ራስን የመሆን ድፍረት

0
22

የአፕል ኩባንያ መስራች የነበረው ስቲቭ ጆብስ እ.አ.አ. በ2011 በካንሰር በሽታ ምክንያት ሲሞት 56 ዓመቱ ነበር:: “ጊዜህ የተገደበ ነው፤ ስለዚህ የሌላ ሰው ሕይወት በመኖር አታባክነው” በሚል አነጋገሩ ይታወቃል:: ስቲቭ እንዳለውም ሞት ቶሎ መጣበት:: በዓለም ከሚታወቁ ቀዳሚ ኩባንያዎች አንዱ አፕልን መመስረት የቻለው በራሱ መንገድ ለመጓዝ በመድፈሩ እና በመትጋቱ ነበር:: ዛሬ እሱ አፈር ሆኗል:: አሻራው ግን  በትውልድ ውስጥ ዘላለም ይቀጥላል::

የሰው ልጆች አንዱ ከሌላው ጋር የመኖር ኡደት ብዙ ውስብስብ ፈተናዎች እና ጥሩ እድሎች ያሉት ነው:: የራሳችንን የመኖር ፍላጎቶች፤ በዙሪያችን ካሉት ሰዎች ተጽእኖዎች እና ግምቶች ጋር የማስታረቅ ፈተናን ማለፍ ከባዱ ርምጃ ነው:: እንደ ሰው ብንችል ነፃ እና ያልተገደበ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት አለን:: ነገር ግን በጥልቅ ውስጥ የተተከለ ከሰዎች ጋር የመኖር እና የመደነቅ ፍላጎትም አለን::

እነዚህ ፍላጎቶች በሚጋጩበት ጊዜ የራሳችንን ግቦች እና ህልሞች ከመከታተል ይልቅ የሌሎችን ግቦች እና ህልሞች በማሳደድ፤ የሌላን ሰው ሕይወት መኖር ልንመርጥ እንችላለን:: ብዙ ሰዎች በወላጆቻቸው፣ በአስተማሪዎች፣ በአሰልጣኞች፣ በአማካሪዎች ወይም በእኩዮቻቸው ፍላጎቶች ተጽዕኖ ይደረግባቸዋል:: ለምሳሌ ጠበቃ ሁን፣ አማካሪ ሁን፣ ዶክተር ሁን፣ የቤተሰብ ንግዱን ምራ፣ ብዙ ደመወዝ የሚከፍልህን ሥራ ምረጥ፣ ስራህን ቀይር በሚል መምከር እና ጫና ማሳደር የተለመደ ነው:: የምንመክረው ሰው ማን እንደሆነ እና ምን እንደሚፈልግ ሳናውቅ ጫና እንፈጥራለን:: ሰዎችም እንዲሁ ይጫኑናል:: ለእናቴ ስል ነው፣ ለአባቴ ብየ ነው፣ ለጓደኛየ ደስ ይበላት ብየ ነው፣ ለሰው ብየ ነው የሚሉ ንግግሮችን ከሰዎች መስማታችን ለዚህ ነው::

ብዙዎች የራሳቸው ባልሆነ አኗኗር ታስረዋል:: ሰዎች የሌላ ሰው ሕይወት በመኖር ጉልበታቸውን የሚያባክኑበት ምክንያት ውስብስብ ነው:: በአብዛኛው ከሥነ ልቦናዊ ፍላጎት፣ ማህበራዊ ተፅእኖ እና የግል ደኅንነት ፍርሃት የመነጨ ነው:: የመጀመሪያው ምክንያት የይሁንታ እና ተቀባይነት ማግኘት ፍላጎት ነው:: ከልጅነት ጀምሮ ሕፃናት የወላጆቻቸውን ፍቅር እና ይሁንታ ለማግኘት የተገሩ ሆነው ያድጋሉ:: ይህ ልማድ አድጎ  የማስደሰት በሽታ ይሆናል:: ለሰው ደስታ ስንል የምንሰዋ እንሆናለን::

ለምሳሌ ወላጆች  ልጃቸውን የህግ ባለሙያ ማድረግ ሊፈልጉ ይችላሉ:: ልጃቸው  የወላጆቹን ፍላጎት ስለሚያሳካ ይቀበሉታል፤ ይወዱታል፤ ይሸልሙታል:: የራሱን ፍላጎት ቢከተል ደግሞ የወላጆችን ፍቅር ሊያጣ ነው:: ይህ ደግሞ ተቀባይነት ማጣትን እንዲጋፈጥ ያደርገዋል:: ይህ ፍርሃት የራሱን መሻት ከመምረጥ ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት መኖር እንዲቀናው አድርጎ ያሳድገዋል:: በኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ብራድ ቡሽማን “አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን እንደ የራሳቸው ሕይወት ማራዘሚያ  አድርገው ያያሉ፤ የራሳቸው ተስፋ እና ህልም  እንዳላቸው አይገነዘቡም” ይላሉ::

የማኅበራዊ ቡድን ተቀባይነት  ጫናውም የሚዘነጋ አይደለም:: ሰዎች የራሳቸውን ማኅበራዊ ደረጃ ሀብት ወይም ስኬት በማኅበራዊ ቡድናቸው ውስጥ ካሉት ሰዎች ጋር ያወዳድራሉ:: ይህ ደግሞ በቡድኑ ዘንድ የተከበሩ ግቦችን (ለምሳሌ የቅንጦት መኪና መግዛት፣ ትልቅ ኩባንያ ውስጥ መሥራት) ለማሳካት ጉልበት እንዲያባክኑ ያደርጋል::

ሁለተኛ የፍርሃት እና የመተማመን ስሜት ማጣት ነው:: የራስን መንገድ መከተል አደጋን እና በሌሎች አለመተማመንን ስለሚጠይቅ ሰዎች ወደ ተሞከረና ወደተፈተነ የሌላ ሰው መንገድ ይሸሻሉ:: አዲስ መንገድ አስፈሪ ነው::

የራስን ህልም መከተል ሲታሰብ የመውደቅና መነሳት ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ በግለሰቡ ላይ ይወድቃል:: የሌላ ሰው መንገድ (ወይም የወላጅ መመሪያ) መከተል ግን ውድቀት ሲመጣ የሚወቀስ አካል እንዲኖር ያስችላል። ባይሳካልን አባቴ እኮ ነው ብለን ለማሳበብ አንቸገርም::

ራስን አለመቻል ግለሰቡ የራሱን ፍላጎት ወይም ምርጫዎች ለመወሰን በቂ ጥበብ ወይም ብቃት እንደሌለው ሲሰማው የሚያደርገው ነው:: በዚህም  ሌላ ሰው የመረጠለትን ወይም የጠቆመውን መንገድ መከተል ይቀለዋል:: ይህ የፍርሀት ምርጫዎችን እንዲወስን ያደርገዋል::

ሦስተኛው የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ እና የንፅፅር ወጥመድ ነው:: በዘመናችን የማኅበራዊ ሚዲያ ለጉልበት ብክነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል:: ሰዎች የሐሰት ስኬትን እንደ እድገት እና አኗኗር መስፈርት ያሳያሉ:: ማኅበራዊ ሚዲያ የሰዎችን ሕይወት የሚያሳየው በጥንቃቄ በተዘጋጀና በተመረጠ መንገድ ነው:: ሰዎች የሌሎችን የውጫዊ ስኬቶች (ቅንጦት፣ ገንዘብ፣ ጉዞ) ሲያዩ የራሳቸው ሕይወት ጉድለት ያለበት መስሎ ይታያቸዋል:: ይህ ውጫዊውን መስፈርት ለማሟላት የራሳቸውን ውስጣዊ ፍላጎት ችላ ብለው ጉልበታቸውን እንዲያባክኑ ያደርጋቸዋል:: የሚያዩት ሁሉ እውነት ይመስላቸዋል:: ተስፋ መቁረጥ እና ቅዠት ውስጥ ይገባሉ::

ሌላ ሰውን የመሆን ግፊት ውስጥ ይገባሉ:: ሚዲያው እና ማስታወቂያዎች ደስተኛ ለመሆን ምን መግዛት ወይም ምን ዓይነት ሕይወት መኖር እንዳለብን የማያቋርጥ ምክር ይሰጣሉ:: ይህ የሌላ ሰው የጥሩ ሕይወት ራዕይ እንድንከተል ያስገድደናል:: ከያዝነው ይልቅ የምንይዘውን የተሻለ ነገር በማሰብ ደስታ እናጣለን::

አራተኛው ምክንያት የውስጣዊ ማንነት ግልጽነት ማጣት ነው:: ብዙ ጊዜ ሰዎች የሌላ ሰው ሕይወት የሚኖሩት የራሳቸውን ውስጣዊ አቅም ስለማያውቁ ነው። ግለሰቡ ዓላማውን፣ ዋና እሴቶቹንና ፍላጎቱን ለመለየት ጊዜ ካላጠፋ የሌሎች ግቦችና ሕልሞች በቀላሉ ቦታውን ይይዙበታል:: ግልጽ የሕይወት መስመር ከሌለን ሰዎች ወደ ሞከሩት ቀላል መስመር እናዘነብላለን::

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ልምድ ዑደት ይፈጥራል:: በልጅነት የወላጆችን ፍላጎት መከተል ሽልማት ስለነበረ ይህ ልማድ በአዋቂነት ጊዜም ይቀጥላል:: እንዴት? መኖር እንዳለብን በራሳችን ከመወሰን ይልቅ ሌሎች ለእኛ  እንዲወስኑ ማድረግ ቀላል ይሆናል::

ራስን የመሆን ጉዞ ድፍረት የሚጠይቅ ነው:: ብዙዎቻችን የሕይወታችንን የመጀመሪያ አጋማሽ የምናሳልፈው በሌሎች ሰዎች ፍላጎት በተገነባ እስር ቤት ወይም ሳጥን ውስጥ ነው። ይህ ሳጥን በቤተሰብ ግፊት፣ በባህል እና ሰው ምን ይለኛል በሚል ፍርሃት የተገነባ ነው። ከዚህ ሳጥን እንዴት መውጣት ይቻላል?

የራስን ሕይወት መምራት ማለት ራስ ወዳድ መሆን ማለት አይደለም:: ይልቁንስ እውነተኛ ማንነትን መግለጽ እንጂ:: በሌሎች ሰዎች ተውኔት ውስጥ ተዋናይ ከመሆን ወጥቶ ለራስህ የሕይወት ተውኔት ደራሲ ወደ መሆን የሚደረግ ጉዞ ነው::

ብሮኒ ዌር በሞት አልጋ ላይ ያሉ ሰዎችን የምትንከባከብ ነርስ ነበረች::ይህን ትዝብቷን ብሮኒ ዌር ዘ ቶፕ ፋይቭ ሪግሬትስ ኦፍ ዘ ዳይንግ (በሞት አፋፍ ላይ ያሉ ሰዎች አምስት ዋና ዋና ቁጭቶች) በሚል ርእስ መጽሐፍ አዘጋጅታዋለች:: ታካሚዎቿ ከመሞታቸው በፊት የሚናገሩትን የመጨረሻ ሃሳቦች ስትመዘግብ ብዙዎቹ የሚቆጩት በገንዘብ ማጣት ወይም ባለመዝናናት አልነበረም:: ትልቁ ቁጭት “ሰዎች ከእኔ እንደሚጠብቁት ሳይሆን ለራሴ እውነተኛ የሆነ ሕይወትን ለመኖር ድፍረት በኖረኝ እመኝ ነበር” የሚል ነው::

የቁጭት ምርመራ ማድረግ የሚለው ዋና ሐሳብ ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ጥሩ ዘዴ ነው:: ራሳችንን አሁን በ80 ዓመት ዕድሜያችን ላይ እንዳለን እናስብ:: አሁን ባለንበት መንገድ ከቀጠልን (በማንወደው ስራ፣ በማይመቸን ግንኙነት ወይም ሃሳባችንን በማፈን ብንቀጥል) ወደፊት ይቆጨናል? በርግጠኝነት መልሳችን አዎ ነው:: አሁን የምናልፈው የለውጥ ህመም ወደፊት ከሚመጣው የቁጭት ህመም ያነሰ መሆኑን አሜን ብለን ተቀብለን መኖር ነው ያለብን::

ተቀባይነት ከማግኘት ይልቅ እውነተኛነትን መምረጥ የተሻለው ነገር ነው:: ጋቦር ማቴ  ዘ ማይዝ ኦፍ ኖርማል በሚለው መጽሐፉ ራሳችንን መሆን ለምን ይከብደናል? ብሎ ይጠይቃል:: እናም ጋቦር ማቴ  ልጆች ሳለን ሁለት ፍላጎቶች ነበሩን ይላል:: ከሌሎች ጋር መተሳሰር እና እውነተኛነት:: አንድ ልጅ እውነተኛ ማንነቱን በማሳየት እና በወላጆቹ በመወደድ መካከል ምርጫ ሲቀርብለት ለመትረፍ ሲል ሁልጊዜ “መወደድን” ይመርጣል:: ይህንን ልማድ ወደ አዋቂነት ዕድሜያችን ይዘነው እንመጣለን፤ ሰዎችን ለማስደሰት ስንል ማንነታችንን እንጨቁናለን:: የራስን ሕይወት ለመኖር ይህንን የልጅነት ልማድ መስበር አለብን:: እውነተኛ ማንነትን ለማግኘት ስንል ከሰዎች ጋር ያለንን መተሳሰር ለጊዜውም ቢሆን ለመሠዋት ፈቃደኛ መሆን ይኖርብናል::

አይሆንም ማለት ስንጀምር ወይም መንገዳችንን ስንቀይር  ሰዎች ይከፋሉ:: ይህ የሆነው እኛ ስህተት ስለሠራን ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የነበረብንን “ሰዎችን የማስደሰት” ውል እያፈረስን ስለሆነ ነው::

የእኛን ድርሻ እና የእነሱን ድርሻ መለየት አለብን:: ዘ ከሬጅ ቱ ቢ ዲስላይክድ የሚለው መጽሐፍ በኪሺሚ እና ኮጋ የተዘጋጀ ነው:: የሥራ ድርሻን  ስለ መለየት ያትታል:: አብዛኛው ጭንቀታችን የሚመጣው በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ወይም እነሱ በኛ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡ በመፍቀድ ነው::

የእኛ ድርሻ ከእሴቶቻችን ጋር የሚስማማ ሕይወት መኖር ነው:: የሌሎች ድርሻ እኛ በምንኖረው ሕይወት ምን እንደሚሰማቸው መወሰን ነው:: ወላጆቻችን  ወይም ጓደኞቻችን በመረጥነው የሥራ መስክ ወይም ሕይወት ካዘኑ ይህ የእነሱ ድርሻ ነው እንጂ የእኛ አይደለም:: የሌሎችን ስሜት መቆጣጠር አንችልም:: የሰዎችን ስሜት ለመጠበቅ መሞከር ባሪያ ያደርገናል:: ለራሳችን ትክክል የሆነውን እናድርግ፤ ሰዎች ለራሳቸው ስሜት ራሳቸው ኃላፊነት ይውሰዱ::

ፈላስፋው ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን ራስን መቻል በሚለው መጽሐፉ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ማንም ሌላ ሰው የሌለው ልዩ እይታ አለ ይላል:: ሌሎችን መምሰል ራስን እንደማጥፋት ነው:: ኤመርሰን እንደሚለው የራሳችንን እውቀት ንቀን የሌሎችን እንድናደንቅ ተምረናል:: የራሳችንን ሃሳብ የእኛ ስለሆነ ብቻ እንንቀዋለን:: ነገር ግን ያንኑ ሃሳብ አንድ ታዋቂ ሰው ሲናገረው እናደንቃለን::

ስለዚህም በራስ ፈለግ ለመኖር ውሳኔዎችን ለሌሎች አሳልፎ መስጠት መቆም ያለበት ነው:: ችግር ሲገጥመን ምክር ከመጠየቃችን በፊት ለ24 ሰዓታት ራሳችን ለመፍታት መሞከር አለብን::ይህ ልምምድ ውስጣዊ አቅማችን እንዲበራ ያደርገዋል:: ለራሳችን ያለንን ግምት እንድናሳድግ ያግዘናል::

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የህዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here