መነጋገርንና መወያየትን ቅድሚያ በመስጠት አትራፊውን መንገድ መከተል መሸነፍ ሳይሆን ለሰላም ዋጋ መስጠትና የህዝብን ህልውና ማስቀደም ነው፤ ከህዝባዊ ውይይቶች የሚገኙ ግብዓቶች ሀገርን ያተርፋሉ፡፡ ከመነጋገር አልፎ መደማመጥ፣ ህዝባዊ ውይይቶችን ለሰላም መስፈን መጠቀም እንደ ሀገር አትራፊና አዋጭ መንገድ ነው፡፡
ሁልጊዜም ቢሆን ጦርነት ካለ ሞት፣ ጦርነት ካለ መፈናቀል፣ ጦርነት ካለ ስደት፣ ጦርነት ካለ ረሃብ አለ። ከቁሳዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳቱ ባሻገር ጊዜያዊ፣ ዘላቂና ቋሚ የሆነ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳትን አስከትሎ ማለፉ የምንጊዜም ሀቅ ነው።
ጦርነት በቅጽበት እውነት የነበረውን ሕይወት ህልምም ተረትም የሚያደርግ ክስተት ነው፡፡
እለት እለት ይህን እያየን የንግግርንና የሰላምን ዋጋ የምንረዳው እንደውሀ ሙላት እያሳሳቀ ከነበርንበት ወዳልነበርንበት ካደረሰን በኋላ መሆኑ ዛሬም ድረስ የሚያሳዝን ነው፡፡ የሰላምን ዋጋ በማቅለል ለጦርነት ከምናወጣው ሃይል፣ በጀትና አቅም ትንሹን ለመደማማጥ፣ ለሰላም ባለማዋላችን፣ ለጦርነት የምንሄደውን ሩቅ መንገድ ትተን አጭሩን መንገድ ተጉዘን ለሰላም ለማዋል ፍላጎት ባለማሳየታችን ዛሬም ድረስ ዋጋ እየከፈልን ነው፡፡
ሁሉም አስከፊ ጦርነቶች በውይይት ነው የተቋጩት፡፡ ነገር ግን ጦርነት ትቶት ከሚሄደው ዳፋ አንዱ ከአንዱ ትምህርት ባለመውሰዱ ሁሉም በዙር ዋጋ እየከፈለ ይኖራል፡፡ በየዘመኑ ትውልድ ካለፈው ቁርሾ እያጣቀሰ እንደመልካም ነገር የየራሱን የጥፋት አሻራ ለማስቀመጥ ሲሽቀዳደም ማየት የዓለማችን ሌላኛው መልክ እየሆነ እየቀጠለ ነው።
ከሁሉም ጦርነቶች ማግስት የምንሰማው ጸጸትና ባልነበር የሚል ቁጭትን ነው፡፡ ከጦርነት ተርፎን የምናወራው ታሪክ የብዙዎች ልብ የተሰበረበትና የደማበት፣ ወደፊት የሄድነውን ያህል በእጥፍ ወደኋላ የምንመለስበት፣ ቤትና ቤተሰብ የሚፈርስበት ሰው መሆን የሚፈተንበት ከባዱ የህይወት ፈተና ነው።
ሰላምን እስካመጣ ድረስ ከግማሽ በላይ መንገድ እንኳ ቢሆን ሄደን ችግርን በስክነት፣ ከእልህ በዘለለና መፍትሔ ባለው መልኩ መነጋገር ትውልድን የማዳን ኃላፊነትንም መወጣት ለምን አቃተን?
ከሰሞኑ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን አላማ ያደረገ ሕዝባዊ ውይይት ባካሄደበት ወቅት ግጭቱ እያስከፈለ ስላለው መጠነ ሰፊ ቀውስ እና የሰላም መንገዶች ተመላክተውበታል፡፡
የሰላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና የመልማት ጥያቄ ያለባት ሀገር ሆና እያለ ይህንን ጥያቄ በትጥቅ ትግል ለማስመለስ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሀገርን ትርፋማ እንደማያደርግ ገልጸዋል፡፡ በሰላማዊ መንገድ ችግርን መፍታት አትራፊ የሚያደርገው ሀገርን ነው፡፡ በትጥቅ ትግል ፍላጎትን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ አካላትም ሆኑ መንግሥትም ችግሩን በኅይል ለመቀልበስ በሚያደርገው ጥረት አትራፊ አይሆኑም፡፡ የትጥቅ ትግል በሚደረግባቸው አካባቢዎች የሚኖረውን ሕዝብም ለከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ ከመዳረግ ያለፈ ትርጉም እንደማያመጣም ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት የትጥቅ ትግል እያስከተለ ያለውን መጠነ ሰፊ ሁለንተናዊ ኪሳራ በመታደግ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ለማስፈን ዝግጁነቱን በተደጋጋሚ እያስታወቀ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም የትጥቅ ትግል መሰረተ ልማት ላይ ውድመት በማድረስ ሕዝብን ለከፋ ጉዳት እየዳረገ ነው በማለት ሰላምን አማራጭ አድርገው ለመጡ አካላት ምስጋና አቅርበው ሌሎችም ሰላማዊ ትግልን ቀዳሚ ምርጫቸው ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ብዙዎችን በሞት ከጎናችን አጥተናል፡፡ ብዙዎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ለረሃብና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡ እንደ ሩዋንዳ ዓይነት ሀገራት “እኔን ያየ ይቀጣ” እያሉ ዓለምን ለሰላም እየሰበኩና ወደልማት ገብተው ባሉበት በዚህ ወቅት የሰላምን ዋጋ እኩል መረዳት ባለመቻላችን ዋጋ እየከፈልን ነው፡፡
እንደኛ ዓይነት ሀገር ያውም ሀገር በቀል የእርቅ፤ የሽምግልናና ችግርን የመፍቻ መንገድ ያለው፣ ጥንታዊና ታሪካዊ ሀገር የራስን ጸብ በራስ ለማርገብ ባለመቻላችን ዛሬም የበርካቶች ህይወት በሚገበርበት ግጭት ውስጥ ሆነን ዋጋ እንከፍላለን፡፡
ሩዋንዳውያን ችግራቸውን ዳግም እንዳይመለስ በእርቅና በይቅር ባይነት ዘግተዋል፡፡ እኛም ችግራችንን በንግግርና በውይይት ፈተን ወደ ልማትና ወደ ሰላም መመለስ አለብን!
በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም