ጅማሬውን በጸሎት ነበር ያደረገው፣ ጸሎቱ ደግሞ በኢትዮጵያ ሳይወሰን ለሁሉም ፍጥረታት የሰላም ጸጋ እንዲበዛላቸው በመስበክ ነበር። ጸሎቱን ያስተጋቡትም በርካታ ሃይማኖቶችን የወከሉ አባቶች ናቸው። ይህም ማንኛውም ሃይማኖት መሠረቱ ሰላም ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ታዲያ በሀገራችን፣ በባሕር ዳር ከተማ ነው።
ከሰሞኑ ሰላምን የሚሰብክ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡ የኢትዮጵያ ሃይማኖት እና የአማራ ክልል ሃይማኖት ጉባዔያት ባዘጋጁት የሰላም ውይይት ሰላም ለምን ራቀን? የሚል ጥያቄ በሁሉም ተሳታፊዎች ዘንድ ተስተጋብቶ “ሁላችንም ባለድርሻዎች ነን፣ የሰላም እጦቱ የስልጣኔ መነሻዋን ኢትዮጵያን አይመጥንም። የድርሻችንን እንወጣ” ሲሉም ነው ተሳታፊዎቹ በቁጭት የተናገሩት።
የዓለም ሀገራትን ታሪክ ከሚያስነብበው ሂስትሪ ዶት ኦርግ (www.history.org) ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ግጭት፣ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋዎች እና መሰል ክስተቶች የዓለማችን ታሪክ ዋና ዋና መገለጫዎች ናቸው። ውስን ሀገራት ከእነዚህ ክስተቶች (ከሰው ሠራሽ) ተምረው በሁሉም ዘርፍ በስልጣኔ ጎዳና ሲራመዱ ጥቂቶቹ ደግሞ እስከ መጥፋት የደረሰ ስብራት ገጥሟቸው ከዓለም ካርታ ተፍቀው ‘ነበሩ’ ለመባል ተገደዋል።
በተመሳሳይ የሚበዛው የዓለማችን ሕዝብ የየራሱ ዕምነት ያለው ነው። ማንኛውም ዕምነት ደግሞ ስለ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መተሳሰብ፣ … መስበክ የየዕለት ተግባሩ ነው።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከ99 በመቶ በላይ ኢትዮጵያዊያን አማኞች ናቸው። ይህ በመሆኑ ደግሞ ፍቅር፣ አንድነት፣ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ መባባል፣ የአንዱን ሕመም ሌላው መጋራት እና መሰል ዕሴቶች የኢትዮጵያዊያን መገለጫዎች ሆነዋል።
የዛሬን አያድርገውና ከሺህዎች ዓመታት በፊት ከዓለማችን እጅግ ውስን ኃያል ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ግንባር ቀደሟ ነበረች። ለዚህ ሁሉ መሠረቱ ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ዕሴቶች በተሳሰረ የአንድነት ገመድ የሀገሬው ሕዝብ መሰለፉ እንደሆነ ድርሳናት ያስገነዝባሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን የሚስተዋሉ ግጭቶች ኢትዮጵያን የማይገልጹ፣ የቀደመ መልካም ታሪካችንንም የማይመጥኑ ናቸው።
ይህን መነሻ በማድረግ ታዲያ የኢትዮጵያ እና የአማራ ክልል ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰላም ማስፈንን ትኩረት አድርጎ ከመላው ሀገሪቱ ከተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መክሯል። ይበጃል! የተባሉ ሐሳቦችም ቀርበዋል።
ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ “ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ” ሲል የእምነቱን አስተምህሮ ያስተጋባል፤ ይህንን ጥልቅ ትርጉም የያዘ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መነሻ ያደረጉት በዕለቱ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት መምህር ይትባረክ ደምለው ናቸው። “ሰላም ለሀገራዊ አንድነት እና ለመልካም ወንድማማችነት በሃይማኖቶች አስተምህሮ” በሚል ርዕሰ ጥናት ያቀረቡት መምህሩ ሰላም በፍቅር እና በመቻቻል እንጂ በጠመንጃ አይመሠረትም ነው ያሉት።
ጥናት አቅራቢው መነሻቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃሉን መነሻ ያድርጉ እንጂ የሁሉም ሃይማኖቶች መሠረቱ ሰላም ስለመሆኑ ነው አንቀጽ እና ምዕራፍ እየጠቀሱ በአስረጂነት ያቀረቡት።
የአባቶች ቅቡልነት ለምን ደበዘዘ?
የሺህዎች ዘመናት የሀገረ መንግሥትነት ታሪካችን እንደሚያስገነዝበው ሃይማኖቶች (በዋናነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን) የኢትዮጵያ የስልጣኔ መሠረቶች ናቸው። የሃይማኖት አባቶች ደግሞ በሁሉም ነገር ቀድመው ተሰላፊዎች በመሆናቸው ተቀባይነታቸው በእጅጉ የገዘፈ ነው። ኢትዮጵያዊነትን መሠረት ያደረጉ ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓቶችም ከዚህ እውነታ የተቀዱ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ በቅርብ ጊዜ በሚታዩ ግጭቶች፣ በእርስ በርስ መጠፋፋቶች፣ … የሃይማኖት አባቶች የት ገቡ? ሽማግሌዎቻችንስ ምን ነካቸው? ተቀባይነታቸውስ ለምን ቀነሰ? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
እነዚህን ጥያቄዎች ያነሳንላቸው የውይይቱ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶች ታዲያ “ተጠያቂነቱ ከእኛው ላይ አይወርድም” ሲሉ ነው ኀላፊነቱን ሳያቅማሙ የተቀበሉት።
ፓስተር ታደሰ አዱኛ የኢትዮጵያ ሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን ፕሬዝዳንት ናቸው። “የሃይማኖት አባቶች የሚያስተምሩትን መኖር አለባቸው፤ ለቃሉ ታምነው በተግባር ሲኖሩ ደግሞ ሕዝብ ይከተላቸዋል፤ ይሰማቸዋል” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ለሚታየው የቅቡልነት መቀነስም ይህንኑ ሃሳብ ነው ያነሱት። “የሃይማኖት አባቶች በሰማይም በምድርም የሚያስጠይቅ አደራ አለብን። በመሆኑም ለእውነት እና ለአስተምህሮዎቻችን መኖር ይገባል” ብለዋል። ይህን ከከወኑ እና ለእውነት ከቆሙ የቀደመው ተቀባይነታቸው የማይመለስበት ምክንያት እንደሌለ አንስተዋል። ለዚህ ደግሞ “ሕዝቡ ፈሪሃ እግዚአብሔር አለበት፤ የምናስተምረውን ከኖርነው ይከተለናል” ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ጸጋው የተትረፈረፈላት ሀገር መሆኗን በማንሳት “ሃይማኖት የሌለባቸው ሀገራት እንኳ በሰላም እየኖሩ ሃይማኖት ባለባት ሀገር ግጭት ነውር ነው” በማለት ነው ሐሳባቸውን ያጠቃለሉት።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሃጂ ጁሃር ሙሃመድ ኢሳ “የሃይማኖት አባት የሕዝብ አባት ነው፣ በአንድ ሆነን መምከራችን ደግሞ ለሰላም ዘብ ለመሆን ነው” ብለዋል። ሀገራችን የሃይማኖት ሀገር እንደሆነች ጠቁመው ግጭቱም ከሃይማኖት አባት በላይ ሊሆን እንደማይገባ ተናግረዋል። በመሆኑም “ልጆቻችንን በመምከር ወደ ሰላም ማምጣት ዓላማችን ነው። ለዚህም በብርታት እንሠራለን” ብለዋል። የሃይማኖት ሰው ነኝ ማለት ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት አባቶችን ምክር መቀበል እና መተግበር እንደሚገባም አክለዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር እና ደሴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ልሳነክርስቶስ ማቴዎስ የሃይማኖት አባቶች ከመልካምነት ሲርቁ እና ከፖለቲካ ሲቀላቀሉ “ቢናገሩ ማንስ ሰምቷቸው” ይላሉ። በመሆኑም ከዚህ በመራቅ በድፍረት እና እውነትን መሠረት አድርገው ሁሉንም ወገን መገሰጽ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዚህም መስዋዕትነት ሊኖር እንደሚችል የጠቆሙት አቡነ ልሳነክርስቶስ ማቴዎስ ይህ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ለመጠበቅ እና ለእውነት ለመኖር መሆኑን አክለዋል። በሀገራችን ለሚታየው ግጭት “እኔው ራሴ የሚጠበቅብኝን ባለመወጣቴ ጸጸት ይሰማኛል” በማለትም ሰላምን ለማጽናት የፊት ተሰላፊነት ሚናቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
“በዝምታ ማለፍ ሁሉንም ይጥላል” ሲሉ ሐሳባቸውን የጀመሩልን ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መላከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን ናቸው። በጠብመንጃ አፈሙዝ ውጤት እንደማይመጣ በማንሳትም የሰላም ውይይቱ በአዳራሽ ብቻ እንዳይቀር ሁሉም የበኩሉን ሀገራዊ ኀላፊነት እንዲወጣ አደራ ብለዋል።
የቅቡልነት መደብዘዝን በተመለከተ ላነሳንላቸው ጥያቄ “የሃይማኖት አባቶች የሚያስተምሩትን ኖረው ማሳየት አለባቸው። ከልብ ካላስተማርን ማን ከልቡ ይሰማናል” በማለትም ነው ሐሳብ የሰነዘሩት። በመሆኑም አባቶች ክፉ ሲሠራ ያዩትን በግልጽ መገሰጽ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የመወያያ የጥናት ጽሑፍ ያቀረቡት መምህር ይትባረክ ደምለው “የሃይማኖት አባቶች ለሰላም የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ በሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ዕምነት ይፈጥራል፤ እንደ ሀገር የተተበተበው ቋጠሮም ይፈታል” ይላሉ። መምህሩ እንዳብራሩት የሃይማኖት አስተምህሮዎቻችን መሠረታቸው ሰላም ነው። ለዚህ ደግሞ ክርስቶስ “ሰላም
ለእናንተ ይሁን!” ብሎ ያስተማረውን ህያው ቃል አብነት አንስተዋል። አባቶች ይህን መሠረት አድርገው እውነተኛ ቃሉን ከመናገር ባለፈ ሲኖሩት ደግሞ እንደ ተጋድሎ ይቆጠርላቸዋል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ሸምጋይነት እንደ ውኃ የሚጠማ ነው ባይ ናቸው።
በጽሑፉ እንደተመላከተው የሃይማኖት ተቋማት በኢትዮጵያ አንድነት እና መተባበር እንዲኖር ድርሻቸው ከፍ ያለ ነው። ትምህርትን ያለማመዱ እና ሕግን የደነገጉ እነዚህ ተቋማት (ቤተክርስቲያን እና መስጊዶች) ናቸው። “ዛሬም የሃይማኖት አባቶች መሰባሰባቸው የሠራችኋት ሀገር ችግር ላይ ናት ተብለው ነው። ለምን? ቢሉ መዳኛችን ሃይማኖታዊ ትምህርቶቻችን ናቸውና” ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የጥላቻ እና የሴራ አብዮት ኢትዮጵያን ለችግር ዳርጓት እንደቆየ አመላክተዋል። ከችግሩ ለመውጣት ደግሞ እያመሰን ከሚገኘው የጥላቻ ጠብ አጫሪነት መራቅ እና የሃይማኖት አባቶችም ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆን እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም ከችግሩ መውጫ ይሆናሉ ያሏቸውን መንገዶች አመላክተዋል። ያልተጠቀምንባቸው እና የጣልናቸውን ባሕላዊ የእርቅ መንገዶች መጠቀም፣ እስካሁን ከተጓዝንበት ጠማማ መንገድ መራቅ፣ ከምንም በላይ ደግሞ “አትግደል፣ በሃሰት አትመስክር” የሚሉትን አምላካዊ ትዕዛዛት መጠበቅ በጥናቱ የቀረቡ ዋና ዋና መሻገሪያ ሀሳቦች ናቸው።
በውይይቱ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የሰላም ኮንፈረንሱን “ትርጉመ ብዙ” ብለውታል። የተጀመረውን ሰላምን የማጽናት ጉዞ ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለውም ተናግረዋል።
አቶ አረጋ እንዳሉት የሰላም መሠረቱ ግብረ ገብነት ነው። የዚህ አስኳሉ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት ናቸው። የሕዝብን እና የመንግሥትን ግንኙነት በማሳለጥ ሲሻክርም ሁሉንም በአስተምሯቸው የሚያስተካክሉ መሠረቶች ናቸው ነው ያሉት። በመሆኑም “የሕዝባችን ሰላም እንዲጸና፣ ሀገራችንም በከፍታዋ እንድትጓዝ ድርሻቸው ጉልህ ነው” ብለዋል። የጉባዔውን ጭብጦች ከመድረክ ባለፈ ወደ ሕዝቡ በመግባት በውጤት የሚለካ ትርጉም፣ ገቢራዊነት ማምጣት እንደሚገባ አክለዋል።
የተዛቡ ግንኙነቶች እንዲታረሙ፣ የተዛቡ እና የግጭት ታሪኮች እንዲስተካከሉ የሃይማኖት ተቋማት ድርሻ ከፍ ያለ መሆኑንም አንስተዋል።
የግጭት ታሪክ መጨረሻው መጠፋፋት፣ ከዓለም ካርታ መፋቅ ነው ያሉት አቶ አረጋ “እኛም ከግጭት ወጥተን ወደምንታወቅበት ታላቅነታችን እንድንመለስ የሃይማኖት ተቋማት የድርሻችሁን እንድትወጡልን አደራ እንላለን” ብለዋል።
“የሰላምን ፋይዳ የምናውቀው በንድፈ ሃሳብ ሳይኾን አጥተናት ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ወደምንታወቅባቸው መልካም ዕሴቶች መመለስ እንደሚገባም ነው የገለጹት።
በመጨረሻም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሰቲያን የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ አብርሃም አባታዊ መልዕክት ጽሑፋችንን እናሳርገው። ብጹዕነታቸው ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት “ቀኑ ፈጽሞ ሳይመሽ ሃይማኖትን ከፖለቲካ፣ ፖለቲካን ከሃይማኖት ሳንቀይጥ ለሰላም እንቁም” ብለዋል።
ብጹዕ አቡነ አብርሃም በመልዕክታቸው እንደተናገሩት የልብ ደስታ ሰላም ነው፤ ከሰላም ውጭ የሚገኝ ድል እና ደስታ ጸጸት እና እሮሮ የማይለየው ነው። ከዚህ ለመዳን፣ የታሪክ ተወቃሽ እና የትውልድ ተጠያቂ ላለመሆን ደግሞ የሁሉንም ወገን ቅንነት ይጠይቃል። በመሆኑም “ቅጥ ካጣው ሃዘናችን፣ ቁልቁለት ላይ ከሚገኘው ተሰሚነታችን እና ተደማጭነታችን ለመውጣት እንደ አባቶቻችን ልንሠራ ይገባል። ቀኑ ፈጽሞ ሳይመሽ ሃይማኖትን ከፓለቲካ፣ ፖለቲካን ከሃይማኖት ሳንቀይጥ ለሰላም እንቁም” ሲሉ አባታዊ ጥሪ አቅርበዋል።።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም