የውስጥ ግጭት የውጪ ጠላቶች በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ይገቡ ዘንድ በር የሚከፍት ክስተት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የውስጥ ግጭት ለአንድ ሀገር ህልውና እና ለሉዓላዊነት ትልቅ ስጋት ሆኖ ይታያል፡፡ ይህን ክስተት ከሀገራችን ታሪክ በመነሳት ስንመለከተው እውነትነቱ ጎልቶ ይታየናል፡፡
ታሪክ እንደሚነግረን ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት በርስ በርስ ግጭት ሰላሟን አጠታ ኖራለች፡፡ ይህ ውስጣዊ ግጭት ለውጪ ጠላቶች ወረራ አጋልጦን እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ፡፡
ባለንበት ዘመንም በሀገራችን እየተካሄደ ያለው የርስ በርስ ግጭት ኢትዮጵያ እንዳታድግ እና እንዳትበለጽግ ለሚሹ የውጭ ኃይሎች ይህን መሻታቸውን ያሳኩ ዘንድ ትልቅ ዕድል ስለሰጣቸው በተለያዩ መንገዶች የኢትዮጵያን አቅም ለማዳከም ሲጥሩ ይስተዋላሉ።
የርስ በርስ ግጭቶች የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ ተልከው የውጭ ምንዛሪ እንዳያስገኙ እንቅፋት ይፈጥራሉ፡፡ ጎብኝዎች እንደ ልብ እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲቀንስም ምክንያት ይሆናሉ፡፡
የውጭ ኩባንያዎችም ግጭቶች ባሉበት ሀገር ገንዘባቸውን አውጥተው ለማልማት ፈቃደኝነቱ አይኖራቸውም፡፡ ከግጭቶች በፊት ሥራ የጀመሩም ቢሆኑ ስጋት ውስጥ ስለሚገቡ ሥራቸውን ለማቆም ይገደዳሉ። ግጭቶች ካሉ ምርቶች ከሚመረቱበት ወደ ተጠቃሚው ሕብረተሰብ መግባት አይችሉም። ይህም በምርቶች ላይ ዋጋ እንዲጨምር ያደርጋል።
በግጭቶች ምክንያት መፈናቀል ይኖል፡፡ አምራቹ ኃይል ሲፈናቀል ደግሞ ምርት ይቀንሳል፡፡ የምርት መቀነስ ካለ ደግሞ የኑሮ ውድነቱ ይባባሳል፡፡ በግጭት ወቅት በሕጋዊ ባንኮች እና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የውጪ ምንዛሪ ልዩነት ይሰፋል። ዶላር በቤት ውስጥ እንዲከማች ምክንያ በመሆንም ገበያው የዶላር እጥረት እንዲፈጠርበት እንዲሁም የብር የመግዛት አቅም እንዲዳከም ምክንያት ይሆናል።
እነዚህን ችግሮች ላብነት ያህል አነሳን እንጂ ግጭቶች በሀገር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
ስለሆነም ግጭቶችን በምክክር እና ድርድር መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ግጭቶችን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በምክክር እና በድርድር መፍታት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን በ10ኛ መደበኛ ስብሰባው አጽንኦት ሰጥቶ መክሯል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቆም እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ድርድር እንዲደረግ፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ የንጹሃን ጥቃት እንዲቆም ላለፉት ሥስት ዓመታት ሲጠየቅ መቆየቱን፣ ም አውስተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን መንግሥት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታታት በተለይም በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የታጠቂ ኃይሎች ጋር የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ ሊያስቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በእርግጥም እንደ ሀገር እያጋጠሙን ላሉ ተደጋጋሚ ግጭቶች ውይይት ዋናው መፍትሄ ነው፡፡
እያጋጠሙን ያሉትን የውስጥ ግጭቶች ለመፍታት ከታሪካዊ ስህተቶቻችን መማር እና ዘላቂ መፍትሔ ላይ ማተኮርም ብልነት ነው። መንግሥትን፣ የታጠቁ ኃይሎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ማኅበራትን ያሳተፈ ውይይት ማድረግ ግጭቶችን ለመፍታት ሁነኛ መፍትሔ ነው፡፡
የታጠቁ ወገኖች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች እና እያንዳንዱ ማኅበረሰብ የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል፡፡ ምሁራን እና የሃይማኖት አባቶች ሕዝቡን በማስተማር እና ገላጋይ በመሆን ግጭቶችን ለማርገብ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አብዝታ የምትሻው ቁም ነገር ነው፡፡ እያንዳንዱ ዜጋም ለዘላቂ ሰላም መረጋጋጥ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡
መንግሥት ሁሌም ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆን እና ዜጎችን ከጥቃት የመከላከል ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል። ከጥላቻ ንግግር መቆጠብ፣ የጋራ ሀገራዊ ዕሴቶች ላይ ማተኮር እና ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


