ሰላምን በውይይት

0
192

ከጥንት እስከ ዛሬ በርካታ የዓለም ሀገራት በግጭት እና በጦርነት ውስጥ አልፈዋል፤ እያለፉም ይገኛሉ:: ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ ሩዋንዳ (ማንነትን መሠረት ያደረገ የዘር ፍጅት)፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዚያ… በከፋ ቀውስ ውስጥ ያለፉ ሀገራት ናቸው:: አንዳንድ ሀገራት  ችግሮቻቸው ስር ሰዶ የከፋ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ምስቅልቅል ሳያስከትል ሰላምን በውይይት መልሰዋል፤ “የዓለም ሕዝብ የሰላም ጠበቃ ነን!“ እስከ ማለትም ደርሰዋል::

ለአብነት እ.አ.አ ከ1948 እስከ 1989 ተፈጥሮ የነበረው የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት በሺህ የሚቆጠሩትን ለሕልፈት ዳርጓል፤ ከሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ወገኖችንም ለስደት አስገድዷል:: ይሁን እንጂ ለቀውስ ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ችግሮች ቀድመው በመለየት ለመፍትሔው ቁጭ ብለው መነጋገርን አስቀደሙ፤ ዘላቂ ሰላምን አሰፈኑ፣ ዛሬ በምጣኔ ሐብት የአፍሪካ ተምሳሌት ለመሆን በቅተዋል::

ቱኒዚያ እና የመንም አጋጥሟቸው የነበረውን ፖለቲካዊ ውጥረት እና የሰላም መናጋት በብሄራዊ ምክክር ለመፍታት ጥረት አድርገዋል:: የምክክር ሂደቱ የውጭ ጣልቃ ገብነት የነበረበት መሆኑ እና የአጀንዳ ልየታውም የተመጠነ አለመሆኑ ግን ሰላምን በንግግር ለማስመር ያደረጉት ጥረት በዘላቂነት እንዳይሰምር ማድረጉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ተቋም መረጃ ያመለክታል:: ጠንካራ፣ ገለልተኛ እና የሀገር ሉዓላዊነትን ያስቀደመ ተቋም አለመኖር የውጭ ጣልቃ ገብነቱ ሥር ሰዶ የሰላም ጥረቱን አደናቅፎታል የሚሉ መላምቶች ይስተጋባሉ::

በቀውስ ውስጥ የነበሩ የዓለም ሀገራት እንዴት ከሰላም መናጋት ወጥተው ዛሬ ላይ አስተማማኝ ሰላም እንደፈጠሩ ማንሳታችን ያለምክንያት አይደለም:: ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰላም ማጣት ውስጥ ትገኛለችና:: ግሎባል ፋይናንስ መጽሄት (gfmag.com) በዓለም አስተማማኝ ሰላም ያሰፈኑ 10 ሀገራትን በጠቆመበት ሪፖርቱ ኢትዮጵያን በ151ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል:: አይስላንድ፣ ዴንማርክ፣ አየርላንድ፣ ኒውዚላድ፣ ኦስትሪያ፣ ሲንጋፖር፣ ፖርቹጋል፣ ስሎቬኒያ እና ስዊዘርላንድን የሰላም ተምሳሌት አድርጎ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ኢትዮጵያን በ151ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጣት ከ163 ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ነው::

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በይፋ ከተጀመረበት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሀገሪቱ የከፋ የሰላም መናጋት ውስጥ ትገኛለች:: ለዚህ ማረጋገጫው በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች መፍትሔ የራቃቸው በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች ናቸው:: በተጨማሪም የፌዴራል የደኅንነት እና የጋራ ግብረ ኀይል በየጊዜው በአዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢዎች በህቡዕ ጥቃት ለመሰንዘር አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖችን ተልዕኮ ማክሸፉን እያሳወቀ መሆኑ አሁንም በትጥቅ የታገዘ ግጭት የሀገሪቱ  ሰላም ስጋት ለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል::

የጸጥታ ችግሮች ዜጎች ሕገ መንግሥቱ ያጎናፀፋቸው መብት ተገፎ  በሀገራቸው የተለያዩ አካባቢዎች እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ አድርጓቸዋል:: ይህም በአንድም ይሁን በሌላ በሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብር እና በኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚፈጥር ይታመናል::

ታዲያ ዓመታትን ያለ መፍትሔ የተሻገረው ግጭት በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ዘላቂ የሰላም መፍትሔ እንዲሰጠው እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራት እና ሌሎች ሰብዓዊ መብት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ አካላት እየጠየቁ ነው:: በተለይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ጄማሲንጋ ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም  በኢትዮጵያ በትጥቅ ግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ወደ ንግግር በመምጣት ሰላምን እንዲያሰፍኑ ጠይቀዋል:: የኢትዮጵያ መንግሥትም የሀገሪቱን ችግሮች በኀይል ለመፍታት ከሚያደርገው ጥረት ወጥቶ በንግግር በመፍታት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት እንዲያስጠብቅ አምባሳደሩ ማሳሰባቸው ይታወሳል::

ከ2015 ዓ.ም ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ለመቆጣጠር መንግሥት ለአሥር ወራት የዘለቀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል:: አዋጁ ሊጠናቀቅ ሁለት ቀን ቢቀረውም አንጻራዊ ሰላም ከማስፈን ያለፈ ክልሉን ወደተሟላ የሰላም እንቅስቃሴ እንዳላሸጋገረው የክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ አስታውቋል::

በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ የኮማድ ፖስቱን ወቅታዊ ሁኔታ ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ገምግሟል:: የመርማሪ ቦርዱ ሰብሳቢ አቶ አዝመራ አንዴሞ የሕዝቡን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲቻል በመጀመሪያ የአካባቢው ሰላም እና ፀጥታ እንዲሁም የሕግ የበላይነት መረጋገጥ እንዳለበት መናገራቸውን ከምክር ቤቱ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ዋቢ ነው።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጋር ተወያይቷል:: የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ ለክልሉ ሰላም በትኩረት መሥራት እንደሚገባ፣ ለዚህም የጋራ ምክር ቤቱ አጀንዳ አድርጎ እንደመከረበት ተናግረዋል:: የፖለቲካ ፓርቲዎች ባላቸው ተደራሽነት ልክ ሕዝብን ለሰላም እንዲያነሳሱ፣ ራሳቸውም ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ጉዳዮች እንዲቆጠቡ፣ የትኛውም የፖለቲካ ልዩነት በውይይት እና በድርድር እንዲፈታ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል::

ሀገርን እንደ ሀገር ለማስቀጠል፣ የክልሉን ሰላምም በዘላቂነት መመለስ የሚቻለው ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ  በመፍታት እንደሆነ አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል:: ችግሮችን በውይይት የመፍታት ልምዱ አናሳ መሆኑ ግን ሕዝቡን ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለው በመሆኑ ለውይይት ምቹ  ሁኔታዎችን መግፋት የሠለጠነ የፖለቲካ አካሄድ አለመሆኑን ጠቁመው፣ ዕድሎችን መጠቀም እንደሚገባም መክረዋል::

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም ከኢቲቪ ወቅታዊ ፕሮግራም ጋር ቆይታ አድርገዋል:: በቆይታቸውም ክልሉ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ ከፍተኛ  ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት ማድረሱን አስታውሰዋል:: በክልሉ ሕዝብ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ትኩረት በተሰጠበት ወቅት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር 148 ትራንስፎርመሮች እና መብራት አስተላላፊ ምሰሶዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጉን ለአብነት አንስተዋል::

የሰላም ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱንም በዚህ ወቅት ገልጸዋል:: ለጸጥታ ችግሩ መፈጠር ገዥ ምክንያት ናቸው የተባሉ የሕዝብ ጥያቄዎች ታውቀው ያደሩ መሆኑን ጠቁመዋል:: የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘት፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻል፣ የተዛባ ትርክት ማረም፣ ኢፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት እና ሌሎችን ለችግሩ ምክንያት ሆነው ከሕዝብ በኩል የሚነሱ ጉዳዮች መሆናቸውን አስምረውበታል::

“የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት በትጥቅ በታገዘ አካሄድ አይደለም“ ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፣ መንግሥት ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ በተጠና መንገድ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል:: በተለይ እንደ ሀገር ተጎጂ እያደረገ ያለውን የተዛባ ትርክት ፈጥኖ ማረም፣ አዳዲስ የተዛቡ ተርክቶች እንዳይፈጠሩም መጠንቀቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል:: ከዚህ ቀደም የነበረውን የተዛበ ትርክት ለማረም ተብሎ ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፍ ሌላ የተዛባ ትርክት ከመፍጠር መጠንቀቅ እንደሚገባም አሳስበዋል::

በክልሉ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር በትኩረት እንደሚሠራም ርእሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል:: ለዚህም በትጥቅ ግጭት ውስጥ ያሉ ቡድኖችን ወደ ውይይት እንዲመጡ በማድረግ የሰላም አማራጮችን መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል:: ከሕዝብ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በአዲስ አበባ አስጀምሯል:: የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ የመጡ የሀሳብ ልዩነቶች ኢትዮጵያን ከልህቀት ወደ ድቀት፣ ከፍቅር ወደ ጥላቻ፣ ከአንድነት ወደ መነጣጠል፣ ከሰላም ወደ ጦርነት እየጎተቷት መሆኑን ጠቅሰዋል:: በመሆኑም የቀውስ ምክንያቶችን በመለየት በመከባበር ወደ መግባባት መድረስ ብቸኛ  መፍትሔ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል::

ኮሚሽነሩ ማንኛውም ችግር የሚፈታው በሀሳብ ልዕልና ነው ብለዋል:: በመሆኑም ጉልበትን የፍላጎት ማሟያ ብቸኛ መፍትሔ  ከማድረግ ይልቅ ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርገው በምክክር መርህ አሸናፊ መሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል::

በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር፣ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን የሚፈታ የፖለቲካ ባሕል ለማዳበር ምክክር ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል::  ወቅታዊ ችግሮችን ዘላቂ በሆነ መንገድ በመፍታት ሰላምን በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለማቆም የሚደረገው ምክክር በስኬት እንዲቋጭ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ፕሮፌሰሩ አሳስበዋል::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here