ታላቁ ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን “ሠላምን በጉልበት ማስጠበቅ አይቻልም፤ በመነጋገር እና በመግባባት ብቻ እንጂ” በሚል ሐሳቡ ይታወቃል:: ከአሚኮ ወቅታዊ ፕሮግራም ጋር በስካይፒ ቆይታ ያደረጉት የሰላም ግንባታ ምሁሩ ንጉሡ አክሊሉ (ዶ/ር) ግጭቶችን በንግግር መፍታት ይገባል የሚለውን ሐሳብ ያጠናክራሉ:: የመደራደር አቅምን ከፍ ለማድረግ በሚል የግጭት ጊዜን ማራዘም የሕዝብን ስቃይ ከማብዛት፣ ኢኮኖሚን ከማዳከም እና ማኅበራዊ ቀውስን ከማባባስ ባለፈ ይዞት ሊመጣ የሚችል ፋይዳ እንደሌለ ይገልጻሉ:: በመሆኑም የምክክር እና የንግግር በርን ዘግቶ ጦርነትን የማስቀጠል አካሄድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያመዝን በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ምርጫ ሊያደርጉት እንደማይገባ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ክፍሎቿ ግጭት ውስጥ ገብታለች:: የሰሜኑ ጦርነት ብዙኃኑን ለከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ድቀት ዳርጎ ውጥረቱ በሰላም ስምምነት ተቋጭቷል:: ስምምነቱ ሀገሪቱ በጦርነቱ ያጣችውን ሀብት ወደ ነበረበት በመመለስ ዕድገቷን ለማረጋገጥ፣ ሕዝቧም እፎይ! ብሎ ወደ ሥራው እንዲገባ ያደርጋል በተባለ ማግስት ግጭቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል እንደገና አገርሽተዋል::
ለዓመታት በሕዝብ ሲጠየቁ ግን ምላሽ የተነፈጋቸው የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች፣ የኢኮኖሚ እና የልማት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት አለመኖር፣ የተዛባ ትርክት፣ የሕገ መንግሥቱ ሁሉንም ሕዝብ በእኩል አቅፎ አለመነሳት ሀገሪቱ አሁን ለገባችበት ቀውስ ገዥ ምክንያቶች ሆነው ይነሳሉ:: የአማራ ክልል አሁናዊ ቀውስ ምክንያትም ከእነዚህ ምክንያቶች ውጪ እንዳልሆነ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በተለያዩ መድረኮች በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል::
የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም መጋቢት 03 ቀን 2016 ዓ.ም የተቋሙን የስድስት ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የግጭት ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ሐሳቦች ሰንዝረዋል:: ኋላቀር የፖለቲካ ባህል መኖርን ቀዳሚ ምክንያት በማድረግ አንስተዋል:: ይህም ሥርዓትን በሐሳብ የበላይነት አሸንፎ ከመቀየር ይልቅ ኀይልን ብቸኛ አማራጭ የማድረግ ልምድ እየሰፋ መምጣቱ የሀገሪቱ ሰላም ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል ብለዋል::
የተዛባ ትርክት አሁንም ሀገሪቱ ከግጭት አዙሪት እንዳትወጣ ስለማድረጉ አቶ ብናልፍ ጠቁመዋል:: በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለው የውይይት ባህል ደካማ መሆን ለግጭቶች አለመብረድ እንደተጨማሪ ምክንያት አንስተዋል::
መንግሥት “ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ትኩረት ሰጥቼ እየሠራሁ ባለሁበት ወቅት የተፈጠሩ ግጭቶች በሥራዬ ላይ እንቅፋት ፈጥረውብኛል” በሚል ግጭቶችን በአጭር ጊዜ በመቋጨት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ክልሉን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በማስገባት የሕግ ማስከበር ሥራ እያከናወነ ይገኛል:: አዋጁም ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዝሟል:: የሰላም ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ በመንግሥት በኩል በተደጋጋሚ ቢገለጽም ግን አሁንም ግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች መቀጠላቸው እየተሰማ ነው፤ መንገዶችም ከጸጥታ ስጋት ነጻ አልሆኑም፤ በተደጋጋሚ ይዘጋሉ:: ይህም የምርት እና አገልግሎት ዝውውር እንዲቆም በማድረግ የዋጋ ውድነት የሕዝቡ ተጨማሪ ፈተና ሆኖ እንዲዘልቅ አድርጎታል::
የጸጥታ ችግሩ ለበርካታ ንጹሀን ወገኖች ሞትና አካል ጉዳት ምክንያት ሆኗል። ይህንንም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ እና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋማት በተለያዩ ጊዜ በማረጋገጥ ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል። የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ግጭቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ፣ የቀጣይ ስጋቶችን እና በሁሉም ሊተገበሩ የሚገቡ የሰላም የመፍትሄ አማራጮችን እየጠቆሙ ነው::
የሀገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጭ የሆነው ግብርና በተፈጠረው የፀጥታ ስጋት ክፉኛ ተፈትኗል:: አርሶ አደሮች መደበኛ የእርሻ ሥራቸውን በወቅቱ እንዳያከናውኑ፣ የግብርና ግብዓት በወቅቱ እንዳያዘጋጁ፣ የማምረት ሥራውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ እንዲሁም ያመረቱትን በወቅቱ ገበያ አፈላልገው እንዳይሸጡ አድርጓቸዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) የካቲት 27 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በክልሉ ዘጠኝ ዞኖች የተከሰተው ድርቅ እንዲሁም የጸጥታ ችግሩን ተከትሎ የተፈጠረው የግብዓት አቅርቦት ውስንነት በክልሉ ምርት እና ምርታማነት እንዲቀንስ አድርጓል:: ለ2015/16 የምርት ዘመን 8 ሚሊዮን 57 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል:: ይሁን እንጂ ግጭቱ የግብርና ግብዓት በወቅቱ እና በበቂ መጠን ተደራሽ እንዳይሆን እክል መፍጠሩንም አስታውቀዋል::
ግጭቱ አሁንም ቀጣይነት የሚኖረው ከሆነ የግብዓት አቅርቦት መስተጓጎሉ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል:: ይሁንና የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂነት ለመለወጥ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን እንዲሰለፍ ጠይቀዋል::
ሰባት ወራትን መፍትሄ ርቆት የዘለቀው ግጭት ሕዝቡ ከማኅበራዊ ተቋማት አገልግሎት ውጪ እንዲሆንም አድርጎታል:: የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ በግጭቱ በርካታ የጤና መሠረተ ልማቶች መውደማቸውን፣ የሕክምና መድኃኒቶች መዘረፋቸውን፣ 124 አንቡላንሶች በታጣቂዎች ተነጥቀው ለግጭት ዓላማ ስለመዋላቸው ጠቅሰዋል::
የፀጥታ ችግሩ በእናቶች እና ሕጻናት ጤና አገልግሎት ላይም ጫና ፈጥሯል። ለዚህ ማሳያው የጤና ክትትል ማድረግ ከነበረባቸው ነፍሰ ጡሮች ውስጥ 36 በመቶዎቹ ከክትትል ውጭ መሆናቸው፣ በጤና ተቋማት ውስጥ መውለድ ካለባቸው እናቶች ውስጥ 44 በመቶዎቹ በቤት ውስጥ እንዲወልዱ ማስገደዱን ተናግረዋል:: አሥራ አራት በመቶ የሚሆኑ ሕጻናት የጀመሩትን ተከታታይ ክትባት ማቋረጣቸውም ግጭቱ በሕጻናት ጤና ላይ የደቀነው ስጋት ማሳያ ተደርጎ ተነስቷል::
በክልሉ በ298 ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን፣ 3 ሺህ 500 የአንደኛ ደረጃ እና 225 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ወደ መማር ማስተማር እስካሁን አለመግባታቸውን፣ ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ያስታወቁት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ናቸው::
የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ በበኩሉ በክልሉ ስምንት አምራች ኢንዱስትሪዎች እና በርካታ የአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ፕሮጀክቶች በግጭቱ ለውድመት ተዳርገዋል።
በግጭቱ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን ያስታወቁት ደግሞ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ናቸው:: ኃላፊው የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ የክልሉ የሰላም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አስታውቀዋል:: “የተሟላ ሰላም መገለጫው ሕዝቡ በነጻነት ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ማከናወን ሲችል ነው” ያሉት ኃላፊው፣ ለዚህ አሁንም የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል:: ኃላፊው ይህንን ካሉ በኋላ የክልሉ መንግሥት አሁናዊ አቋም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት መሆኑን ደግሞ አስታውቀዋል::
“ፈተናዎችን በጽናት እና በቁርጠኝነት በመሻገር የሕዝባችንን ዘላቂ ሰላም እና ልማት እናረጋግጣለን!” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ በተደረገው የምክክር መድረክ የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል:: የተፈጠረው ክስተትና የደረሰው ጉዳት የአማራን ሕዝብ ነባር እሴት እና ማንነት የማይመጥን ነው ብለዋል:: የክልሉን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማጽናት አሁንም የፖለቲካ አመራሩ በቁርጠኝነት እና በልበ ሙሉነት ሊሠራ እንደሚገባ ጠይቀዋል::
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው የፖለቲካ አመራሩ ክልሉ የገጠመውን ውስብስብ ችግር እና ፈተና በሚገባ ማጤን እንደሚገባ ጠቁመዋል:: አንዱ የሌላውን ችግር መረዳት፣ ልምድ መቀያየር፣ መደጋገፍ እና መተጋገዝ ወቅቱ የፈጠረውን ፈተና ለመሻገር ምቹ መደላድል እንደሚሆንም አስገንዝበዋል፡
ውይይትን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ማጠናከር፣ ጎን ለጎንም ብዝኃነትን እና አብሮነትን መሰረት ያደረገ ትርክት ማጎልበት ዋና የመፍትሄ አማራጭ ሆኖ ሊሠራበት እንደሚገባ የጠቆሙት ደግሞ የሰላም ሚኒሥትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ናቸው:: ሚኒስትሩ እንደሚሉት ምንም ዓይነት የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ሁሉም በጋራ ሊቆም እንደሚገባ ጠቁመዋል:: “ሲመች ኢትዮጵያ ሳይመች ደግሞ ‘ኢትዮጵያ ለኔ ምኔ ናት?’ የሚል አመለካከት ሊወገድ ይገባል” ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል::
ሚኒሥትሩ የመገናኛ ብዙኃን ሰላምን በማስፈን ያላቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡ፤ በተቃራኒው ችግሮች እንዲባባሱ የሚሠሩ ደግሞ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
የሰላም ግንባታ ምሁሩ ንጉሡ አክሊሉ (ዶ/ር) “ግጭቶችን በምክክር ለመፍታት በሩ ፈጽሞ ዝግ ሊሆን አይገባም!” ይላሉ:: እንደ ምሁሩ ገለጻ ከ50 በመቶ በላይ ችግሮች የሚፈቱት በሀገር በቀል እሴቶች ነው። አሁን ግን ፖለቲካዊ ችግሮችን ሊፈታ አልቻለም። ሶማሊያ እና ቤኒሻንጉል ካማሺ ዞን እና የጋሞ አባቶች ግጭቶችን የፈቱበትን መንገድ አድንቀዋል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓቶች ፖለቲካዊ ችግሮችን መፍታት አልቻሉም፤ እናም የተለያዩ ባህሎችን ወደ ሀገራዊ መድረክ በማምጣት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል:: በመሆኑም ለሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓትን ትልቅ ቦታ መስጠትም ከችግር ለመውጣት ዋና መፍትሄ ሆኖ ተመላክቷል::
ግጭቶች እያስከተሉት ካለው ቀውስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መውጣት የሁሉም ሕዝብ ፍላጎት ነው:: በመሆኑም በግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በአወንታ ሊደግፉ ይገባል:: መንግሥትም ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያሳየውን ፍላጎት በቁርጠኝነት ወደ መሬት ሊያወርድ ይገባል:: ሰላም ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ግለሰቦች እና ድርጅቶችም ሁለቱን ወገኖች የማቀራረብ ሥራ ሊተገብሩ ይገባል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም