆን በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት በካይ ጋዞች (የግሪን ሀውስ ጋዝ) ልቀትን ለመቀነስ ቃል የገቡበት ነው። በዚህ ፕሮቶኮል በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራት በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ በካይ ልቀት ቅነሳ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸዋል።
የኪዮቶ ፕሮቶኮል ያደጉ ሀገራት እ.አ.አ ከ1990 እስከ 2012 በአማካይ በአምስት በመቶ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ ቁርጠኞች መሆናቸውን የሚያሳዩበት ነበር:: ይሁንና የተፈለገውን ውጤት ባለማስገኘቱ ፕሮቶኮሉ እ.አ.አ 2015 በጸደቀው በፓሪሱ ስምምነት ተተክቷል::
በተጨማሪም የኮፕ ስብሰባ ማሕበረሰቦችን እና ስነ-ምህዳሮች የአየር ንብረት ለውጥ የማይቀር ተፅዕኖዎችን እንዲለማመዱ ለመርዳት ዓለም አቀፍ ጥረቶችን እንዲያራምዱ ያግዛል:: ጉባኤው ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤን ያሳድጋል፣ መንግሥታትን፣ የንግድ ድርጅቶችን እና የሲቪል ማሕበረሰቡን በማሰባሰብ በተግባራዊ የአየር ንብረት መፍትሔዎች እና ፈጠራዎች ላይ ትብብርን ያበረታታል።
በኮፕ የሚደረጉ ውሳኔዎች ታዳሽ ኃይልን፣ የኢነርጂ ቆጣቢነትን እና ሌሎች ዘላቂ አሠራሮችን በማስተዋወቅ ነጋዴዎች እና ባለሀብቶች ዝቅተኛ ካርቦንን ወደሚጠይቅ ኢኮኖሚ እንዲገቡ የሚደረገውን ሽግግር በማፋጠን ይረዳል::
የኮፕ ምዕራፎች ጉልህ ቢሆኑም፣ ብዙ የአየር ንብረት ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች የአየር ንብረት ሁኔታው አሳሳቢ እና አልፎ ተርፎም ከባድ እንደሆነ ያስጠነቅቃሉ። ከዓለም አቀፉ የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት፣ ናሳ እና አይፒሲሲ የተገኙ ሳይንሳዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአየር ንብረት ለውጥ ባለፉት 30 ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱን ያሳያሉ።
እ.አ.አ በ2024 የዓለም አማካይ የሙቀት መጠን ከአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ ከሆነ (በፊት ከነበረው በላይ) በርካታ ወራትን አስቆጥሯል:: እ.አ.አ ከ1990ዎቹ መግቢያ ጀምሮ የባሕር ከፍታ በሰባት ነጥብ ስድስት ሴንቲሜትር ገደማ ከፍ ብሏል:: የሳተላይት መለኪያዎች ከተጀመሩ ወዲህ የከፍታው መጠን በእጥፍ ጨምሯል:: ሙቀት፣ ጎርፍ እና አውሎ ነፋሶች ተደጋጋሚ እና ኃይለኛ እየሆኑ መጥተዋል:: በግብርና፣ ጤና እና መሠረተ ልማት ላይ አስከፊ ተጽዕኖዎችንም እያደረሱ ነው። በከባቢ አየር ውስጥ ያለው የሙቀት አማቂ ጋዞች (CO2፣ ሚቴን እና ናይትረስ ኦክሳይድ) ከበርካታ ሺህ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ::
ከጦርነቶች እስከ የንግድ አለመግባባቶች ድረስ ዓለም አቀፋዊ ትብብር ውጥረት ውስጥ ነው። አሜሪካ ከፓሪሱ ስምምነት መውጣቷ የአየር ንብረት ቀውሱ አንድነትን እና ምኞትን በሚጠይቅበት ጊዜ አስገዳጅ የአየር ንብረት ግዴታዎችን ለማውጣት አስቸጋሪ አድርጎታል::
የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ሥራ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያደረሰ ይገኛል:: የሙቀት መጠን መጨመር፣ የዝናብ መጠን መዘበራረቅ (ከፍተኛ እና ዝቅተኛ የዝናብ መጠን መኖር) እንደ ድርቅ፣ ጎርፍ እና አውሎ ነፋሶችን በመፍጠር ጉዳት እያስከተለ ነው። የጎርፍ ድግግሞሽ እና የጎርፍ መጠን መጨመር ሰብሎችን ይጎዳል:: ድርቅ ደግሞ ሰብልን በማውደም የአካባቢ ሙቀትም እንዲጨምር ያደርጋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በእንስሳት፣ በአፈር ለምነት እና በመስኖ ውኃ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን ያሳድራል:: የባሕር ከፍታ እንዲጨምር በማድረግ ጨዋማ ውኃ እንዲኖር እንዲሁም የተባዮችን እና በሽታዎችን ስርጭት ያመጣል::
የአየር ንብረት ለውጥ የረጅም ጊዜ የሙቀት ለውጦችን እና የአየር ሁኔታን ይመለከታል። የአየር ንብረት ለውጥ በፀሐይ እንቅስቃሴ ወይም በትላልቅ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች ምክንያት ሲከሰት ለውጦቹ ተፈጥሯዊ ሊሆኑ ይችላሉ:: ነገር ግን እ.አ.አ ከ1800ዎቹ ጀምሮ የሰው ልጅ እንቅስቃሴ የአየር ንብረት ለውጥ ዋና አንቀሳቃሽ ሆኖ ቆይቷል:: በዋናነት እንደ ከሰል፣ ነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ያሉ ነገሮችን ለማውጣት የሚቃጠለው ቅሪተ አካል ካባቢ አየርን ይበክላል::
ነዳጅን ለማውጣት የሚቃጠለው ቅሪተ አካል የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀቶችን ይጨምራሉ፤ የፀሐይን ሙቀት አምቆ በመያዝም የሙቀት መጠንን ይጨምራሉ። የደን መጨፍጨፍ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠንን መጨመርን ያስከትላል:: ነዳጅ ዘይት እና ጋዝ የሚቴን ልቀት መጨመር ዋና ምንጮች ናቸው:: ኢነርጂ፣ ኢንዱስትሪ፣ ትራንስፖርት፣ ሕንፃዎች፣ ግብርና እና የመሬት አጠቃቀም በካይ ጋዞችን ከሚያስከትሉ ዋና ዋና ዘርፎች መካከል ናቸው::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ ኮፕ COP 32ን ለማስተናገድ ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል:: ስብሰባው በ2027 (እ.አ.አ) በአዲስ አበባ ይካሄዳል:: በብራዚል ቤሌም ከተማ በተካሄደው የ2025ቱ የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ ኮፕ 32 ጠንካራ እና ትርጉም ያለው ውጤት እንዲያስመዘግብ እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የጋራ እርምጃዎችን ለመውሰድ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደምትሠራ አሳውቃለች::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሕዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


