የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም
የእስራኤል – ሀማስ ጦርነት ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል። ጦርነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ አድማሱን አስፍቶ መካከለኛው ምሥራቅን እያመሰ ይገኛል። የሀማስ እና እስራኤል ጦርነትን ተከትሎ ሊባኖስ፣ ኢራን እና የየመኑ ሀውቲ አማጺያን በጦርነቱ እየተሳተፉ ነው። ጦርነቱ መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶችን አስከትሏል፤ እያሰከተለም ነው።
በጋዛ የተገደሉትን ከ44 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ ባለው ጦርነት ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በእስራኤል በኩል ደግሞ ከአንድ ሺህ 800 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል። ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል። 100 ሺህ የሚጠጉ እስራኤላውያንም በተመሳሳይ በጦርነቱ ሳቢያ ተፈናቅለዋል።
ከጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስራኤል የሰብአዊ እና የንግድ የምግብ አቅርቦት ወደ ደቡብ ጋዛ እንዳይገባ ካገደች በኋላ በጋዛ ውስጥ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ተደቅኗል። በሰሜን ጋዛ ግዛትም ቢሆን በጃባሊያ፣ ቤት ሆነን እና በቤተ ላህያን አካባቢዎች የምግብ አቅርቦቶች መገደቡን መረጃዎች አመልክተዋል። ይህም በረሃብ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ሮይተርስ ዘግቧል።
በቅርቡ ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች መዘረፋቸውን የዘገበው ደግሞ አልጀዚራ ነው። ከ109 የጭነት መኪኖች መካከል 98ቱ መዘረፋቸውን እና መጎዳታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል። በዚህ ምክንያት እየተባባሰ የመጣው የምግብ እጥረት በአፋጣኝ መፍትሔ ካልተሰጠው አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ህይወታቸው አደጋ ላይ ይወድቃል።
የጭነት መኪኖችን ዘረፋ እና ውድመት የሰማው ሀማስም በመግለጫ ድርጊቱን ተቃውሞታል። መሰል ወንጀል ሲፈጽም የተገኘ ማንኛውም ሰው ብርቱ ቅጣት ይጠብቀዋል ብሏል። እስራኤል በበኩሏ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች እርዳታ እንዲያገኙ እንደምታደርግ አሳውቃለች። በሌላ በኩል እስራኤል በጋዛ ለሚገኙ ንጹሀን ከለላ ካልሰጠች እና ወደ ቦታው እርዳታ እንዲገባ ካልፈቀደች የጦር መሣሪያ አቅርቦቱን እንደሚያዘገየው አሜሪካ አስታውቃለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በሰሜን ጋዛ ላይ የምታደርገውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች። እስራኤል ሰሜናዊውን የጋዛ ክፍልን መቆጣጠሯን ሮይተርስ ይፋ አድርጓል::የእስራኤል የፋይናንስ ሚኒስቴር ቤዛሌል ስሞትሪች ሀማስ ያገታቸውን እስራኤላውያንን ለማስለቀቅ ሙሉ በሙሉ የጋዛን ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል እንቆጣጠራለን ብለዋል። “ታጋቾች ወደ ቤታቸው ካልተመለሱ ለዘላለም እዚያ እንድምንቆይ ሊያውቁ ይገባል” ሲሉ የፋይናንስ ሚኒስቴሩ ተደምጠዋል።
ይህ ደግሞ የጋዛን አንድ ሦስተኛ ሕዝብ ዋጋ ያስከፍላል። ሀማስ እጅ እስከሚሰጥ እና እስኪወገድ ስምምነት የሚባል ነገር እንደሌለም ጠቁመዋል። “ከሀማስ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ማለት እጅ መስጠት እና መሸነፍ ማለት ነው” ብለዋል የገንዘብ ሚኒስቴሩ ቤዛሌል ስሞትሪች። እናም እስራኤል በሰሜን ጋዛ እየሰነዘረች ያለችውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።
በግዛቱ በሆስፒታል ላይ ባደረገችው ጥቃት የሕክምና አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙት ተቋማት ውስጥ አንዱ የሆነው የካሚል አድዋን ጉዳት ደርሶበታል። “እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየሠራን ነው። 45 የሕክምና ባለሙያዎች በእስራኤል ወታደሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል። መዳን የሚችሉ ሕሙማንንም በየቀኑ እያጣናቸው ነው” ሲሉ የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ሆሳም አቡ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ (OCHA) ጋዛ ውስጥ አሁንም ከ75 ሺህ እስከ 95 ሺህ ሰዎች እንዳሉ ይገምታል። አካባቢው አሁን ድረስ በእስራኤል ወታደሮች እየተደበደበ ሲሆን ከጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከአንድ ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ህይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል። ብዙ ፍልስጤማውያን በየዕለቱ ጥቃት እየደረሰባቸው እና ሰብዓዊ እርዳታ የሚሹ ቢሆንም ሰሜናዊ ጋዛን ለመልቀቅ ግን ፈቃደኞች አይደሉም ነው የተባለው። አንዳንዶች አካባቢውን ለቀው ከወጡ በእስራኤል ወታደሮች ጥቃት ሊደርስብን ይችላል ብለው ይሰጋሉ።
አሜሪካ፣ ኳታር እና ግብጽ እስራኤል እና ሀማስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ብዙ ጥረቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸው አይዘነጋም። ይሁን እንጂ ኳታር ሀማስ እና እስራኤል ፈቃደኝነት እና ቁርጠኝነት እስከሚያሳዩ ድረስ በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ታጋቾች እንዲለቀቁ ስታደርግ የነበረውን የማሸማገል ጥረት ማቆሟን ባለፈው ሳምንት መግለጿ ይታወሳል።
ኳታር ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ከግብጽ እና ከአሜሪካ ጋር በመሆን ለረጅም ጊዜ ያደረጉት አደራዳሪነት ምንም ውጤት አለማምጣቱን ተከትሎ ነው። ሀማስ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ጠቅልሎ እንዲወጣ መፈለጉ እና እስራኤል የጋዛን የጸጥታ ሁኔታ በዘላቂነት ለመቆጣጠር ያላት ፍለጎት ለድርድሩ አለመሳካት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል።
ኳታር ሀማስን እና እስራኤልን ለማሸማገል ያደረገችው ጥረት ፉርሽ ከሆነ በኋላ የሀማስ ከፍተኛ አመራሮች ኳታርን ለቀው ወደ ቱርክ አምርተዋል ሲል አንድ የአረብ ዲፕሎማት ለእስራኤል ታይምስ መናገሩ ተዘግቧል ። የቱርክ ዲፕሎማት ምንጮች ግን የሀማስ መሪዎች ሀገራቸውን ከመጎብኘት ውጪ በቱርክ የመኖር ፍላጎት እንደሌላቸው አሳውቀዋል ነው የተባለው። አሜሪካ የሀማስ መሪዎች የትም ቦታ ተመቻችተው መቀመጥ እንደሌለባቸው በማመን ቱርክ የሀማስ መሪዎችን እንዳታስጠጋ ማስጠንቀቋን አልጀዚራ ዘግቧል።
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ግን አሜሪካ ያቀረበችውን ረቂቅ የተኩስ አቁም ሃሳብ መቀበሉ መረጃዎች ወጥተዋል። በአሜሪካ የቀረበው የድርድር ሀሳብ ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ነው ተብሏል። ንጹሀንን ለመጠበቅ እና ወደ መኖሪያ ቀያቸው ለመመለስ ታስቦ ነው የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ የታሰበው። በሂደት ደግሞ ጦርነቱን ለማስቆም ዕቅድ ተይዟል። የተኩስ አቁም ስምምነቱ የ2006ቱን የእስራኤል እና ሄዝቦላህ ጦርነት ባስቆመው የመንግሥታቱ ድርጅት የውሳኔ ሃሳብ 1701 ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ተጠይቋል።
የውሳኔ ሃሳቡ ሄዝቦላህ ከእስራኤል ሰሜናዊ ድንበር በ20 ኪሎሜትሮች እንዲርቅ የሚጠይቅ ነው። በእስራኤል በኩል እስካሁን የተባለ ነገር ባይኖርም የሌባኖስ ጠቅላይ ሚኒስቴር ናጂቢ ማካቲ ምላሻቸው አወንታዊ መሆኑ ተገልጿል። ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደምትቀበለው ቢነገርም የእስራኤል ጄቶች በቤሩት እና አካባቢው የሚፈጽሙትን ድብደባ አላቆሙም። የሄዝቦላህ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መሀመድ አፊፍ እስራኤል በማዕከላዊ ቤይሩት ባደረገችው ጥቃት መገደሉ የሚታወስ ነው። ሄዝቦላህም ወደ እስራኤል ሮኬቶችን መተኮሱን ቀጥሏል።
የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ተጨማሪ አራት ሰዎች ሲሞቱ 14 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ብሏል። በሌላ በኩል የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር መርሀ ግብር በከፊል መምታቷን መናገራቸው አይዘነጋም። አሜሪካ ግን እስራኤል በኢራን የኒውክሌር መርሀ ግብር ላይ ጥቃት እንድትፈጽም እንደማትፈቅድ ተገልጿል። ይሁን እንጂ ኔታኒያሁ የኒውክሌር መርሀ ግብሩን ሙሉ በሙሉ የማውደም ዕቅድ እንዳላቸው ተናግሯል።፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም