ራሱን የለወጠ ተቋም ይቀይራል

0
20

የፍትሕ ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ እና የዳኝነት ነፃነትን የሚፈትኑ ተግዳሮቶችን በማስወገድ ፍርድ ቤቶች ገለልተኛ ሆነው የሚሠሩበትን መንገድ ለማጠናከር ባለፉት 10 ቀናት በአማራ ክልል ለሚገኙ  የፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች፣ ዳኞች እና የጉባኤ ተሚዎች  የመጀመሪያ የሆነው ሥልጠና ተሰጥቷል:: ሰልጣኞች በቆይታቸው በዘርፉ ዕውቀት ያላቸው ምሁራን የሕይዎት ልምዳቸውን፣ ዕውቀታቸውን…አጋርተዋቸዋል::

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቸርነት ተገኘ ከስልጠናው ተሳታፊዎች አንዱ ናቸው:: ፕሬዝዳንቱ ሥልጠናው በሀገሪቱ በወጡ ሕጐች እና ስትራቲጂዎች፣ በክልላዊ ሕጐች፣ በእሳቢዎች እና በፓሊሲዎች ዙሪያ   በዳኝነቱ ሥራ የተሻለ ለማገልገል የሚያስችል ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው  ገልፀውልናል:: የተገልጋይ እርካታን  ከፍ ለማድግ፣ በትምህርት ያገኙትን እውቀት ለመፈተሽ እንዲሁም በግል ሕይወታቸው የተሻለ ሥብዕናን ለመገንባት የሚያስችል እንደነበርም አክለዋል::

ዳኝነትን መሠረት አድርገው ሕግን የሚተርጉሙ አካላት በተገቢው መንገድ የወጡ መመሪያዎችን እና ሕጎችን በመረዳት ሕዝብን መሰረት አድርገው የሚወጡ መሆኑንም መገንዘብ እንዲቻል ያደረገ እና ግንዛቤ እንዲኖር ያስቻለ ስልጠና መሆኑን ፕሬዝዳንት ቸርነት  መስክረዋል::

በሌላ በኩል ራስን መለወጥ፣ ተቋምን ለመለወጥ የሚረዳ በመሆኑ ስልጠናው ምሁራን  በየዘርፉ ልምዳቸውን በማካፈል ሃሳብ የሚቀርብበት ስለነበር ሕዝቡን በአግባቡ እንዲያገለግል አቅም የሚፈጥር እንደበርም  ነው ያነሱት::

በቀጣይ 5  እና 25  ዓመታት የክልሉን ፍርድ ቤቶች የት ማድረስ ነው የታሰበው? ለሚለው   ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ተመልክቶ የሚፈለገውን የጋራ ራእይ እና የተቋም አንድነት  ክልሉ የጋራ ዕቅድ እንዲይዝ የተሻለ አቅም የፈጠረ  መድረክ እንደሆነ ነው አቶ ቸርነት ያነሱት:: በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ አሁን የተጀመረው ፍርድ ቤቶችን የማዘመን (አዲስ ቴክኖሎጅ)ሥራ  ደግሞ በርካታ ባለጉዳዮች  አገልግሎትን ያለምንም እንግልት ማግኘት የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል::

የደቡብ ወሎ ዞኖ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ትዕግስት ዳኛቸው በበኩላቸው ስልጠናው የፍርድ ቤቶችን የአሠራር  ክፍተቶች የሚሞላ እንደሆነ ገልጸዋል። ዳኞች ያሉበትን ደረጃ የሚያሳይ፣ በአሠራር ሂደት የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት፣ በጋራ ለመሥራት እና ራዕዩን ከግብ የሚያደርስ ፍርድ ቤት ለመገንባት ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮች የተንሸራሸሩበት እንደሆነም ነው ወ/ሮ ትእግስት የገለፁት።

የዳኝነት አካላት የሚዳኙት እና የሚያገለግሉት ሕዝብን ነው፤ ሕዝብ የሚገለገልበት ሕግ ዳኞችን ይመለከታል፤ ዳኞች ከትምህርት ቤት ይዘውት ከወጡት ዕውቀት በተጨማሪ የሚወጡ አዳዲስ ሕጎችን ለማወቅ እና ለመተርጎም ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው በሥልጠናው ተገንዝበዋል።   አዳዳስ መመሪያ እና ደንቦችን በአግባቡ ለመረዳት እና ወደ ሥራ ለመተርጎም የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።

ሌላኛው ተሳታፊ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አሊ መሐመድ ደግሞ በሥልጠናው  ዳኞችን እና የጉባኤ ተሿሚዎችን በሙሉ ያካተተ እና ለጋራ ሥራ እና ለውጥ የሚያነሳሳ እንደሆነ ጠቁመዋል::መድረኩ  የበለጠ መተባበር፣ በጋራ መሥራት እና የጋራ ራዕይ ያላቸው ዳኞችን ለመፍጠርም ያስቻለ ነው ብለዋል።

ሕዝቡ ”ፍትሕ የሚሰጥ ፍርድ ቤት አለ” ብሎ አመኔታ እንዲኖረው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዲጂታል አሠራርን መዘርጋቱ ለለውጡ ማሳያ ነው:: በዞን ደረጃም ባለው አቅም ሁሉ ዘመናዊ አሠራሮችን ለመገንባት እየተሠራ ነው፤ ይሁን እንጅ አብዛኛው የፍርድ ቤት ተገልጋይ በወረዳዎች ስለሚገኝ ቴክኖሎጂው እስከታች እንዲወርድ በጋራ መሠራት እንደሚገባ ጠይቀዋል::

ሌላው የባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መጽደቁን በአዎንታ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ባሕል፣ እሴት እና ታሪክን አክብረው የሚሠሩ፤ በሕዝቡ ዘንድ ግጭቶችን የሚፈቱ ፣ አንድነትን የሚገነቡ፣ እንደ ዘመናዊ ፍርድ ቤት አሸናፊ እና ተሸናፊ የሌለበት በመሆናቸው የመደበኛው ፍርድ ቤቶችን ሥራ አይቶ በመፍታት በብዙ መንገድ እንደ ሚያቀሉ አብራርተዋል::

ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ለዚህ ዝግጅት እንደ ጀመረ ያነሱት አቶ አሊ፤ በባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የሚያገለግሉ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተመርጠው የቀደመ ልምዳቸውን የሚያዳብር ሥልጠና መውሰዳቸውንም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅን ያቀረቡት የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሃናን አበበ በበኩላቸው መንግሥት ባሕልን የማሳደግ እና የመጠበቅ ኃላፊነት ስለተሰጠው ግዴታውንም ጭምር ለመወጣት የባሕል ፍርድ ቤቶች ማቋቋማቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው አሳውቀዋል::

ጉዳያቸው በባሕል ፍርድ ቤቶች እንዲታዩላቸው የሚፈልጉ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመኖራቸው ደግሞ  ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ተደራሽ በመሆናቸው ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ሕግ መንግሥታዊ እና ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ መቀረጽ ስላለባቸው በአዋጅ መቋቋማቸውን ነው የተናገሩት።

የባሕል ፍርድ ቤቶች ሲመሠረቱ መርሆዎች እንዳሏቸው የተናገሩት ወይዘሪት ሃናን፤ እነዚህም በፈቃድ ላይ የተመሠረተ መሆን፤ ባሕላዊ ሥርዓትን ማስጠበቅ፣ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ መሆን እና የሰብዓዊ መብትን ማክበር መናቸው።

የባሕላዊ ፍርድ ቤት ሽማግሌዎች ሥነ ምግባር ያላቸው፣ አድሎ የሌለባቸው፣ በጥቅም የማይሠሩ፣ ምስጢር የሚጠብቁ፣ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ተሳታፊ አለመሆን ዋና ዋና መመዘኛዎቹ ናቸው::

የባሕል ፍርድ ቤቶች በሕዝብ ግልጽ በሆነ ቦታ ላይ የሚካሄዱ መሆናቸውን የጠቆሙት ወይዘሪት ሃናን፤  ዜጎች በእርቅ እንዲስማሙ፣ አብረው እንዲኖሩ እና ቂም እንዲሽር የማድረግ አቅማቸው ከፍ ያለ መሆናቸውንም አመላክተዋል።

የአዋጁን አፈጻጸም እንዲከታተል ለክልሉ ምክር ቤት ተጠሪ የሆነ እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠብሣቢነት የሚመራ የባሕላዊ ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት መቋቋሙንም ወይዘሪት ሃናን አንስተዋል::  ምክር ቤቱ የባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን ሥራ እንደሚከታተልም ተናግረዋል::

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ፍርድ ቤቶች የሰላም፣ የመረጋጋት እና እንደ ሃገር ፀንቶ የመኖር ምልክቶች እንደሆኑ ተናግረዋል:: ሥልጠናው የፍትሕ ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ እና የዳኝነት ነፃነትን የሚፈትኑ ተግዳሮቶችን በማስወገድ ፍርድ ቤቶች ገለልተኛ ሆነው የሚሠሩበትን መንገድ ለማጠናከር የሚያስችል እንደሆነም ነው የጠቆሙት::

አቶ ዓለምአንተ እንዳሉት በቀጣይ  የለውጥ ሥራውን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዲቻል ዘመናዊ አሠራር እና ሥነ ምግባር ግንባታ ላይ መሥራት ይገባል:: ምክንያቱ ደግሞ  በጥቂት ሥነ ምግባር ችግር ባለባቸው ዳኞች የፍርድ ቤቶች ሥም እንዳይነሳ መከታተል እና ርምጃ መውሰድ፣ የዳኝነት አገልግሎቱን እና የዳኞችን የውሣኔ አቅም ማጎልበት እንዲሁም ለባሕል ፍርድ ቤቶች ዕውቅና  በመሥጠት ወደ ሥራ የማስገባት ተግባሮች ይሠራሉ:: ተገልጋዩ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በፍርድ ቤቶች /ፍትሕ ተቋማት/ እምነት ኖሮት ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ዳኞች ከሥብዕና ግንባታ ጀምሮ ተገቢውን አቅም መገንባት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል::

 

የሕግ አንቀጽ

የአማራ ክልል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ የፍርድ ቤቶች ሚና

የአስተዳደር ተቋማት መመሪያ አወጣጥ እና ውሳኔ አሰጣጥ ሥነ- ሥርዓት እንዲሁም በሚሰጡ ውሳኔዎች እና በሚወጡ መመሪያዎች ላይ ቅር የተሰኘ ወገን የመመሪያዎችን ወይም የውሳኔዎችን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት የሚታረምበትን ሥርዓት በመደንገግ አስተዳደራዊ ፍትሕን ለማስፈን የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን ምክንያት በማድረግ የአማራ ክልል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ አዋጅ ቁጥር 292/2017 እንዲወጣ ተደርጓል፡፡

  • አቤቱታ የማቅረብ መብት

የአስተዳደር ተቋማት የሚያወጡትን መመሪያ አስመልክቶ ማንኛውም ሰው መመሪያው እንዲከለስ አቤቱታውን ለፍርድ ቤት የማቅረብ መብት አለው፡፡

የአስተዳደር አካላት የሚሰጡትን ውሳኔ በተመለከተ በውሳኔው ጥቅሙ የተነካበት ሰው ብቻ ውሳኔ እንዲከለስ አቤቱታውን ለፍርድ ቤት የማቅረብ መብት ይኖረዋል፡፡

  • አቤቱታ የሚቀርብበት ፍርድ ቤት

ለቅሬታ ምክንያት የሆነው የአስተዳደር ውሳኔ የተሰጠው በዞን እና ከዞን በታች ባሉ የአስተዳደር ተቋማት ከሆነ ለክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚቀርብ ይሆናል፡፡

  • በቢሮ እና በቢሮ ደረጃ ባሉ የአስተዳደር ተቋማት የተሰጠ ውሳኔ እንዲሁም የአስተዳደር መመሪያ እንዲከለስ የሚቀርብ አቤቱታን የማየት ሥልጣን የተሰጠው ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡

ምንጭ- አብክመ ጠ/ፍ/ቤት

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here