ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም
ኢትዮጵያዊያን የራሳችን መለያ የሆኑ የአለባበስ ባህል ያለን ሕዝቦች ነን:: ይሄው አለባበሳችን በዓለም አደባባይም “እኚህ ኢትዮጵያዊያን ናቸው” የሚያስብለን እንደሆነም አያጠራጥርም:: የጽሑፌ ማጠንጠኛ የኢትዮጵያዊያን አለባበስ ስለሆነ እንጂ እኛ ኢትዮጵያዊያን በፀጉር ስሪታችንም ቢሆን ለየት ያልን እንደሆነ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ እችላለሁ::
ሹሩባን ለዓለም ሕዝብ ያስተዋወቅነው እኛ ሳንሆን አንቀርም የሚል ግምቱም አለኝ፤ የቀደሙ ነገሥታቶቻችን ሹሩባዎች ከፀጉር ስሪት ጋር በተያያዘ ቀደምት እንደነበርንም ምስክሮች ናቸው:: ለነገሩ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሰው ዘር መገኛነታችን አንስቶ፣ በሕንፃ ሥራዎችም ሆነ በሌሎች ነገሮቻችን ከዓለም ቀዳሚዎቹ ሕዝቦች እንደበርን ታሪክ በድርሳኑ መዝግቦልናል::
አሁን ወደተነሳሁበት ነገረ አለባበሳችን ልመለስ፤ በኢትዮጵያችን ገጠር አከባቢዎች በእረኞች የሚለበሱት ቁምጣዎች የማጣት ወይም የኋላ ቀርነት ምልክት ሆነው፣ በነጮቹ ሲለበሱ ደግሞ የስልጣኔ ምልክት ተደርገው እንደሚወሰዱ ስንቶቻችን ልብ ብለናል? ለሠርግ አለባበሶቻችን፣ ለነ በርኖስ፣ ለነ ካባ እና መሰል ልብሶቻችንስ ስንቶቻችን ክብር ሰጥተናቸዋል?
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ መስተንግዶ ላይ ለሚሠሩ ዜጎቻችን የአለባበስ መመሪያ ሊያወጣ መሆኑን ስሰማ በጣሙን ነው ደስ ያለኝ:: ከተማ አስተዳዳሩን ለዚህ መመሪያ እና ደንብ ያበቃው (በእኔ እሳቤ) የሴት እህቶቻችን ቅጥ ያጣ ወይም መረን የለቀቀ አለባበስ ይመስለኛል:: በእርግጥ የሴቶቹ ልብስ የሚሠራው በአሰሪዎቻቸው ፍላጐት ላይ ተመስርቶ በመሆኑ ልጆቹን በደፈናው መውቀስ አይቻል ይሆናል::የወንዶቹ አለባበስም ቢሆን ከኢትዮጵያዊነት እሴት ያፈነገጠ ከሆነ በመመሪያ መታከሙ አይከፋም::
“ነውር” የሚለው ቃል ከኢትዮጵያዊያን መዝገበ ቃላት ላይ የተወገደ ይመስል የብዙ ሴት እህቶቻችን አለባበስ ለእርቃንነት የተቃረበ ነውረኛ አለባበስ መሆኑን ማስተዋል ከጀመርን ሰነባብተናል:: “መብት” የሚለው ቃል ያለቦታው እየተደነቀረ እህቶቻችን በአደባባይ ገላቸውን እያሳዩ መሄዳቸውን እንደ መብታቸው ቁጠሩላቸው የሚሉንም በዝተዋል::
እንደ ሀመር ባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ እርቃን መሆንን እንደማናነውረው ሁሉ በትላልቅ ከተሞች ውስጥ ገላቸውን ለብዙዎች ዐይን አጋልጠው የሚሄዱ እህቶቻችንን ደግሞ ከመታዘብ አሊያም ከመውቀስ የሚገደን ነገር የለም:: ውብ የሆነው የሴቶቻችን ገላ በፀሐይ፣ በብርድ እና በሰው ዐይን ሲለበለብ እያየን ካላዘንን በምን ልናዝን ነው?
እራፊ ጨርቅ ገላቸው ላይ አሳርፈው አደባባይ የሚወጡ እህቶቻችን ለገላቸው ከሚሰጣቸው ውዳሴ ይልቅ ለነውራቸው የሚለገሳቸው እርግማን ይበዛልና ምርጫቸው ልክ አለመሆኑን መናገር ይገደናል:: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትላላቅ ሆቴሎች እና ሌሎች ድርጅቶች ውስጥ በመስተንግዶ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ዜጎች የአለባበስ መመሪያ አወጣለሁ ሲልም በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያዊ የአለባበስ ባህሎቻችንን ለተቀረው ዓለም ሕዝብ አስተዋውቃለሁ ማለቱ እንደሆነ አያጠራጥርም::
አንዲት ሴት በለበሰችው ጉርድ ቀሚስ ምክንያት ታክሲ ላይ መሳፈር፣ ወንበር ላይ መቀመጥ እና ለሌሎችም ድርጊቶቿ ምቾት ካጣች የቆራጣው ቀሚስ ጥቅም ምን ይሆን? በለበሰችው አጭር ቀሚስ ምክንያት ጐንበስ ካለች ነውሯ የሚታይባት ሴት የልብሷ ጥቅም ምን ይሆን? ከውስጥ ሱሪ የማይሻል ወይም የውስጥ ሱሪዋን የሚያሳይ ቀሚስ የለበሰች ሴት እጆቿን አስሬ ቀሚሷን ወደ ታች ለመሳብ ስትጠቀምባቸው የመዋሉ ልፋት ምን ለማግኘት የታሰበበት ነው? አለባበሳችን ብቻ ሳይሆን አስተሳሰባችን ኢትዮጵያዊ ለሆንን ሰዎች ከተገላለጠው ውበት ይልቅ የተሸፋፈነው ይማርከናል፤ በምናባችሁ አንዲት ከላይም ሆነ ከታች ገላዋን አጋልጦ የሚያሳይ ልብስ የለበሰችን ሴት እና የሀበሻ ቀሚስ የለበሰችን ሴት አስቀምጡ እና ለየትኛዋ አክብሮት ይኖራችኋል? መልሱ የግላችሁ ቢሆንም የብዙዎቻችን አድናቆት በሀበሻ ቀሚስ ላጌጠችው ሴት እንደሚሆን ግን አልጠራጠርም::
በአብዛኛዎቹ የሕንድ ፊልሞች ውስጥ የምናየው የሴት ተዋናዮቹ አለባበስ የሀገራቸውን ባህል ያከበረ ነው:: በብዙ የአረብ ሀገራት ውስጥ ሴቶች የስፖርት ትጥቆችን ለብሰው በስፖርቱ መድረክ እንዳይሳተፉ የሚደረጉትም ሀገራቱ ባላቸው የአለባበስ መመሪያ እና ደንብ መሰረት እንጂ ሆን ተብሎ በሴቶች ላይ ጫና ለማሳደርም አይመስለኝም:: በሀይማኖት ተፅዕኖ ምክንያት የስፓርት ትጥቆችን እንዳይለብሱ የተገደዱ ሴቶች የመብት ጥያቄ ከማንሳትም አልፈው በብዙዎቹ ሀገራት ዘንድ ፈቃድ እያገኙ ዐይተናቸዋል::
ገላን አራቁቶ የተቃራኒ ፆታን ዕይታ መከጀል በየትኛውም መስፈርት መሰልጠን ሊሆን አይችልም:: በአንድ ወቅት ታዋቂዋ አሜሪካዊት የፓኘ ሙዚቃ አቀንቃኝ ማዶና የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ብላ መለመላዋን (እርቃኗን) አደባባይ ወጣች፤ በእርግጥም ማዶና እንዳሰበችው የብዙ አሜሪካዊያንን ብቻ ሳይሆን የዓለም ሕዝብን ትኩረት መሳብ ትላለች፤ አሜሪካንን ጨምሮ ብዙ ሀገራትም እንደ ማዶና እርቃን ሆኖ አደባባይ ላይ መውጣት በሕግ የሚያስቀጣ መሆኑን ደንብ አውጥተዋል::
በኛም ሀገር ለማዶና ሩብ ጉዳይ የሆኑ ሴቶችን አደባባይ ወጥተው ብናያቸውም በሕግ ሲጠየቁ ግን አላየናቸውም:: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር መስተንግዶ ላይ በሚሠሩ ዜጎች የሚጀምረውን የአለባበስ መመሪያ በሁሉም የሀገራችን ክፍል የሚተገበርበት ጊዜም ሩቅ አይሆንም የሚል ግምቱ አለኝ::
የሃሳቤን ማጠንጠኛ በአብዛኛው በሴቶች አለባበስ ላይ ስላደረኩት እንጂ የአንዳንድ ወንዶች አለባበስም በኛ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከነውርም ያለፈ ነውር ሆኖ እያየነው ነው:: ሱሪያቸውን ወደታች ዝቅ አድርገው እንደተገረዘ ልጅ እዚያና እዚህ እየረገጡ የሚሄዱ ወንዶች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው:: በአሜሪካ ፊልሞች ውስጥ የጥቁር ተዋናዮችን አለባበስ ኮርጆ ኢትዮጵያ ውሰጥ መልበስ መሰልጠን ሳይሆን የራስን ባህል ያለማወቅ ምስክርነት ነው::
ወንድ ልጅ ሱሪውን ያለቀበቶ ሲታጠቅ አያምርበትም በሚባልባት ሀገራችን፣ የወንድ ልጅን መሸነፍ ለመግለፅ ‘ሱሪውን አስወለቁት’ በሚባልባት ሀገራችን ውስጥ በራሳቸው ፈቃድ ሱሪያቸውን ዝቅ አድርገው ቆሻሻቸውን ለሚያሳዩን ወንዶችም የአለባበስ መመሪያ እና ደንብ ሊወጣላቸው ይገባል::
በርከት ያሉ የታክሲ ረዳቶች ሱሪያቸውን ዝቅ አድርገው መልበሳቸው ብቻ ሳይሆን ከሱሪያቸው በታች የቆሸሸ የውስጥ ሱሪያቸውን እያሳዩን መሄዳቸው ለእኛ ለሀበሾች በእጅጉ ነውር ነው፤ ሴት ልጅ ችግርን ለመቋቋም መቀነቷን ጠበቅ ታደርጋለች እንደሚባለው ሁሉ ወንድ ልጅም በችግሩ ወቅት ቀበቶውን ጠበቅ በማድረጉ ይታወቅ ነበር::
ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት እኛ ኢትዮጵያዊያን የበርካታ አካባቢዎችን የሸማ ሥራ የታደልን እና የተለያዩ ውብ አለባበሶች ያሉን ሕዝቦች ነን:: የሴቶቻችን የፀጉር ስሪት በብዙ ዓለም ሴቶች ዘንድ ተወዳጅ ሆኖ እንደተኮረጀው ሁሉ የብዙ እህቶቻችን አለባበስም የብዙዎችን ዐይን እየሳበ ይገኛል:: እዚህ ጋር ጥቂት አብነቶችን ለመግለፅ ያህል ታዋቂዋ አሜሪካዊት የቴሌቪዥን ውይይት አዘጋጇ ኦፕራ ዊንፍሬ በሀበሻ ቀሚስ አጊጣ ዝግጅቷን ስታቀርብ ብዙዎቻችን ዐይተናታል:: ታዋቂዋ አቀንቃኝ ቢዮንሴ ኖልስም ፀጉሯን ሹሩባ ተሰርታ እና የሀበሻ ቀሚስ ለብሳ መድረክ ላይ ሥራዋን ስታቀርብ የብዙዎቻችንን ቀልብ ስባለች::
በራስ ወርቅ መድመቅ እየተቻለ የሌሎቹን ልባሽ መከጀል፤ በፍላጐት ቅኝ የመገዛት እሳቤ ነው:: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መስተንግዶ ላይ ለሚሰሩ ዜጎቻችን የሚያወጣው የአለባበስ መመሪያ እና ደንብ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ተፈፃሚ እንዲሆንም ምኞቴ ነው:: የእኔ ሥጋት በሀገራችን ውስጥ የሚወጡ መመሪያ እና ደንቦች አብዛኛዎቹ የተፈፃሚነት ችግር ስላለባቸው ከአለባበስ ጋር ተያይዞ የወጣው መመሪያ እና ደንብም ደብዛው እንዳይጠፋ የሚል ነው::
ከሁሉም በላይ ግን የማያምርብንን እና የሚያነውረንን ልብስ አውልቀን በሚያምርብን እና በሚያስከብረን ልብስ መቀየሩ መመሪያ እና ደንብ ባያስፈልገው ጥሩ ነው እላለሁ:: እናንተስ? ሃሳብ አስተያየታችሁን ለአሚኮ በኩር ጋዜጣ ይድረስ በሉ እና እናስተናግድላችኋለን::
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም