ኢትዮጵያ በታሪኳ ያጋጠሟትን ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎችን እየመከተች ለዓለም የሰላም ተምሳሌት ሆና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቆይታለች:: “ዛሬ በታሪክ ያ ሩቅ ድረስ ይሸት የነበረው የሰላም ስማችን እየጎደፈ መጥቶ የርስ በርስ ግጭት ውስጥ ገብተናል፤ እኛ እኮ በጥንቱ ዘመን የስደተኛ መጠለያ ሆነን ነበር፣ አሁን ግን ራሱ ነው ለራሱ ሕዝብ የስደተኛ ሰፈር የፈጠረው” በማለት ኢትዮጵያ የገባችበገትን አሁናዊ የሰላም መታጣት አሳሳቢነት የተናገሩት በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ መሠረት ወርቁ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ከበኲር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው::
በእርግጥም ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ ውስጣዊ ችግሮች ነበሩባት፤ ሁሉም ግን በወቅቱ በነበሩ የመሪዎች ጥበብ፣ አርቆ አስተዋይነት ታልፎ ሀገር እንደ ሀገር ቀጥላ ዛሬ ላይ ደርሳለች:: ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ እንደ ጥንቱ አይደለችም፤ በከፍተኛ የዕድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች:: የትናንቱ የርስ በርስ ግጭት አዙሪት ግን ዛሬም እንደ አዲስ አገርሽቶ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች ቀጥለዋል:: ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ የፖለቲካ ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረጉ ጥረቶች፣ የተደራረቡ የሕዝብ ጥያቄዎች መኖር ሀገሪቱ አሁን የገባችበት ቀውስ መልኮች ናቸው:: እነዚህም ግጭቶች የህዝብ ለሕዝብ መስተጋብር እንዲላላ በማድረግ ሀገራዊ አንድነት ላይ አደጋ እንዳይደቅኑ ስጋት አለ:: ታዲያ መንግሥት ይህንን ስጋት ለመቀልበስ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሕግ ማስከበር ሥራ እየሠራ ይገኛል:: የሰሜኑ ጦርነት በሰላም ስምምነት ተቋጭቶ ለጊዜው ሕዝቡ የሰላም አየር እየተነፈሰ ባለበት በዚህ ወቅት በአማራ ክልል እና በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች ቀጥለዋል::
ጦርነቶች እና ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የልማት ሥራዎች በሚፈለገው አግባብ እየተከናወኑ አይደለም:: መንገዶች በተደጋጋሚ ይዘጋሉ:: ይህም በምርት አቅርቦት ላይ ጫና በመፍጠር የዋጋ ንረት የዜጎች ፈተና እንዲሆን፣ ዜጎች ፈጣን የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ አድርገዋል:: በአማራ ክልል ባለፉት ሰላም በታጣባቸው ወቅቶች የታየውም ይህንኑ እውነታ ነው::
ኢትዮጵያ ችግሮቿን እንደ ትናንቱ በሰከነ መንገድ ፈታ እንዴት ለዜጎቿ የተመቸች ትሁን የሚለው ገዥ ጉዳይ ሆኖ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል:: የአማራ ክልል ባለፈው አንድ ዓመት ያጋጠመው የሰላም እና ደኅንነት ችግር በቀጣዩ ዓመትም እንዳይቀጥል ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለታጣቂ ኅይሎች የሰላም ጥሪዎችን ከማድረግ ጀምሮ ሕዝባዊ ውይይቶችን ተደርገዋል፤ እየተደረገም ይገኛል:: ይህም ክልሉን ወደ አንጻራዊ ሰላም በማሸጋገር የልማት ሥራዎች እንዲጀመሩ እና እንዲጠናቀቁ እያደረገ መሆኑን የክልሉ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ማስታወቁ የሚታወስ ነው::
ክልሉን ወደተሟላ የሰላም ሁኔታ መመለስ ግን ዋናው ቀሪ ሥራ ሆኖ እየተሠራበት እንደሚገኝም ተመላክቷል:: ለዚህም መንግሥትን እና የፋኖ ኀይሎችን በማቀራረብ ችግሩን በድርድር ለመፍታት የሚያስችል አመቻች የሰላም ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል:: የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ሰብሳቢ ያየህራድ በለጠ በትግል ላይ ያሉ ወገኖች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እና ድርድር በመፍታት ክልሉ ከቀውስ እንዲወጣ ለማድረግ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል:: ችግሩን በድርድር እና ንግግር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ይሳካል የሚል እምነት እንዳላቸው ሰብሳቢው ገልጸዋል:: የፌደራል መንግሥቱም ለጥረቱ ዕውቅና ሰጥቶ መግለጫ እንዲያወጣ ካውንስሉ በግልጽ ጥሪ ማቅረቡንም ሰብሳቢው ገልጸዋል::
ካውንስሉ ገለልተኛ ሆኖ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ ተፈትተው ሕዝቡ የሰላም አየር እንዲያገኝ እየሠራ የሚገኝ በመሆኑ በትግል ላይ ያሉ ወገኖች በካውንስሉ ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖራቸው ጠይቀዋል:: ታጣቂ ኀይሉ ካውንስሉ ለመንግሥት የወገነ ነው ብሎ የሚያምን ከሆነ ራሳቸው ያመኑበትን አመቻች ወደ ካውንስሉ ማካተት እንደሚችሉ በሩ ክፍት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል:: ከዚህ ውጭ እየተደረገ ያለው አካሄድ ግን ድርድሩ ስኬታማ እንዳይሆን መሰናክል የሚፈጥር በመሆኑ የፋኖ ኀይሎች በብልጠት እንዲረዱት እና እንዲመረምሩት ጠይቀዋል::
በአጠቃላይ ሕዝቡ ስለ ሰላም በማወጅ ሁሉም ወገን ወደ ድርድር እንዲመጣ አወንታዊ ጫና እንዲያሳርፍ ሰብሳቢው ጥሪ አቅርበዋል::
እንደ ሀገር ያለውን አለመግባባት በመፍታት ሀገራዊ አንድነትን ለማምጣት ደግሞ የሽግግር ፍትህ እና ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ሰንበትበት ብሏል:: እስካሁን ምላሽ ያላገኙ እና በሕዝብ መካከል መከፋፈል የፈጠሩ ጉዳዮችን መስመር በማስያዝ ቀጣይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ምክክር ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ያስታወቁት ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የእርቀ ሰላም ባለሙያ እና አማካሪ ጋረደው አሰፋ ናቸው::
ድርድር ከጦርነት እና ወደ ጦርነት ከሚወስድ ውዝግብ ለመውጣት የሚደረግ የሰጥቶ መቀበል መርህን የሚከተል የሰላም ሂደት መሆኑንም አንስተዋል:: የድርድር ሂደት ጦርነትን በማቆም ወደ ተሻለ ሰላም መመለስ እና ዳግም ወደ ጦርነት ላለመግባት ስምምነት ማድረግን ያጠቃልላል::
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ልዩነቶችን በምክክር በመፍታት ሀገራዊ ሰላምን ማረጋገጥ ዋናው ጉዳይ ሊሆን ይገባል:: ሀገራዊ ምክክሩ ሀገር እና ሕዝብ የሚካስበት፣ ሁሉም የሚያሸንፉበት፣ የተደበቀው እውነት ገሀድ ወጥቶ ዘላቂ ሰላም የሚገነባበት እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል:: በዚህ ሂደት ውስጣዊ ችግሮቻቸውን በንግግር ቋጭተው በአሁኑ ወቅት በሰላም እየኖሩ ያሉ ሀገራት ሲኖሩ፣ አንዳንዶች ደግሞ ጅምራቸው ከሽፎባቸው ሀገር እስከመበተን ደርሷል::
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ ሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዚያ፣ ቤኒን፣ ኬኒያ፣ ሩዋንዳ እና ሌሎችንም በምክክር ሂደት ስኬታማ የሆኑ ስለመሆናቸው ያነሳሉ:: የምክክር ሂደቱ ከየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነት ነጻ መሆኑ ከመሆኑም ባለፈ ምክክሩ በሀገር ልጆች መመራቱ እና የሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ተሳትፎ የተንጸባረቀበት በመሆኑ በስኬታማነት እንዲጠቀስ ማስቻሉን አንስተዋል::
ልዩነቶቻቸውን በሀገራዊ ምክክር ቋጭተው ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የጀመሩ፣ ነገር ግን የከሸፈባቸው ሀገራት ስለመኖራቸውም ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል:: ለአብነትም የመንን ያነሳሉ:: የየመን ሀገራዊ የምክክር ሂደት ባለቤቶቹ የመናዊያን ሳይሆኑ ሳውዲ አረቢያ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ የሚዘውሩት ስለነበር ሳይሳካ እንደቀረ ጠቁመዋል::
ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለው የምክክር ሂደት ከየትኛውም ኀይል እና ቡድን ተፅዕኖ ነጻ ሆኖ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል:: “ጦርነትን የመሠራት ችሎታው ካለን፤ ሰላምንም የመሥራት ችሎታው አለን” ያሉት ዮናስ (ዶ/ር) በየትኛውም የትግል መስክ የሚገኙ ወገኖች ወደ ምክክር እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል::
እኛም እንላለን፤ ባለፈው አንድ ዓመት ያጋጠመውን የሰላም እና ደኅንነት መናጋት ችግር ሕዝብን አስቀድሞ ወደ ንግግር እና ድርድር በመምጣት ለሕዝብ ወገንተኝነትን ማረጋገጥ ይገባል:: በመሆኑም በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኅይሎች መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በቀናነት በመቀበል፣ መንግሥትም ለድርድር ያሳየውን ፍላጎት አጠናክሮ በመቀጠል ሕዝብን ከደኅንነት ስጋት መታደግ ይገባል:: ሁለቱም ወገን አሁናዊ ሙሉ ትኩረታቸውን ከግጭት እንዴት ወጥቶ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል? የሚለውን በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማት መሸጋገር ተገቢ ነው::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም