ሰላም እንዲመጣ ንግግር ይቅደም!

0
167

በአማራ ክልል ይፋዊ የሆነ  በትጥቅ የታገዘ ግጭት ከተጀመረ  ዘጠኝ ወር አለፈው። ከሀምሌ መገባደጃ ጀምሮ የታወጀው አስቸኳይ አዋጅ  ስድስተኛ ወሩን ደፍኖ፣ አራተኛ ወር ተደምሮበት ለአስር ወር እንዲዘልቅ ተወስኖ ነበር። አሁን አስረኛ ወሩም ሊጠናቀቅ ከወር ያነሰ ዕድሜ ቀርቶታል።  አንዳንዶች  ከጦርነት ይልቅ ውይይት እና ንግግር፣ ድርድር እና ምክክር፣ ሁሉን አካታች  ተቋማዊ ውሳኔ ያስፈልጋል  ሲሉም ገና በግጭቱ አፍላ ወቅት ብዙዎች ተናግረው ነበር። ይሁን እንጂ  ሰላምን በጦርነት ለማምጣት  ተኩሱ ቀጠለ። ይህ ግጭት የሰብዓዊ ሕይዎትን እየቀጠፈ፣ ኢኮኖሚውን እያወደመ እና ማህበራዊ መስተጋብርን እየበጣጠሰ፣ ተቋማትን እያሽመደመደ፣ ወንድማማቾችን በጎራ እያጋደለ ከዘጠኝ ወር በላይ አለፈው። ሰላም የጠፋበት ምክንያት ለይቶ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በመሳሪያ የታገዘ ውጊያው ቀጠለ። ይህም ለማህበራዊ ጉስቁልና እና ለነገ ታሪክም ጠባሳውን አትሟል። የግጭቱን አፈጣጠር እና አፈታት ከማጤን ይልቅ እኔ ትክክል፣ ሌላው ስህተት የሚለው  ግትር አቋምም መፍትሄውን አርቆታል። ነገሩን አሳንሶ ማየት፣ መፈረጅ፣ ጥላቻ መዝራትም የግጭቱ ባህሪ ሆኖ ቀጥሏል።

የሻከሩ ልቦች፣ የተጎዱ ወገኖች፣ የወደሙ ተቋማት፣ የተሽመደመደውን ኢኮኖሚ ለመጠገን እና አሁንም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከመነጋገር የተሻለ መፍትሄ የለም። በጦርነቱ በተለይም በርስ በርስ ጦርነት አንድ ወገን ብቻ አሸንፎ ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ስለማይቻል ሕዝብን ማዳመጥ፣ የሕዝብ ጥያቄን መመለስ፣ ሕዝብን ጌታ ማድረግ ያስፈልጋል። ችግርን ወደ ሶስተኛ አካል በመጠቆም እና በመፈራረጅ፣ በመገዳደል፣ በማሰር፣ በማሳቀቅ የሚመጣ ዘላቂ ሰላም ስለማይኖር አሁንም ከልብ ሀቀኛ ንግግር እና  ውይይት ይደረግ። ከውይይት እና ንግግር የተነጠለ ፖለቲካ ለሀገር ውድመት፣ ለዜጎች ስደት እና ሞት ጋባዥ ከመሆን ያለፈ ትርጉም አይኖረውም።

“ገዳዩ ባልሽ ነው፣ ሟቹም ወንድምሽ፣

ሀዘኑ ቅጥ አጣ

ከቤትም አልወጣ”

እንደሚባለው ሀገረሰባዊ አነጋገር ሟች እና ገዳይ ወንድማማች ናቸው።  ከራስ ወደ ራስ የሚተኮስ ጥይት መቅሰፍቱ ብዙ ነው። ከዚህ መቅሰፍት ለመውጣት ንግግር፣ መደማመጥ፣ መነጋገር፣ መረዳዳት ያስፈልጋል።  ኢትዮጵያ  ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ  ከብዙ  ሺህ በላይ ዜጎቿን በርስ በርስ ጦርነት አጥታለች፤ ኢኮኖሚዋም ደቋል።

ጦርነት የሞት መንገድ ነው። የሞትን መንገድ ለመዝጋት ያልረፈደ ንግግር፣ እውነተኛ ፖለቲካዊ ትንታኔ፣ አሳታፊ ስነ መንግስታዊ አደረጃጀት ያስፈልጋል። የዜጎች በሕይዎት የመኖር መብት ይረጋገጥ ዘንድ የመሳሪያ አፈ ሙዝ ተዘግቶ የአካፋ እና የዶማ እጀታ ይነሳ። የጠረጴዛ ፖለቲካ ይፋፋ።  በሐሳብ መሟገት፣ ባሸነፈው ሐሳብ መመራራት ይለመድ። ጦርነት የሚወልደው ሌላኛ ጦርነት በመሆኑ  አሁንም ሌላ ጦርነት እንዳይወለድ የጦርነት ሶንከፎች መነቃቀል እና በሰላም መጠገን ይኖርባቸዋል። ጦርነት እንዳይወለድ ለማድረግ ደግሞ ፍትሕ፣ የሕግ የበላይነት  እና  አሳታፊነት አስፈላጊ በመሆኑ ለዚህ መስራት ግድ ይላል። ይህ ሲሆን ሰላም ይመጣል፣ ጦርነትም መድረሻ ያጣል።

ዜጎች ሰላም ተርበዋል። የተራቡትን ሰላም እንዲያገኙ እውነተኛ ፖለቲካዊ ንግግር   ተገቢ ነው። መገዳደል እንዲቆም ልዩነቶችን በድርድር መፍታትን መፍራት  ተገቢ አይደለም። በዜጎች ሞት የሚመነዘር ፖለቲካ  ፈፅሞ ሊኖር አይገባም።

(የሺሃሳብ አበራ)

በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here