ሰላማችንን እናስፍን፤ ግብርናችንን እናዘምን!

0
166

ኢትዮጵያ ግብርና መር ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትን መከተል ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህንን የዕድገት ስልት ለመከተሏ ዋናው ምክንያትም  ሁሉንም ዓይነት ምርት ለማምረት የሚችል ለም መሬት ባለቤት መኾኗ ነው፡፡ ከሰማኒያ አምስት በመቶ  የሚልቀው ሕዝቧም ቢኾን መተዳደሪያውን በግብርና ላይ አድርጎ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ግብርና መር የልማት ስልትን ትከተላለች ሲባልም ከግብርናዉ ዘርፍ የሚገኘው ምርት  ኢንዱስትሪውን እየመገበ ምጣኔ ሀብቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ይሸጋገራል ማለት እንደኾነ የመስኩ ምሁራን ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ የግብርናው ዘርፍ ኢንዱስትሪውን ይመግብ ዘንድ ደግሞ ዘርፉን ማዘመን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደኾነ ይታመናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ግብርናው  በዘመናዊ የማምረቻ ዘዴዎች ሊታገዝ፣ ምርት እና ምርታማነትም ሊያድግ ይገባል፡፡

ምርት እና ምርታማነት ሲያድግ ኢንዱስትሪዎች የግብአት ችግር አይኖርባቸውም፡፡ ጥራት ያለው ግብአት፣ በተፈለገው ጊዜ እንዲሁም የጥራት ደረጃ ያገኛሉ፡፡ ባገኙት ግብአት ላይም እሴት ጨምረውበት ያመርታሉ፡፡ እሴት ተጨምሮበት የተመረተው ምርትም የውጪ ምንዛሬን ከማዳኑም በላይ የኢንዱስትሪ ዘርፉን እየመገበ ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን ይውላል፡፡ በዚህ መልኩ የግብርና ልማቱ ለኢንዱስትሪ ልማቱ  ምሶሶ ኾኖ እንዲያገለግል ማድረግ ይቻላል፡፡

ከዚህ እውነታ በመነሳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግብርና ልማቱ የኢንዱስትሪው መሠረት ኾኖ ያገለግል ዘንድ ትኩረት እየተሰጠ ነው፡፡ ላብነት ያህል የዱቄት ፋብሪካዎችን አጋጥሟቸው የነበረው የግብአት አቅርቦት ችግር ይቃለል ዘንድ በበጋ መስኖ ስንዴ ለማምረት ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

በበጋ መስኖ ስንዴን በማምረት ፋብሪካዎችን ለመመገብ የተሰጠው ትኩረት መልካም ቢሆንም ኢትዮጵያን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የምጣኔ ሀብት ዕድገት ለማሸጋገር ሁነኛ ሚና መጫዎት የሚችለው የግብርናው ዘርፍ ችግሮች ተጋርጠውበት ይገኛል፡፡ ከችግሮቹ አንዱ እና ዋነኛው ደግሞ የሰላም እጦት ነው፡፡ የሰላም እጦቱ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ግብአት በሚፈለገው ጥራት እና መጠን ለማምረት እንቅፋት ፈጥሯል፡፡  ለምርት እና ምርታማነት መጨመር የሚረዱ ግብአቶችን የማቅረቡን ሂደት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ሠራተኛውም እንደልቡ በመንቀሳቀስ በማምረት ተግባሩ እንዳይሳተፍ ገድቦት ይገኛል፡፡

በተለይም ምዕራብ ጎንደር ዞን የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎችን ሊመግቡ የሚችሉ እንደ ጥጥ፣ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር እና ሌሎችም የቅባት እህሎች የሚመረቱበት አካባቢ ነው፡፡  አካባቢው አምራች በመኾኑም ለበርካታ ወገኖች ጊዜያዊም ቢኾን የሥራ ዕድል ፈጥሮ ኖሯል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዚህ ዓመት በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ሥራ ፈላጊው ወገናችን ወደ አካባቢው መግባት አልቻለም፡፡ የሠራተኛው ወደ አካባቢው አለመግባት ደግሞ ምርት በወቅቱ እንዳይሰበሰብ እና  እንዲባክን ምክንያት ኾኗል፡፡ ከዚህም በላይ የሰላም መደፍረሱ እንደ ትራክተር፣ ኮምባይነር፣ የጭነት መኪና… ያሉ ለምርት መሰብሰቢያነት፣ መውቂያነት እንዲሁም ማጓጓዣነት  የሚያገለግሉ መሣሪያዎችንም ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀሱን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ በዚህ የተነሳም  ከብክነት የተረፈውን ምርት እንኳን ወደ ተፈለገበት ቦታ ለማጓጓዝ ወይም  ለሚፈልጉት ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ አልተቻለም፡፡

የሰላም መታጣቱ የግብርናው ዘርፍ በዘመናዊ የማምረቻ ዘዴዎች እንዳይታገዝ፣ ምርት እና ምርታማነት እንዳያድግ፣ የተመረተውም በወቅቱ ተሰብስቦ እንዳይጓጓዝ፣ ኢንዱስትሪዎች በግብአት እጥረት የተነሳ በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ ከማድረጉም ባለፈ ሀገርን በዕድገት እና ሥልጣኔ ጎዳና ለማራመድ የሚችለውን የሰው ሀብታችንን እያሳጣን ይገኛል፡፡

በጦርነት ውስጥ ኾኖ ስለልማት፣ ዕድገት እና ብልጽግና ማሰብ፣ ያሰቡትንም መተግበር አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ጦርነት ባለበት በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ ውሎ የማደር… ዋስትና የለም፡፡ ስጋት እና በጥርጣሬ  መተያየት የዕለት ከዕለት ክስተት ይሆናል፡፡ ስለሆነም  ከስጋት እና ጥርጣሬ ወጥተን ስለልማት እና ዕድገት ማሰብ፣ ያሰብነውን በመተግበር ግብርናችንን ማዘመን እንችል ዘንድ ሁላችንም የሰላም ዘብ ልንሆን እና ሰላማችንን ልናሰፍን ይገባል፡፡

(አባትሁን ዘገየ)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here