ጁሊያኖ ሲሞኒ ይባላል፡፡ ከአባቱ ዲያጎ ሲሞኒ እና ከእናቱ ካሮሊና ባልዲኒ በኢጣሊያዋ ላዚዮ ከተማ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2013 ተወልዷል፡፡
ጁሊያኖ አሁን ላይ ዕድሜው 22 ሲሆን በጣሊያኗ ላዚዮ ከተማ ለመወለዱ ምክንያት የሆነው አባቱ ዲያጎ ሲሞኒ በወቅቱ ለጣሊያኑ ክለብ ለላዚዮ ይጫወት ስለነበረ ነው፡፡
ጁሊያኖ ሲሞኒ ገና የስምንት ዓመት ወጣት እያለ አባቱ ዲያጎ ሲሞኒ የስፔኑን ክለብ አትሌቲኮ ማድሪድን እንዲያሠለጥን ዕድል ተሰጠው፡፡ ትንሹ ጁሊያኖም የአባቱን ወደ አትሌቲኮ ማድሪድ መሄድ ወሬ ሲሰማ “እነ ራዳሜል ፋልካኦን ልታሠለጥን ነው?“ ሲል ጠየቀው፡፡ ኮሎምቢያዊው ራዳሜል ፋልካኦ በወቅቱ በስፔን ላሊጋ ለአትሌቲኮ ማድሪድ ድንቅ እንቅስቀሴ በማድረጉ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ዓለም ላይ ከነበሩት የፊት መስመር ተጨዋቾች በግብ አስቆጣሪነቱ የሚታወቅም ነበር፡፡
የትንሹ ጁሊያኖ ሲሞኒ ጥያቄ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ “አትሌቲኮ ማድሪድ የምትሄደው እነ ሊዮኔል ሜሲን እና ክርስቲያኖ ሮናልዶን በተቃራኒነት ልትገጥም ነው?“ በማለትም ለአባቱ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
አባትም “አዎ ልጄ“ ሲል መልሶለታል፡፡
ትንሹ ጁሊያኖ ሲሞኒ በወቅቱ አትሌቲኮ ማድሪድን ለማሠልጠን ዕድል ላገኘው ለአባቱ ዲያጎ ሲሞኒ የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ማብቂያ ያላቸው አልመሰሉም፡፡ “አባዬ፣ በአትሌቲኮ ማድሪድ አሠልጣኝነትህ ጥሩ ነገሮችን ከሠራህ እኮ ከኛ ጋር ተለያይተህ ልትቀር ነው አይደል?“ የሚል ሌላ ጥያቄ አስከተለ፡፡
አባት ዲያጎ ሲሞኒ ለዚህኛው የልጁ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከራሱ ጋር ብዙ መምከር አስፈልጎታል፡፡ ወደ አትሌቲኮ ማድሪድ ለሥራ በሚሄድበት ወቅት ልጆቹን እና ባለቤቱን አርጀንቲና ውስጥ ጥሎ መሄዱ የግድ ነበር፤ በተለይ የትንሹን ልጁን የጁሊያኖን ዕድገት በቅርብ ሆኖ መከታተል ያለመቻሉ ጉዳይ ለዲያጎ ሲሞኒ ቅሬታ ፈጥሮበታል፡፡
የእንጀራ ነገር ሆኖበት ቤተሰቡን ትቶ አትሌቲኮ ማድሪድን ለማሠልጠን ወደ ማድሪድ ከተማ ያቀናው ዲያጎ ሲሞኒ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቤተሰቡን ወደ ማድሪድ ከተማ በመውሰድ ኑሯቸውን በአንድ ላይ ማድረግ ችለዋል፡፡
የትንሹ ጁሊያኖ ራስን ፍለጋ የሚጀምረውም ከዚህ በኋላ ነው፡፡ አባቱ የሚያሠለጥነውን አትሌቲኮ ማድሪድ ጨዋታዎች ሲኖሩት ከአባቱ ጋር ወደ ሜዳ እየገባ ጨዋታዎችን ይመለከታል፤ ጨዋታዎችን መመልከት ብቻም ሳይሆን በስታዲየሙ ውስጥ ኳስ በመመለስ ከኳስ ጋር ያለውን ቅርበት አሳድጓል፡፡
ዲያጎ ሲሞኒ ልጁን ጁሊያኖ ሲሞኒን በአትሌቲኮ ማድሪድ ዋንዳ ሜትሮ ፖሊታኖ ስታዲየም ለደጋፊዎቹ አቅፎ ሲያስተዋውቀው የወደፊቱ የአትሌቲኮ ማድሪድ ተስፈኛ ተጨዋች ይሆናል በሚል አልነበረም፤ እንደውም አባት ልጁን የእግር ኳስ ተጨዋች ይሆናል የሚል ግምትም አልነበረውም፡፡ የሆነው ግን ያልታሰበው ነው፡፡
ትንሹ ጁሊያኖ ሲሞኒ ታላላቅ ወንድሞቹ ጆቫኒ እና ጂያንሉካ ሲሞኒ ታዋቂ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ ጂዮቫኒ ሲሞኒ ከክለብ ተጨዋችነቱ በተጨማሪ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን መለያን በመልበስ ጭምር እንደ ሊዮኔል ሜሲ ካሉ ታዋቂ አርጀንቲናዊያን ጋር በእግር ኳሱ መድረክ መሰለፍ የቻለ ነው፡፡
አባቱ ዲያጎ ሲሞኒ የእግር ኳስ ተጨዋች እና አሠልጣኝ እንዲሁም ታላላቅ ወንድሞቹም በእግር ኳሱ መድረክ የሚታወቁት ጁሊያኖ ሲሞኒ በአትሌቲኮ ማድሪድ ከኳስ አቀባይነት በመነሳት ራሱን ወደ ትልቅ ተጨዋችነት ለመቀየር በርካታ ውጣ ውረዶችን ዓይቷል፡፡ በአርጀንቲናው ሪቨር ፕሌት አካዳሚ የሙከራ ጊዜን ከማሳለፍ አንስቶ ለስፔኖቹ ሪያል ዛራጎዛ እና ለአላቬስ ክለቦች በውሰት በመጫወት ራሱን ሲፈልግ ቆይቷል፡፡
የቀድሞው የአትሌቲኮ ማድሪድ፣ ቪያሪያል፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ኢንተር ሚላን አጥቂ የነበረው ኡራጓዊው ዲያጎ ፎርላን “ዲያጎ ሲሞኒ በተጨዋችነት ዘመኑም ሆነ በአሠልጣኝነቱ ጊዜ የሚገባውን ክብር አግኝቷል ብዬ አላስብም፤ ልጆቹም ምርጥ ችሎታ ያላቸው ተጨዋቾች ናቸው፤ በተለይ ትንሹ ጁሊያኖ ሲሞኒ አሁንላይ በአትሌቲኮ ማድሪድ የመሰለፍ ዕድል ያገኘው የአሠልጣኙ ልጅ ስለሆነ ሳይሆን በብቃቱ ነው“ ሲል የጁሊያኖን ክህሎት አወድሷል፡፡
ጁሊያኖ ሲሞኒ አሁን በአትሌቲኮ ማድሪድ እና በአባቱ አሠልጣኝነት ሥር ከመጫወቱ በፊት ለዛራጎዛ እና ለአላቬስ ክለቦች በውሰት ውል ተጫውቷል፡፡ ጁሊያኖ ለአትሌቲኮ ማድሪድ ዋናው ቡድን ላስፓልማስን 2 ለ 0 ባሸነፉበት ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ባሳለፍነው የጥር ወር ደግሞ ክለቡ አትሌቲኮ ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊግ ከሜዳው ውጪ አርቢ ዛልዝበርግን 4 ለ 1 ሲያሸንፍ አንድ ግብ በማስቆጠር እና አንድ ግብ የሆነ ኳስ በማቀበል ሚናውን ተወጥቷል፡፡
ከጂዮቫኒ ሲሞኒ በመቀጠል ለአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ሁለተኛው የዲያጎ ሲሞኒ ልጅ መሆን የቻለው ጁሊያኖ ሲሞኒ ለብሔራዊ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወተው አርጀንቲና ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከፔሩ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ነው፡፡
ዲያጎ ሲሞኒ ገና በሕጻንነቱ አቅፎ ለአትሌቲኮ ማድሪድ ደጋፊዎች ያስተዋወቀው ጁሊያኖ ሲሞኒ አሁን በእግር ኳስ ክህሎቱ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ደጋፊዎችም በተጨማሪ ለአርጀንቲናዊያን ደጋፊዎችም የደስታ ምንጭ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡ አርጀንቲና እና ብራዚል ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ባደረጉት ጨዋታ አርጀንቲና ብራዚልን 4 ለ 1 ስታሸንፍ የ22 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ጁሊያኖ ሲሞኒ አንድ ድንቅ ግብ በብራዚሎች መረብ ላይ በማሳረፍ የግብ አካውንቱን አንድ ብሎ ጀምሯል፡፡
በርካታ ከዋክብትን በማፍራት በምትታወቀው አርጀንቲና ውስጥ የብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ ማድረግ እና የላቲን ደርቢ በሚባለው የብራዚል እና የአርጀንቲና ጨዋታ ተሰልፎ ግብ ማስቆጠር ብዙዎች ተመኝተውት ያልተሳካላቸው ጉዳይ ነው፡፡ ጁሊያኖ ግን ከብዙ ጥረት እና ትጋት በኋላ ራሱን በአርጀንቲናዎች የከዋክብት ስብስብ ውስጥ አግኝቷል፡፡ በቀጣይ ይሄ ወጣት አርጀንቲናዊ በእግር ኳሱ ምን እንደሚያሳየን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም