ራዕይን በጽናት

0
119

ዐይናዲስ ጋሻው ተወልዳ ያደገችው በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ግና ቂርቆስ ቀበሌ ነው:: የተወለደችበትን ቀዬ ለቃ አሁን ወደ ምትኖርባት  ባሕር ዳር የመጣችው ደግሞ የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያለች በሕጻንነት ዕድሜዋ ነበር::

በአሁኑ ወቅት ዐይናዲስ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናት:: የጽናት ተምሳሌቷ ባለታሪካችን እስከ ሰባተኛ ክፍል ከአክስቷ ጋር ሆና ትምህርቷን ተከታትላለች:: የዛሬ  የሕይወት ውጣ ውረዷ ጅማሮውን የሚያደርገውም ከሰባተኛ ክፍል በኋላ ነው::

የሕይወትን ውጣ ውረድ ገና በልጅነት ዕድሜ እያስተናገደች ያለችው ዐይናዲስ፣ ከሰባተኛ ክፍል ጀምራ አሁን እስከ ደረሰችበት የክፍል ደረጃ ራሷን በራሷ እያስተዳደረች ትገኛለች:: የታሪኳን ጅማሮ ዐይናዲስ የምታስታውሰው እንዲህ በማለት ነው፡- “የአክስቴ ባለቤት ወታደር ነው፤ በሥራ ምክንያት ወደ ሌላ ቦታ ሲቀየር አክስቴ እኔን ከልጆቿ ጋር እያስተማረች ለማስተዳደር አቅም አነሳት፤ እኔ ደግሞ ትምህርቴን አቋርጨ ወደተወለድሁበት ገጠር መመለስ አልፈለግሁም፤ ቤት ተከራይቼ ለመማር ወሰንኩ፤ አሁን አክስቴ ከምታግዘኝ በተጨማሪ ከትምህርቴ ጎን ለጎን በተመላላሽ እየሠራሁ በማገኘው ገቢ ራሴን በራሴ እያስተዳደርኩ ነው::”

ታታሪዋ ዐይናዲስ የዛሬን ፈታኝ ሕይወት አልፋ ከነገ ለመድረስ ትልቅ ትልምን አስቀምጣለች:: ይህም ይበልጥ እንድትበረታ፣ ለችግር እጅ እንዳትሰጥ፣ ወዳልተፈለገ ሕይወት እንዳትገባ፣ ይልቁንም ለሌሎች በአርአያነት ለመጠቀስ እንድትተጋ አድርጓታል::

ዐይናዲስ ጥዋት ስትነሳ የተዘጋጀ ምግብ አይጠብቃትም:: እንደ ሌሎች ተማሪዎች ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት መሄድ፣ መማር እና ሰዓትን ጠብቆ ወደ ቤት መመለስም የዐይናዲስ የዕለት ከዕለት ክዋኔዎች አይደሉም::

የዐይናዲስ የዘወትር የጥዋት መነሻ ሰዓት ከንጋቱ 10፡30 ነው:: ቀኗ መልካም ሆኖ ያሰበችው ሁሉ በቀና መንገድ እንዲጓዝላት ጸሎት የዘወትር ቀዳሚ ተግባሯ ነው:: ከዚያም ቁርሷን ትሠራለች:: ጾም ካልሆነ ተመግባ ከትምህርት ሰዓቱ መጠናቀቅ በኋላ ጉዞዋ ወደ መኖሪያ ቤቷ ሳይሆን ገቢ ወደምታገኝበት የሥራ ቦታ በመሆኑ ለምሳ የሚሆናትንም ቋጥራ ወደ ትምህርት ቤት ትሄዳለች::

ልብስ ማጠብ፣ እንጀራ መጋገር፣ አልፎ አልፎም ጽዳት ዐይናዲስ በተመላላሽ የምታከናውናቸው ሥራዎች ናቸው:: የገቢ መሠረቷ የሆኑ እነዚህን ሥራዎች በአብዛኛው የምታከናውናቸው ከትምህርት ቤት መልስ ባሉ ጊዜያት ነው:: እነዚህ ጊዜያት ለብዙዎች በመምህራን የተሰጡ የመለማመጃ የቤት ሥራዎችን ለመሥራት፣ ምቹ  ቦታን መርጦ ለማጥናት፣ ቤተ መጻሕፍት ለመጠቀም፣ ለእርስ በእርስ መረዳጃ… የሚውሉ ናቸው:: ዐይናዲስ ግን ሁሌም ከትምህርት ውጪ ያሉ ጊዜያትን በተመላላሽ ለምትሠራቸው ሥራዎች ታውላለች:: ከቤተሰብ ጋር ሆነው ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች  ለእረፍት እና ለቤተሰብ የሚሰጧቸው የአመሻሽ ጊዜያት ደግሞ ለወጣቷ የጥናት ሰዓቶች ይሆናሉ::

የሥራ መደራረብ እና ድካም በትምህርት አቀባበሏ ላይ አሉታዊ ጫና እንዳይፈጥር ያሏትን ጊዜያት የማጣጣም ሥራ እንደምትሠራ ተናግራለች:: አልፎ አልፎ ከመደበኛው የትምህርት ሰዓት ውጪ የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርት በሚኖር ወቅት የገቢ ምንጭ ማግኛ ሥራዋን ወደ ሌሊት የማሸጋገር ልምድ እንዳላት ተናግራለች:: ይህንን የምታደርገው ግን ደኅንነቷን ስጋት ላይ በማይጥሉ ጊዜያት ብቻ መሆኑን ጠቁማለች::

ዐይናዲስ የተሻለ የትምህርት አቀባበል እንዳላት ተናግራለች:: አብዛኛው የጥናት ጊዜዋ ጅማሮውን የሚያደርገው ከምሽቱ 2፡00 በኋላ ነው:: ይህንን ጊዜ ለምን ምርጫዋ እንዳደረገች ዐይናዲስ ትናገራለች፤ “ውሎዬ አድካሚ በመሆኑ በቂ እረፍት ማድረግን አስቀድማለሁ፤ የምኖርበት ግቢ ለጥናት ምቾት የማይሰጡ ድምጾች የሚስተጋቡበት በመሆኑ ጥናት የምጀምረው ሁሌም ከምሽቱ 2፡00 ነው::”

ከዚህ ሰዓት ጀምሮ እስከ 8፡00 ያለውን ጊዜዋን የምታሳልፈው በመተኛት ሳይሆን በጥናት  መሆኑ ነግራናለች:: ሰፊውን የእንቅልፍ ጊዜ ለጥናት የማዋሉ ምስጢርም በዚህ ዓመት የሀገር አቀፍ ፈተና ስለምትወስድ ከምትማረው ውጪ በየክፍል ደረጃው ሳትማር ያለፉ የትምህርት ይዘቶችን ለመሸፈን ነው:: ቀሪ ጊዜዋን በአግባቡ ለመጠቀም በመምህራን የሚሰጡ መልመጃዎችን ትምህርት ቤት ውስጥ ሠርቶ የማጠናቀቅ ልምድ እንዳላትም ተናግራለች::

“እስካሁን የመጣሁበትን የድካም መንገድ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ዳር ለማድረስ ጥረት እያደረግሁ ነው፤ ሜዲካል ሳይንስ ማጥናት ደግሞ ትልቁ ህልሜ ነው፤ የተጨናነቀ ጊዜዬም ማስመዝገብ በምፈልገው ውጤት ላይ ጫና እንዳያሳድርብኝ ጥንቃቄ እያደረግሁ ነው”  በማለት ለህልሟ እውን መሆን እያደረገች ያለውን ጥረት አጫውታናለች::

የፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ስለ ዐይናዲስ ምስክርነትን ሰጥተዋል:: ብዙ ጊዜ የድካም ስሜት እንደሚስተዋልባት፣ ነገር ግን በትምህርቷ ደግሞ ጠንካራ እና ለሌሎች አርአያ መሆን እንደምትችል መስክረዋል:: ብዙ ሰዎች ትንሽ ነገር ሲጎድልባቸው ተስፋ የሚያደርጉት ያጣሉ፤ የዐይናዲስ ጽኑ ተስፋ ግን ለብዙዎች አርአያ መሆን የሚችል እንደሆነ ጠቁመዋል::

ራሷን ሰው ለማድረግ የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑንም መምህራኖቹ ተናግረዋል:: “በቀጣይ የሚሰጠውን ሀገር ዓቀፍ ፈተና በድል ተወጥታ ዩኒቨርሲቲ እንድትገባ ጊዜ ያስፈልጋታል” ያሉት መምህራኖቹ… በመሆኑም ከሥራ ጫና እንድትወጣ አቅም ያለው ሁሉ በኢኮኖሚ ሊደግፏት እንደሚገባ ጠይቀዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የታኅሳስ 147 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here