ረቂቅ በጀቱ አንድ ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ ቀረበ

0
66

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል:: በዚህ ወቅት የ2018 ዓ.ም ረቂቅ በጀት ተዋውቋል::

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ ረቂቅ በጀቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡ ሲሆን አንድ ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ይሆናል ተብሏል:: ከዚህ ውስጥ አንድ ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን ብር የሚጠጋው ለመደበኛ ወጪ እንደሚውል ተመላክቷል:: 415 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ለካፒታል ወጪ ይመደባል ተብሎ ታሳቢ የተደረገ ነው:: 315 ቢሊዮን ብሩ ለክልል መንግሥታት ድጋፍ እንዲውል ሲደረግ 14 ቢሊዮን ብር ለክልሎች የዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ድጋፍ የሚውል ነው ተብሏል::

ከገንዘብ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ከረቂቅ በጀቱ ውስጥ 73 በመቶ ወይም አንድ ትሪሊዮን ብር የሚሆነው ከታክስ ገቢ የሚሰበሰብ ነው:: 236 ቢሊዮን ብር ከልማት አጋሮች፣ ቀሪው ደግሞ ከፕሮጀክቶች ድጋፍ እና ከልዩ ልዩ ገቢዎች ለማግኘት መታቀዱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ አስታውቀዋል::

በረቂቅ በጀቱ ከጥቅል ሀገራዊ ምርት አንፃር ያልተጣራ የበጀት ጉድለት ሁለት ነጥብ ሁለት በመቶ እንዲሁም የተጣራ የበጀት ጉድለት አንድ በመቶ መሆኑም ተመላክቷል::

የበጀት ጉድለቱን በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ እንደሚሸፍን አቶ አህመድ አስታውቀዋል::

ጥብቅ የገንዘብ እና የበጀት ፖሊሲን በመከተል የመንግሥት ወጪን በሀገራዊ ገቢ ለመሸፈን ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል። ይህም የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እና ውጤታማ የበጀት አጠቃቀምን ለመተግበር የሚያስችል እንደሆነ ተመላክቷል::

የ2018 ረቂቅ በጀት የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን እና የ10 ዓመቱን መሪ የልማት ዕቅድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል:: በአዲሱ ዓመት የስምንት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚጠበቅ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል::

ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ24 በመቶ ከፍ ብሎ የቀረበው ረቂቅ በጀት ለተጨማሪ ዝርዝር ዕይታ ወደ ፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here