አያት ቅድመ አያቶቻችን የወራሪውን የፋሽስት ጣሊያን ጦር ድባቅ መተው ከሀገራችን ጠራርገው ካስወጡት ከ25 ዓመታት በኋላ ነው ሻምበል አበበ ቢቂላ ሁሌም ተደጋግሞ የሚሰማውን እና የሚነበበውን ገድል በሮም ጎዳናዎች የፈጸመው።
ሻምበል አበበ ቢቂላ እ.አ.አ በ1960 በሮም ኦሎምፒክ ነው ለአፍሪካ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በማራቶን ውድድር ያጠለቀው። የክብር ዘበኛው ወታደር ድል ጥቁር አፍሪካውያን በኦሎምፒክ እንዲሳተፉ በር ከፍቷል፤ በቅኝ ግዛት ለነበሩት የአፍሪካ ሀገሮችም ድል አብሳሪ ሆኖ መነቃቃትን ፈጥሯል።
ሀገራችን በ1960 እ.አ.አ በሮም ኦሎምፒክ በሁለት የስፖርት ዓይነቶች መሳተፏን የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ፤ በአትሌቲክስ እና በብስክሌት ስፖርቶች። የኢትዮጵያ ልዑክ ለሮም ኦሎምፒክ በስዊድናዊው አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን እየተመራ ቀደም ብሎ ወራት ሲቀሩት ነበር ዝግጅት የጀመረው።
ቀኑ ሲቃረብም ብሄራዊ ቡድኑ ወደ ቦታው ለማቅናት አትሌቶችን በመምረጥ ለጉዞ ተዘጋጅቷል። ዋሚ ቢራቱ፣ ንጉሤ ሮባ እና አበበ ዋቅጅራ በማራቶን ኢትዮጵያን እንዲወክሉ ተመርጠዋል። ለወራት ጠንካራ ልምምድ ያደረገው አበበ ቢቂላ ግን አልተመረጠም ነበር። በሌሎች ርቀቶች ሙሳ ሰይድ እና ማሞ ወልዴ፣ በብስክሌት ስፖርት ደግሞ ገረመው ደንቦባ፣ አላዛር ክፍሉ እና ሌሎች አትሌቶች ወደ አውሮፓ ለማቅናት በአውሮፕላን ማረፊያው እየተጠባበቁ ነው።
በኦሎምፒክ ጨዋታዎች አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ልዑክ ጭምር እንዲመሩ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። የኢትዮጵያ ልዑክም አውሮፕላኑ ነዳጅ እስኪሞላ እየተጠባበቀ ነው። ብዙዎቹ የመጀመሪያቸው ስለሆነ ጉጉት፣ አግራሞት እና ፍርሀት ይስተዋልባቸዋል። ማሞ ወልዴ፣ ንጉሤ ሮባ እና ባሻዬ ፈለቀ በ1956ቱ የሜልቦርን ኦሎምፒክ በመሳተፋቸው እና ልምድ በማካበታቸው ምንም ዓይነት የተለየ ስሜት አልታየባቸውም።
በተለይ ንጉሤ ፈለቀ ከአሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን ጋር ስዊድን ደርሶ የመጣበትን አጋጣሚ በማስታወስ በጀግንነት የፈጸሙትን ሥራ ይተርክላቸዋል። አበበ ዋቅጅራም በንግግራቸው መሀል እየገባ ወጣት አትሌቶች ፍርሀታቸውን እንዲያስወግዱ ይመክራል፤ ይዘክራል። ለፈጣሪያቸው ደግሞ ጸሎት እንዲያደርጉ ያሳስባል። ከዚህ ልዑክ ጋር ያልነበረው በሮም ኦሎምፒክ ያሸንፋል ተብሎ የተጠበቀው ዋሚ ቢራቱ ነው።
እርሱን ለማምጣት ደግሞ የስፖርት ዳይሬክተሩ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እና ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ወደ ቤቱ አቅንተዋል። ከብዙ ጥበቃ በኋላ አቶ ይድነቃቸው እና ፍቅሩ ኪዳኔ ድጋሚ ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ተመልሰዋል። እየከነፈች አውሮፕላን ማረፊያ በደረሰችው ጂፕ መኪና ውስጥ ግን ዋሚ ቢራቱ አልነበረም። ሁለቱ ታላላቅ የስፖርት ሰዎችም ለወራት ለሮም ኦሎምፒክ ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ የነበረው ዋሚ ቢራቱ እግር ኳስ ሲጫወት የመጎዳቱን ዜና ለስዊድናዊ አሰልጣኝ አረዱ።
ዋሚ ጉልበቱን በመጎዳቱ ቶሎ እንደማያገግም ሀኪሞች ማረጋገጣቸውን ጭምር አክለው አቶ ይድነቃቸው ተናገሩ። በዚህ የተደናገጡት አሰልጣኙ በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ልምድ የሌለውን እና በምርጫው ያልተካተተውን አበበ ቢቂላን ይዘው ለመጓዝ ወሰኑ።
የባዶ እግር ሯጩን (Bare foot runner) መጽሐፍ ስንገልጠው የሻምበል አበበ ቢቂላን ድርሳን እንዲህ ያስነብበናል። የክቡር ዘበኛው ወታደር አበበ ቢቂላ ለኦሎምፒክ አለመመረጡን ቀድሞ ስላወቀ የዕለት ተግባሩን በማከናወን ላይ እያለ ነበር አቶ ይድነቃቸው እና ጋዜጠኛ ፍቅሩ ያገኙት።
ሁለቱ የስፖርቱ ሰዎች አበበ ቢቂላን በመያዝ አውሮፕላን ማረፊያው ደረሱ። አውሮፕላኑም በዋሚ ቢራቱ የተተካውን እና ታላቅ ገድል እንደ ሚፈጽም ያላወቀንው ጀግናውን አበበ ቢቂላን ይዞ የሜዲትራንያንን ባሕር አቆራርጦ በአውሮፓ ምድር ጣሊያን ደረሰ።
ጣሊያን በደረሰ ማግስትም ልምምድ ጀምረዋል። በቀጣዩ ቀን አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን አትሌቶችን ለማስመዝገብ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ወደ ሚደረግበት ስቴዲየም ይዟቸው መሔዱን መጽሐፉ ያትታል።
ለሀገሩ ባዳ ለሕዝቡ እንግዳ የሆነው አበበ ቢቂላ በስቴዲየሙ ውስጥ በየቦታው ልምምድ የሚሠሩ አትሌቶችን ይመለከታል። ከማሞ ወልዴ ጋርም የሚሠሩትን በአጽንኦት ይከታተላል። ከአንድ አሜሪካዊት ስፖርተኛ ጋርም ይተዋወቃል። አበበ ከምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ እንደመጣ እና በማራቶን እንደሚወዳደር ለአሜሪካዊት ሰፖርተኛ ይገልጽላታል። ይሁን እንጂ ንግግራቸውን በዝምታ ሲከታታል የነበረ ማይክ የሚባል አሜሪካዊ ስፖርተኛ በመሀል ጣልቃ በመግባት ማራቶን ከባድ እንደሆነ ያወራል።
የውድድሩን መጨረሻ መስመር እንዳለፈ ነፍስ እና ሥጋው እንደሚለያይ በመንገር አበበን ያስፈራራዋል። አሜሪካዊቷ ዊልማ ግን ጣልቃ በመግባት ማይክ አበበን ማስፈራራት እንደሌለበት በማመን ታስቆመዋለች፤ ትገስፀዋለችም። አሜሪካዊቷ ስፖርተኛ ጓደኛዋ የተናገረውን በሙሉ አበበ እንደማይረዳው በመንገር ለአበበ መልካም ምኞቷን በመግለጽ ትሰናበተዋለች።
አሁን የጭንቁ ቀን እየተቃረበ ነው። የማራቶን ውድድሩ ሊካሄድ ሁለት ቀናት ብቻ ቀርተውታል። አሰልጣኝ ኒስካነን የውድድሩን መነሻ እና መድረሻ ለኢትዮጵያውያን ማራቶን ሯጮች ለማሳየት፣ ሌሎች ቴክኒኮችንም ለማስረዳት ወደ ሮም ከተማ ደቡባዊ ክፍል መኪና በመከራየት አትሌቶችን ይዟቸው ይሄዳል።
አሰልጣኝ “ዛሬ ልምምድ ትሠራላችሁ፤ ነገ ታርፋላችሁ፤ በቀጣዩ ቀን ውድድሩ ይደረጋል::” ይላቸዋል። በ10ሺህ እና በሌሎች ርቀቶች እንዲሁም በብስክሌት ውድድር የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች ውጤት አልቀናቸውም። ብቸኛው የሜዳሊያ ተስፋም ማራቶን ብቻ ሆኗል። አበበ ቢቂላ ሌሎችን ውድድሮች ስቴዲየም ገብቶ ተመልክቷል። ከእነዚህም ብዙ ልምድ ቀስሟል።
“በማራቶን ውድድር ፍጥነት አስፈላጊ ነው፤ ፍጥነት መቀነስ ዋጋ ያስከፍላል፤ ጥንካሬ እና ብርታት ያስፈልጋል። ስለዚህ ድካም እና ህመሙን በመርሳት ወደ ፊት መሮጥ ይኖርብኛል። ነገር ግን አትጨነቁ፤ አሸንፋለሁ” ሲል ከውድድሩ መጀመር ቀደም ብሎ የክብር ዘበኛው ወታደር በልበ ሙሉነት ለአሰልጣኙ እና ለአቶ ይድነቃቸው ተናግሯል።
በእርግጥም ቃሉን እንደሚፈጽም ስዊድናዊው አሰልጣኝ ተማምነዋል። ሩሲያዊውን ሰርጌ ፖፖቭን እና ሞሮኳዊውን ራህዲ ቤን አብዱ ሰላምን ግን አሳንሶ እንዳያያቸው መከሩት። እነዚህ አትሌቶች ሲሮጡ አብረው ተጠጋግተው በመሆኑ እነርሱን መከታተል እንዳለበት አሰልጣኙ አስረድተውታል።
በአሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን መሪነት ሮምን እየጎበኙ ያሉት የማራቶን ተወዳዳሪዎች ጣሊያን ከኢትዮጵያ የዘረፈውን የአክሱም ሀውልት ካቆመበት የሮም አደባባይ ደረሱ። ሁሉም ከመኪናቸው በመውረድ የአክሱምን ሀውልት ተመለከቱ። ተወዳዳሪዎቹ አበበ ቢቂላ እና አበበ ዋቅጅራ ልምምድ ለማድረግ ማሟሟቅ ጀመሩ። ንጋት በመሆኑ ፀሐይ መውጣት ጀምራለች።
የሀውልቱ ጥላ በእነርሱ ላይ ሲያርፍ የሚያናግራቸው እንደመሰላቸው ተሰማቸው። የእነርሱን የቁጭት ፊት የተመለከቱት ኒስካነን ሀውልቱን ያውቁት እንደ ሆነ ለሁለቱ አትሌቶች ጥያቄ አቀረቡ። በእርግጥም ታሪኩን ጠንቅቀው ያውቁታልና በቁጭት ጉዳዩን መተረክ ጀመሩ። አሰልጣኙ ይህን ጉዳይ ያነሱት አንድም በቁጭት ውጤት እንዲያመጡ፣ አንድም ከዚህ ሲደርሱ ፍጥነታቸውን እንዲጨምሩ ለማስታወስ ነው።
የማራቶን ውድድሩ መነሻ እና መድረሻ ዝነኛው የአክሱም ሀውልት ከቆመበት የሮም አደባባይ በዐስር ኪሎ ሜትር ብቻ ይርቃል። ስለሆነም የውድድሩ ወሳኝ ቦታ በመሆኑ የማሸነፊያ ስነ ልቦናዊ እና ቴክኒካዊ ቦታ ይህ እንደ ሆነ አሰልጣኝ ኒስካነን በውል ተረድቶታል። ታዲያ ለማሸነፍም አትሌቶች ከዚህ ቦታ ሲደርሱ ፍጥነታቸውን መጨመር ግድ እንደሚላቸው፤ ከተፎካካሪዎቻቸውም ተነጥለው መውጣት እንዳለባቸው በአሰልጣኙ ተደጋግሞ ተነገሯቸዋል።
አበበ ዋቅጅራ ከፊቱ የቆመውን የአክሱም ሀውልት እየተመለከተ ለኢትዮጵያ ክብር ሲሉ እንደሚዋደቁ ተናገረ። አሰልጣኝ ኒስካነን ለሀገራቸው ክብር የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ በማመን አበበ ቢቂላን ስለሚጫማው ጫማ ጠየቀው። ሻምበል አበበ ቢቂላም ጫማው እንዳልተመቸው እና በባዶ እግሩ ለመሮጥ ማሰቡን ከብዙ ማብራሪያ ጋር አስረድቷል።
የአበበ በባዶ እግር መሮጥ እንግዳ ባይሆንም የሮምን ጥቁር አስፋልት እግሩ እንዲለምደው፤ በሮም ጎዳናዎች በባዶ እግሩ ልምምዶችን በማድረግ የዕለቱን ልምምድ አጠናቋል። አመሻሽ ላይ ስዊድናዊው አሰልጣኝ ወደ ኦሎምፒክ ሰፈር በማቅናት ጋዜጦችን በማንበብ መረጃ ለመሰብሰብ ሞክሯል። በርካታ የጣሊያን ጋዜጦች የድግሱ አጋፋሪ ሀገር በብስክሌት ውድድር ብዙ ሜዳሊያዎችን ማግኘቷን ኒስካነን አነበቡ።
በኢትዮጵያ ይህን ዜና የሰሙት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የብስክሌት ተወዳዳሪዎቹ ውጤት ባለማምጣታቸው ቅር ተሰኝተዋል። አሁን የቀረው ብቸኛው የሜዳሊያ ተስፋ የማራቶን ውድድር ነው። ይህ ደግሞ በአበበ ቢቂላ እና አበበ ዋቅጅራ ትክሻ ላይ አርፏል። ሰዓቱ ሲቃረብ አበበ ቢቂላ መጨነቅ ጀምሯል። ቀደም ብሎ ማይክ በተባለው አሜሪካዊ ስፖርተኛ የተነገረው አሉባልታ ከሻምበል አበበ ቢቂላ አዕምሮ ሊጠፋ አልቻለም።
አበበ ፍርሀቱ እየጨመረ ሲመጣ በአሜሪካዊው ስፖርተኛ ማይክ የተነገረው ወሬ እውነት ስለመሆኑ አሰልጣኙን ይጠይቃል። ኦኒ ኒስካነንም በእርግጥ እውነት መሆኑን በመናገር ከኢትዮጵያውያን ግን የሚያሸንፍ እንጂ የሚሞት አለመኖሩን በማስረዳት ፍርሀቱ እንዲገፈፍ በማድረግ ወደ መወዳደሪያ ቦታ እንዲያቀና አድርገዋል።
በመጨረሻም ከ37 ሀገራት የተውጣጡ ተወዳዳሪዎች ፉክክሩን ለመጀመር ተደርድረዋል። በመወዳደሪያው መም የተደረደሩት አትሌቶች የአበበን ባዶ እግር ከተመለከቱ በኋላ ዐስር ኪሎ ሜትር እንኳ እንደማይሮጥ በማሰብ ተሳልቀዋል፤ ተዘባብተዋል። ውድድሩ ሲጀመር በአበበ የተሳለቁት እነዚያ በርካታ አትሌቶች ግን ከ45 ደቂቃ በኋላ መበታተን ጀምረዋል። ቀደም ብሎ በአሰልጣኝ ኒስካነን ጠንካራነታቸው የተነገረላቸው የሶቪየት፣ የሞሮኮ እና የአውስትራሊያ አትሌቶች ግን ተፈራርተው አሁንም ጎን ለጎን መሮጣቸውን ቀጥለዋል።
ሻምበል አበበ ምንም እንኳ በግልጽ ማንነታቸውን መለየት ባይችልም ከእነርሱ ግን አልራቀም ነበር። እንዲያውም ጣሊያናውያን በተኙበት በዚያ በውድቅት ሌሊት አበበ ቢቂላ በሮም ጎዳናዎች የሚሮጥ ሳይሆን የሚንሳፈፍ ይመስል ነበር ይላል- ጽሑፉ። አሁን ውድድሩ በመገባደድ ላይ ይገኛል፤ ርቀቱም ዐስር ኪሎ ሜትር ብቻ ይቀራል:: አሰልጣኝ ኒስካነን፣ አቶ ይድነቃቸው እና ጋዜጠኛ ፍቅሩም ፍጥነቱን እንዲጨምር ከኋላ እየተከተሉ ቢጠይቁትም የተባለውን ባለማድረጉ እንደ ደከመው በማሰብ ተስፋ ቆርጠው ነበር ይላል- ጹሑፉ።
በሮም አደባባይ የአክሱም ሀውልት ካለበት ሲደርስ ዘራፊዎቹን በምድራቸው ለመበቀል ከኋላ የሚከተለው የእግር ኮቴ አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ዞሮ በማየት ፍጥነቱን ጨምሯል። ከዚያም ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን አዲስ የድል ብስራት የተሰማበት የድል ዜና በሮም ጎዳናዎች በዚህ መልኩ ተፈጽሟል። አበበ 42 ኪሎ ሜትሩን ለማጠናቀቅ ሁለት ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ ከሁለት ማይኮሮ ሴከንድ ነበር የፈጀበት። ይህም አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ነበር።
የውድድሩን የመጨረሻ መስመር ካለፈ በኋላ እንደ ሌሎች አትሌቶች ተዝለፍልፎ ይወድቃል ተብሎ የተጠበቀው ኢትዮጵያዊው ጀግና ሰውነቱን ለማቀዝቀዝ ልምምድ ሲሠራ መታየቱ ብዙዎቹን አስገርሟል። ጋዜጠኞችም ምድራዊ ሳይሆን ከሌላ ፕላኔት የመጣ ፍጡር ነው እስከማለት ደርሰዋል። በድርጊቱ የተገረሙ እና የተደነቁ ጋዜጠኞች “አልደከመህም ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ ያቀርቡለታል። አበበም ተጨማሪ 20 ኪሎ ሜትር መሮጥ የሚያስችል ጉልበት እንዳለው በመናገር ብዙዎችን አስደንቋል።
ውድድሩ ሌሊት በመከናወኑ ፉክክሩን ያልተመለከቱት ጣሊያናውያን ከእንቅልፋቸው ሲነሱ በሮም ጎዳናዎች አዲስ ታሪክ መሠራቱን ከመገናኛ አውታሮች አነበቡ፤ አደመጡ። በርካታ የጣሊያን የሕትመት ውጤቶች “ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር በርካታ ወታደሮችን አሰለፈች፤ ኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላ ግን በባዶ እግሩ ሮምን ወረረ” በማለት በፊት ገጾቻቸው አስነበቡ። አበበ ቢቂላ በዚህ መንገድ በዘመናት ሂደት የማይደበዝዝ ታሪክ ሠራ። በ1964 የሙኒክ ኦሎምፒክም ድሉን ደግሞታል። ሻምበል አበበ ስሙ ምንጊዜም ከመቃብር በላይ ቢሆንም ባጸደ ሥጋ ከዚህ ዓለም ከተለየ 50 ዓመታት ተቆጥረዋል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም