አማራ ክልል በነፍጥ ከታገዘ ግጭት ጋር አንድ ዓመት ያህል መክረሙ ክልሉን ወደ ውስብስብ ምስቅልቅሎሽ እንዲገባ አድርጓል፡፡ ህጻናት ተረጋግተው እንዳይማሩ፣ እናቶች እንዳይታከሙ፣ መሥራት የሚችሉ እጆች እንዳይሠሩ መሰናክል ተፈጥሯል፡፡ ይህንኑ ችግር ለመፍታት ሲባልም ዜጎችን ከስጋት አላቅቆ ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ ግጭቱ በንግግር ወይም በድርድር እንዲፈታ ሰሞኑን አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ይህንን ተግባር ደግሞ የተቋቋመው የሰላም ካውንስል (የሰላም ምክርቤት) እንዲወጣ ሀላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ካውንስሉ ተደራዳሪ አካላትን አቀራራቢ እንጂ ራሱ አደራዳሪ አለመሆኑንም በይፋ ገልጻል፡፡ በመንግሥት እና ተፋላሚ ወገኖች መካከል መቀራረብ ተፈጥሮ ግጭቱ በንግግር እንዲፈታ ካውንስሉ ያቀረበውን ጥሪ እንደ በጎ ጅምር በማየት ሁሉም ወገን በድርድር ሰላምን ለማስፈን መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ያ ሲሆን ሰላምን በሰላም ማምጣት ይቻላል፡፡
ሰላም በሰላም እንዲመጣ የየትኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ መሻት ነው። የትኛውም ሰዋዊ ፍጡር ጦርነት፣ ግጭት፣ ትርምስ፣ ሁከት ምቾት ሊሰጠው አይችልም። ሰላምን በሰላም ለማምጣት ወርቃማው መንገድ እውነተኛ ውይይት፣ ንግግር፣ ድርድር፣ እርቅ መሆናቸው ግልፅ ነው። ለዚህ ደግሞ መደማመጥ እና መግባባት ያስፈልጋል። ጫፍ ከያዘ አቋም ወደመሃሉ በመምጣት በለዘበ አካሄድ መቀራረብ ተገቢነት አለው።
ማዶ እና ማዶ ሆኖ ድንጋይ ከመወራወር፣ በሚወረወረው ድንጋይ ድልድይ ሰርቶ ወንዙን መሻገር፣ በጋራ አብሮ መጓዝ እና ረጅም ሕልምን ማሳካት ይቻላል። ካለንግግር መግባባት፣ ካለውይይት መረዳዳትን ማምጣት ስለማይቻል ለውይይት ሁሉም ወገን ልቡን ከፍቶ መቀራረብ ይኖርበታል።
ካለውይይት እና ንግግር መግባባት “አፍን ዘግቶ ፉጨት” ስለሚሆን የእውነቱን መንገድ መከተል ተገቢ ነው። ነባራዊ ሁኔታዎችን መገምገም፣ ለሕዝብ የሚጠቅመውን መምረጥ እና ለነገ የተመቸውን መስመር ይዞ መንቀሳቀስ ቀጠሮ የማይሰጠው ተግባር መሆንም ይኖርበታል። ከመፈራረጅ በመነጋገር መግባባት፣ ድንጋይ ከመወራወሩ በድንጋዩ ጡብ መሥራት የብልሆች ምርጫ ነው።
ግጭት ፣ ጦርነት፣ ሁከት ሕዝቡን ሰልችቶታል። ሰላም ሰላም የማይል ሕዝብ የለም። ለሕዝብ መሻቱን እንዲያገኝ ሰላምን በሰላም እንቀበለው። የሰላም ጊዜው አሁን ነው፤ እናም በሰላም እንድንኖር ለሰላም እንስራ። ሰላም በተናጠል ሳይሆን በጋራ ፍላጎት የሚመጣ የልፋት ውጤት በመሆኑ ሁሉም ወገን እጁን ለሰላም፣ ልቡን ለውይይት ይክፈት።ሰላም የጠቢበኞች ምርጫ ነው። ሰላም የተስፋ እና ስኬት ዋስትና ነው፡፡
በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም