ሰላም የሁሉም መሠረት ነው!

0
192

ለተከታታይ ዓመታት መፈናቀል፣ ግጭት እና ጦርነት የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ክፉኛ ፈትኖታል። ከዚህ ሰው ሠራሽ ችግር ላይ ደግሞ ድርቅ ተከስቷል። ድርቁ ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት አርቋል። ብዙዎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል። ፆም አዳሪ  መንደሮችን ፈጥሯል። እንስሳትን ለሞት እና ለበሽታ ብሎም ለረሀብ ዳርጓል። ድርቅ መከሰቱ በብዙ ሀገራትም ሊፈጠር የሚችል ክስተት ቢሆንም፣ ረሀብን መውለዱ ግን አስጊ ክስተት ነው።

ርዳታ ለማቅረብ እንኳን በአማራ ክልል  ዓመት ሊደፍን እየተቃረበ ያለው አለመረጋጋት እና ግጭት ለመጓጓዣ ምቹ አይደለም። መንገዶች ይዘጋሉ፣ ለመጓዝም አስተማማኝ የሰላም ዋስትና የለም። ይህም ለተራቡ ዜጎች  በፍጥነት ለመድረስ  ነገሩን በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ አድርጎታል።  በተለይም ደግሞ   ዘላቂ መፍትሄውን ለማበጀት የሰላም ሁኔታው እና አንዱ አንዱን እየፈረጀና አለመረጋጋቱ ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል።

በዘላቂነት የአየር ንብረት ለውጥን እንዲሁም ብክለትን ለመከላከል ችግኝ መትከል አስፈላጊ ነው፣ ከዚህ ባለፈ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ዛፎችን መትከል፣ የበጋ መስኖን ማጠናከር እና በጊዜያዊነት በፍጥነት መድረስ የሚችሉ ፍጆታዎች ላይ በማተኮር ችግሩን መቀነስን እንደ መፍትሔ በመውሰድ ድርቅ ረሀብ እንዳይሆን፣ እንዲቀንስም በማድረግ ጊዜያዊ መፍትሔ ማበጀትም ያሻል። ለጊዜው ደግሞ ድርቅ ለፈተናቸው ዜጎች የዕለት ምግብ ድጋፍ ማድረግ፣ ቀጣይ ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢ ነው። ሆኖም ግን  የግጭቱ አለመቆም  ዜና የተራቡ ዜጎችን ድምፅ ማሰማት ስላልቻለ መፍትሔውንም አርቆታል፡፡

በመሆኑም ሀገርን ለማረጋጋት እና ለማልማት የመጀመሪያው አማራጭ ሰላም ነውና ለሰላም  የሚሆን ቀና ልብ እና ጥበብ ያስፈልጋል። የአንድ ሀገር ልጆች ከመተኳኮስ በጋራ ወደ ማልማት ይገቡ ዘንድ ነገሮችን መርምሮ የሚገነዘብ መሪ ያስፈልጋል። ስለዚህ ድርቁ የወለደውን ረሀብ ለመከላከል አፋጣኝ እና ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማዘጋጀት በአንድ በኩል የሰላም መንገድን መከተል፣ በሌላ መንገድ ደግሞ በመተባበር የተራቡ ዜጎችን ለመርዳት መተባበር ሞራላዊ ግዴታ ነው። ረሀብ ጊዜ ስለማይሰጥ የሰብዓዊ ድጋፉ እንዲፋጠን የሚያስችል አሠራር መዘርጋት እና ለዚህም ሁሉም ወገን መተባበር ይጠበቅበታል።

ሰላም ከጠፋ ሁሉም ነገር ይጠፋል። የልማት መሠረቱ ሰላም ነው። ረሀብም በሰላም ይሸነፋል።  ለሰላም ሁሉም ይሥራ፤ ወገኖቻችንንም እንደግፍ።  መደጋገፉ  እውነተኛ ሰላምን ለማረጋገጥ እና ለተቸገሩት ለመድረስም ይሆናል።

(የሺሃሳብ አበራ)

በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here