“ርካሽ’’ የሚባል የሰው ጉልበት አለ?

0
83

አንዳንድ ሀገራት በተፈጥሮ ከታደሉት ሀብት በተጨማሪ የሰው ኃይል ሀብታቸው ሌላኛው አቅማቸው ኾኖ ይታያል:: አንዳንድ ሀገራት ደግሞ እንደ ነዳጅ እና ማዕድን የመሳሰሉ የተፈጥሮ ሀብት ኖሯቸው የሰው ኃይል ሀብት በማጣት ሲቸገሩ ይስተዋላሉ::

የተፈጥሮ ሀብት ኖሯቸው የሰው ኃይል ያጡ ሀገራት  የሰው ኃይል ካላቸው ሀገራት የሰው ኃይልን ያስገባሉ:: ከዚህ ሁኔታ የምንረዳው አንዳንድ ሀገራት ምንም እንኳን ተፈጥሮ ፀጋዋን አብዝታ ብትለግሳቸውም ያንን ፀጋ ወደ ሀብትነት የሚቀይርላቸው የሰው ኃይል ይፈልጋሉ::

እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራትም ቢኾኑ በየዓመቱ የዲቪ ሎተሪ ዕድልን እያመቻቹ ከተለያዩ ሀገራት የሰው ኃይልን ወደ ሀገራቸው የሚያስገቡት ለፅድቅ ሲሉ አለመሆኑ ይታወቃል:: በብዙዎች ዘንድ እንደ ምድረ ገነት የምትቆጠረው አሜሪካ የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን ወደ ጉያዋ ለመሳብ የጠቀማትም የምትከተለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ለሚሠራላት ሰው የምትከፍለው ምንዳዋም ጭምር ነው::

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት እና አንዳንድ የሌላ አህጉር ደሃ ሀገራት ያላቸውን የሰው ኃይል ወደ ሀብትነት መቀየር ተስኗቸው ዜጎቻቸውን ለስደት ሲዳርጉ ይስተዋላሉ:: ለሰው ሀብት ልዩ ትኩረት የሰጡ አውሮፓውያንና ሌሎች ሀብታም ሀገራት ደግሞ በስደት እና በሕጋዊ መልኩ የሚመጣላቸውን የሰው ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ሲያውሉት እያስተዋልን ነው::

ሀገራችንን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በተፈጥሮ የታደሉትን ፀጋ በአግባቡ ማልማት ተስኗቸው በሀብት ላይ ተኝተው የሚራቡ ኾነዋል:: ኢትዮጵያችን የውጪ አልሚዎችን (ኢንቨስተሮችን) ለመሳብ በምታደርገው ጥረት ውስጥ “በሀገሪቱ ርካሽ የኾነ የሰው ጉልበት መኖሩ” የሚለው መስፈርት እኔን በግሌ ደስ የማይለኝ አገላለጽ ነው:: የዛሬው ትዝብቴ ማጠንጠኛም ይሄው ቀላል የሚመስል ግን ደግሞ የሰውን ልጅ ጉልበት የሚያራክስ ጉዳይ ነው::

በእርግጥ በሀገራችን ውስጥ አስደማሚ ልማትን ማምጣት የሚችል በርካታ የሰው ኃይል መኖሩ አይታበልም፤ ነገር ግን ይህንን የሰው ኃይል “ርካሽ የሰው ጉልበት” በሚል አልሚዎችን ለመሳብ መጠቀም ስህተት ይመስለኛል:: የሰው ኃይል ወይም የሰው ጉልበት ከላይ በጽሑፌ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በተፈጥሮ ከሚገኝ ፀጋ ባልተናነሰ አስፈላጊ የሆነ ሀብት ነው:: ይህንን ሀብት አሳንሶ በማየት ወይም ለዜጎች ጉልበት ተገቢውን ክብር ባለመስጠት «ርካሽ የሰው ኃይል» በሚል ማስተዋወቅ በየትኛውም መስፈሪያ ልክ ሊሆን አይችልም::

ሀገራችን ውስጥ መጥተው ማልማት ለሚፈልጉ የውጪ ባለሀብቶች ማልማት ለሚፈልጉት ነገር የሚሆናቸው ጥሬ ዕቃ፣ የተፈጥሮ ፀጋና በቂ የሆነ የሰው ኃይል መኖሩን መግለጽ ተገቢ ነው:: በቂ የሆነ የሰው ኃይል ማለት ግን «ርካሽ የሰው ኃይል» ማለት እንዳልኾነ ሊሰመርበት ይገባል::

የተለያዩ መረጃዎችን ሳነብ በታዘብኩት መሠረት በርካታ የአፍሪካ እና የሌሎችም ደሃ አህጉራት ዜጎች ወደ ሀገራቸው   ገብተው የሚያለሙ የውጪ ባለሀብቶች ለሀገራቱ  የጉልበት ሠራተኞችም ሆኑ ለሠለጠኑ ሙያተኞች የሚከፍሉት ደመወዝ አነስተኛ ነው:: የዚህ ምክንያቱ  ደግሞ ባለሀብቶቹ ወደ ሀገራቱ  እንዲመጡ ሲጋበዙ «ርካሽ የሰው ጉልበት» አለ ተብለው ተቀስቅሰው ወይም (ሎቢ) ተደርገው ስለኾነ ይመስለኛል::

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ሀገራችን ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ የሠለጠኑ ዜጎቿን ለሥራ ወደ አረብ ሀገራት መላኳን ገልጸዋል:: እነዚያ የኢትዮጵያውያንን የሰው ኃይል የፈለጉ ሀገራት ደግሞ መቼም ቢሆን ርካሽ የሰው ጉልበት ከኢትዮጵያ አገኘን እንደማይሉ እርግጠኛ ነኝ::

ሀሳቤን በሌሎች አብነቶችም ላፍታታው:: ኳታር የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት የዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን ብቻ ሳይሆን በርካታ የሰው ኃይልም አስፈልጓታል:: በነዳጅ ሀብቷ የበለጸገችው ኳታር ለዓለም ዋንጫው ዘመናዊ ስታዲየሞችን ስትገነባ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በተጨማሪ በርከት ያለ የሰው ኃይልም አስፈልጓት ስለነበረ ለተለያዩ የዓለም ሀገራት የሰው ኃይል ጥሪ አድርጋለች::

የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ባየነው መልኩ በደመቀ እና ባማረ መልኩ እንዲጠናቀቅም ኳታር ከዓለም ዙሪያ ወደ ቀዬዋ ለመጡ ብዙ የቀን ሠራተኞች እና ሙያተኞች በርካታ ሚሊዮን ብሮችን ከፍላለች:: ኳታር የዓለም ዋንጫውን ለማዘጋጀት ምንም እንኳን  የገንዘብ አቅሙ ቢኖራትም የሰው ኃይል ስላልነበራት ይሄንን ሀብት ያሰባሰበችው የሰው ሀብት ካላቸው ሀገራት ነው::

ሌላም አብነት ላንሳ፤ ጀርመኖች ምንም እንኳን በርካታ የሠለጠነ የሰው ሀብት ቢኖራቸውም በቅርቡ አጋጥሟቸው የነበረውን የሕክምና ሙያተኞች እጥረት የቀረፉት ለዓለም ሀገራት ባሰራጩት “የሕክምና ባለሙያ እንፈልጋለን” ማስታወቂያ ነው::

በርካታ የስካንዲቪያን ሀገራት ደግሞ የሀገራቸው ሀብት እና ያላቸው የሕዝብ ቁጥር አልመጣጠን እያላቸው ልጆችን አብዝተው ለሚወልዱ ዜጎቻቸው በርካታ ሽልማቶችን በገጸ በረከትነት ሲያቀርቡ እያስተዋልን ነው:: ሀብት ኖሯቸው የሰው ኃይል ያጡ ሀገራት በትምህርት ዕድል እና በመሳሰሉት አጋጣሚዎች የሌሎች ሀገራትን ዜጎች የሚያማልሉት ወይም የሚያስኮበልሉትም ያለምክንያት አይደለም::

ቻይና እና ሕንድን የመሳሰሉት ሀገራት የሕዝብ ብዛታቸው የዓለምን ብዙ ድርሻ ቢወስድም ሁለቱም ሀገራት “ርካሽ የሰው ጉልበት አለን” ብለው ሲቀሰቅሱ ተደምጠው አያውቁም:: ሁለቱም ሀገራት በተለያየ የሙያ መስክ ያሠለጠኗቸውን ዜጎቻቸውን በተለያዩ የአፍሪካና ሌሎችም አህጉራት አሰማርተው ለዜጎቻቸው የሥራ ዕድልን ሲፈጥሩ ግን ዓይተናል:: በኛ ሀገር በቅርቡ እንደተጀመረው ዜጎችን አሠልጥኖ ወደ አረብ ሀገራት በመላክ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ሁሉ ማለት ነው::

የሰው ኃይልን በርካሽነት መፈረጅ ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ ነው:: የሰው ኃይል መታየት ያለበት እንደ መልካም ፀጋ እንጂ እንደ ትርፍ ነገር መኾን የለበትም:: በማዕድን ማውጣት፣ በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በኃይል አቅርቦትና ሌሎችም ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ጉልበታቸውና የሙያ ክህሎታቸው በርካሽ የሚገኝ ተደርጎ መታሰቡ መቆም ይኖርበታል:: ኢትዮጵያ ያላት በርከት ያለ የሰው ኃይል እንጂ ርካሽ የሰው ጉልበት አለመሆኑም መታወቅ አለበት::

“የሰው ያለህ!” እያሉ የሚጣሩ ሀገራት በበዙባት ዓለማችን ውስጥ የሰው ኃይልን እንደ ትልቅ ሀብት ባለመቁጠር ለዜጎች በቀንም ይሁን በወር የሚከፈላቸው ገንዘብ ለዕለት ጉርስ የማይበቃ ከኾነ፣ ለዜጎች ጉልበት እና ዕውቀት የሰጠነውን ዋጋ ርካሽነት ማረጋገጫ ስለሚኾን አገላለጻችን ማስተካከያ ቢደረግበት በብዙ እናተርፋለን ::

አንዳንድ ሀገራት የተፈጥሮ ጸጋ ኖሯቸው የሰው ጸጋን ግን አልታደሉም:: እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የተፈጥሮንም ሆነ የሰው ጸጋን  የታደልን በመሆናችን በሁለቱም ጸጋዎቻችን ተጠቅምን ቀድመን ትልቅ እንደነበርነው ሁሉ አሁንም ወደ ትልቅነታችን መመለስ ይኖርብናል፤  ያን ማድረግ ባንችል እንኳን አንደኛውን ጸጋችንን (የሰው ኃይል) በጭራሽ አሳንሰን ማየት አይኖርብንም::

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here