ላለፉት ሁለት ዓመታት በአማራ ክልል የተካሄደው እና አሁንም የቀጠለው ግጭት ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፤ እያደረሰም ይገኛል፡፡ በርካታ ሰዎች ሕይዎታቸውን አጥተዋል፤ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በግለሰቦች ላይ የሚፈጸም እገታን ጨምሮ ወንጀል ተስፋፍቷል፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት አጋጥሟል፤ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ሌሎች መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፤ ለልማት የሚውለው ሀብት ለግጭት ውሏል፤ ቀድመው ተይዘው የነበሩ አንዳንድ ፕሮጀክቶች በወቅቱ እንዳይጠናቀቁ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችም እንዳይጀመሩ ግጭቱ ምክንያት ሆኗል፡፡
በግጭቱ ምክንያት ሰው እንደልቡ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ተቸግሯል፡፡ በተለይም አርሶ አደሩ በስፋት ለማምረት እና ያመረተውን ገበያ እንዳያቀርብ ግጭቱ ምክንያት በመሆኑ አርሶ አደሩ በምርቱ ተጠቃሚ ካለመሆኑም በላይ የኑሮ ውድነቱ ሌላ ጫና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የመማር ማስተማሩ ሂደት በእጅጉ ተስተጓጉሏል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ተምረው ቀጣዩን የክፍል ደረጃ መድረስ ሲገባቸው ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ተተኪ ትውልድ በሚፈለገው ደረጃ ማፍራት አልተቻለም፡፡ በግጭቱ ምክንያት የአማራ ሕዝብ ነባር እሴቶችም ቢሆኑ እየተሸረሸሩ ነው:: የጤና አገልግሎት አሰጣጡ ተፈትኗል፤ እንደ ኮሌራ እና ወባ ያሉ የማኅበረሰብ የጤና ችግሮችን ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኗል፡፡ የሰላም ችግሩ የክልሉ ሕዝብ ማኅበራዊ መስተጋብሩም እንዲላላ ምክንያት ሆኗል፡፡
ይህም ሆኖ መንግሥት በየጊዜው የሚገኘውን አንጻራዊ ሰላም እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም የልማት ሥራዎችን ጀምሮ እያጠናቀቀ ነው፡፡ ከብዙ የልማት ሥራዎች መካከልም የኮሪደር ልማቱ ተጠቃሽ ነው፡፡
ከልማቱ ጎን ለጎን ስለ ሰላም የሚደረጉ ውይይቶች እና ምክክሮች ቀጥለዋል፡፡ ግጭቱን ለማስቆም፣ ብሎም በግጭቱ ምክንያት የተከሰቱትን እና እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረጉ ምክክሮች ሁነኛ አማራጮች መሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ መንግሥትም ለክልሉ ከግጭት አዙሪት የመውጫ መንገዱ ውይይት እና ድርድር መሆኑን በማጤን ሰላም ይሰፍን ዘንድ ሲሠራ ቆይቷል፡፡
ግጭቱ ካስከተላቸው ፈርጀ ብዙ ችግሮች አንጻር ባሁኑ ወቅት ክልሉን ወደቀደመ የሰላም ሁኔታው ከመመለስ የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ የለም፡፡ የአማራ ክልል ምክር ቤትም በ6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባዔው ያረጋገጠው ይሄንኑ ነው፡፡ ውይይት እና ምክክር ብቸኛው ከግጭት የመውጫ መንገድ መሆኑን ተገንዝቦ ሁሉም ችግሩን በውይይት እና ምክክር ለመፍታት መረባረብ ይኖርበታል፡፡
እየተሻሻለ የመጣውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ እና ሕዝብ የሚፈልገውን በሰላም ወጥቶ የመግባት ፍላጎት ለማሳካት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡ መሪዎች ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅተው መሥራት እና የተጀመሩ ሕዝባዊ ውይይቶችን ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕዝቡም ለሰላሙ መረጋገጥ ባለቤቱ መሆኑን ዐውቆ በተጀመሩት ሕዝባዊ ውይይቶች በንቃት መሳተፍ ይኖርበታል፡፡ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከሚደረግ ጥረት ጎን ለጎን የመልሶ ግንባታ ሥራን በትኩረት ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ ፡፡
በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም