ሰላምን ለማስፈን ጥሪ ቀረበ

0
169

የአማራ ክልል ያለፈውን አንድ ዓመት በግጭት ውስጥ አልፏል:: በዚህም ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ ጉዳት መድረሱን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም ማስታወቁ ይታወሳል:: ሰብዓዊ ኪሳራው እና ማኅበራዊ ጉዳቱም ከፍተኛ ሆኖ ይነሳል::

ግጭቱ በክልሉ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለው መጠነ ሰፊ ጉዳት እንዲያበቃ የአማራ ክልል መንግሥት የሰላም ካውንስል በማቋቋም ችግሩን በውይይት እና ድርድር ለመፍታት ጥሪ አቅርቧል::

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደበት ወቅት መንግሥት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት ምን እንደሆነ በምክር ቤት አባላት ተጠይቋል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ትግል የሥልጣን መቀያየር ሳይሆን ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት በመስጠት አንስተዋል::

በኢትዮጵያ አሁናዊ ጉዞ ነባር እና ወቅታዊ  ችግሮች ፈተና እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል:: ከጥንት የመጡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ታሪካዊ ነባር ችግሮች መሆናቸውን ሲያነሱ ምጣኔ ሃብታዊ ስብራትን ወቅታዊ ችግር በማለት ገልጸዋል::

ጦርነት መጀመር በጣም ቀላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር ግን ጦርነት አቁሞ ወደ ምክክር ለመምጣት እንኳ ብዙ ሰብዓዊ ኪሳራ ካስተናገደ በኋላ ነው ብለዋል:: በመሆኑም ሰላማዊ ትግልን ማስቀደም እንደሚገባ ጠቁመዋል::

መንግሥት አሁንም ለሰላም የሚከፈል ማንኛውንም ዋጋ በመክፈል ግጭቶችን ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል:: ለምን “ከሰላም ውጭ ያለው አማራጭ ዋጋ የለውም ብለዋል:: የጋራ ሀገር ነው፣ አንድ እንሁን፣ በጋራ እናልማ በምርጫ በውይይት እንመን” ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።

ነባር ችግሮችን ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን የገለጹት ዶ/ር ዐቢይ ልዩነቶችን በምክክር እና በውይይት መፍታት እንደ ሀገር ብዙ አትራፊ እንደሚያደርግ ገልጸዋል:: የትናንቱን ጉዳይ ለመዝጋት ደግሞ የሽግግር ፍትሕ እንዲኖር እንሥራ፣ ተቋማትን፣ ሕግጋትን እናሻሽል በሚል እየተሠራ ነው ብለዋል።

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here