ኢትዮጵያ ሁሉንም የምርት አይነት ማብቀል የሚችል ለም መሬት ባለቤት መሆኗ፣ ከ85 በመቶ በላይ ሕዝቧ በእርሻ መተዳደሩን… ግብርና መር ኢንዱስትሪ አብዮትን እንድትከተል አድርጓታል:: ይህንንም አብዮት እውን ለማድረግ ሀገሪቱ በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ እና ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት በሚውሉ ሰብሎች ላይ በማተኮር እየሠራች ነው:: በቂ እና ጥራቱ የተጠበቀ ምርት ለማምረትም ባለሐብቶችን ወደ እርሻ ከማስገባት ባሻገር ለእርሻ ሜካናይዜሽን ትኩረት መሰጠቱን መረጃዎች ያሳያሉ::
በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ እና ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች በግብዓትነት የሚውሉ የሰብል ምርቶችን በስፋት በማምረት ከሚታወቁ የአማራ ክልል አካባቢዎች የምዕራብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው:: ሰሊጥ እና አኩሪ አተር የዞኑ መገለጫዎች ሆነው በትኩረት እየተሠራባቸው መሆኑን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል::
እንደ ማሽላ ያሉ የምግብ ሰብሎችም በዞኑ በስፋት ቢመረቱም በውጭ ገበያ ተፈላጊነታቸው እና ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች ሽፋን ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑ ተመላክቷል:: ለዚህ ዋናው አብነት በዞኑ በ2014/15 የምርት ዘመን 449 ሺህ 358 ሄክታር መሬት ለውጭ ገበያ /ኤክስፖርት/ ተፈላጊ በሆኑ ምርቶች፣ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ግብዓት በሚሆኑ እና በሌሎች የምግብ ሰብሎች ተሸፍኗል። ከነዚህም 6 ሚሊዮን 829 ሺህ 7 ኩንታል ምርት ተገኝቷል። በ2015/16 የምርት ዘመንም 498 ሺህ 45 ሄክታር መሬት በተጠቀሱት ሰብሎች ተሸፍኖ 7 ሚሊዮን 278 ሺህ 659 ኩንታል ምርት መገኘቱን በድህረ ምርት ግምገማው ተረጋግጧል::
የምዕራብ ጎንደር ዞን ክልሉ ካለው የእርሻ መሬት ውስጥ ዘጠኝ ነጥብ ስምንት በመቶ እና በምርት አምስት በመቶ ድርሻ እንዳለው የመምሪያው መረጃ ያሳያል:: የሰሊጥ ክልላዊ ድርሻውም 29 ነጥብ 8 በመቶ ሲሆን፣ የምርት ድርሻው 27 ነጥብ 9 በመቶ መሆኑ ዞኑ ለውጭ ገበያ ለሚቀርቡ እና ለፋብሪካ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች የሰጠው ትኩረት ማሳያ ሆነው ይነሳሉ::
በአካባቢው በእርሻ ኢንቨስትመንት ተሰማርተው በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ እና ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆኑ ሰብሎችን እያመረቱ የሚገኙ ባለሐብቶች ወቅታዊ የጸጥታ ችግሩ እና ጠንካራ የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ በዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዳላደረጋቸው ለበኲር በስልክ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ሁለት በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሐብቶች መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በስፋት እንዲመረቱ የለያቸውን ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ጥጥ፣ ማሾ እና ቦለቄ ያመርታሉ:: ከባለሐብቶቹ መካከል አንደኛው የምዕራብ ጎንደር ዞን የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ከሚፈልጉት ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ በቂ ምርት የሚመረትበት አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል:: በአንጻሩ በሀገር ውስጥ ጥጥን፣ ሰሊጥን እና ሌሎች የቅባት እህሎችን የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች “በጥሬ እቃ ግብዓት ተፈተንን” ማለታቸው እንደሚያስገርማቸው ይገልጻሉ::
አርሶ አደሩ ባመረተበት ልክ ተጠቃሚ የሚያደርገው ዋጋ ማጣቱ፣ ፋብሪካዎች የሚፈልጉትን እና የሚያስፈልጋቸውን የምርት መጠን በጥናት ለይቶ በጋራ የመሥራት ክፍተት መኖሩ እና የጸጥታ ሁኔታው አስተማማኝ አለመሆኑ የግብርናው ዘርፍ በአስተማማኝ ሁኔታ ኢንዱስትሪዎችን እንዳይደግፍ እያደረገ ነው ይላሉ::
ባለሀብቶች መንግሥት ብዙ አርሶ አደሮች ወደ ግብርናው ዘርፍ እንዲገቡ እያደረገ ባለበት ጥረት ልክ ጠንካራ የገበያ ትስስር አልፈጠረም በሚልም ይወቅሳሉ:: በወቅቱ አኩሪ አተር በስፋት እንዲመረት መንግሥት ዘር እስከማቅረብ መድረሱን ለምርቱ ከፍተኛ ትኩረት ለመስጠቱ ማሳያ አድርገው አንስተዋል:: ባለሀብቱ በ2015/16 የምርት ዘመን አኩሪ አተር፣ ጥጥ፣ ሰሊጥ በስፋት አምርተዋል:: ያመረቱትን ገበያ አፈላልገው በተሻለ ዋጋ እንዳይሸጡ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታው ፈትኗቸዋል:: የሀገር ውስጥ የአኩሪ አተር ዋጋ ከ24 ብር አለመብለጡ እና የጥጥ ምርት ተፈላጊ አለመሆን በዘርፉ እንዳይቆዩ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል::
የሰላም መናጋቱ እንደ ቀደሙት ዓመታት ሁሉ የሚፈለገው ሠራተኛ ወደ አካባቢው እንዳይገባ መከልከሉንም አስታውሰዋል:: ይህም የግብርና ምርቶች ለብክነት ሳይዳረጉ በአጭር ጊዜ ለመሰብሰብ እንዳይቻል አድርጓል:: ትራክተር፣ የጭነት መኪና እና ሞተር በሚንቀሳቀስበት ወቅት ማንነታቸው በማይታወቁ ሰዎች ከፍተኛ ክፍያ መጠየቁ በእርሻ የተሰማሩ ባለሐብቶች በዘርፉ ተስፋ እንዲቆርጡ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል::
በውይይት መፍታት የሚቻለውን ችግር በጦርነት መፍትሄ ለመስጠት የሚደረግ ሂደት ሀገሪቱን ለከፋ ቀውስ እየዳረጋት መሆኑንም ባለሐብቱ ጠቁመዋል:: “መንግሥት አሁንም ችግሮችን በውይይት መፍታትን ካላስቀደም ሀገሪቱ ከቀውስ አዙሪት ትወጣለች የሚል እምነት የለኝም” ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል:: ግብርና የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት መሆኑ እየተገለጸ ባለበት ወቅት ለሰላም ችግሮች ፈጣን ምላሽ አለመስጠት ዘርፉ ውጤታማ እንዳይሆን ሊያደርገው እንደሚችል ባለሀብቱ ያምናሉ::
የነዳጅ አቅርቦት እጥረት እና የሰላም ችግሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰቱ የልማት አደናቃፊ ክስተቶች መሆናቸውን ያስታወቁት ደግሞ ሌላው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለሐብት ናቸው:: ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና የምርት ብክነትን ለመቀነስ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን እንደሚገባ ያምናሉ:: ለዚህም በትራክተር ማረስ እና በኮምባይነር መሰብሰብ ያስፈልጋል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት እና የዋጋው ተመጣጣኝ አለመሆን ይህንን የማዘመን ሂደት ሊገድበው እንደሚችል ገልጸዋል::
ለስምንት ወራት የዘለቀው የአማራ ክልል ቀውስ የግብርናውን ዘርፍ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እንደገደበው፣ ይህም ለግብርናው ዘርፍ የነገ ሥጋት አድርገው አንስተዋል:: እስካሁን የቀረበ የአፈር ማዳበሪያ አለመኖሩን ለአብነት አንስተዋል::
በአሁኑ ወቅት የተፈጠሩ የዘርፉ ፈተናዎች ቁንጮ የሰላም መናጋቱ ነው ብለው የሚያምኑት ባለሐብቱ፣ በመሆኑም መንግሥት ጦርነትን ለሰላም ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ ወደ ጦርነት የገቡ አካላትን በማነጋገር ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለሀገሪቱ ዕድገት ሁሉም እንዲነሳ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠይቀዋል::
የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንዳርጌ ጌጡ ዞኑ ሰሊጥ እና አኩሪ አተርን በስፋት በማምረት ለውጭ ገበያ እና ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች የጥሬ ግብዓት ፍላጎት ምላሽ እየሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል:: የእነዚህ ምርቶች የማሳ ሽፋን እና የምርት መጠን ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሆኑን አኃዞችን እየመዘዙ ያስረዳሉ:: በ2014/15 የምርት ዘመን 124 ሺህ 432 ሄክታር መሬት በሰሊጥ ሲሸፈን 572 ሺህ 31 ኩንታል ምርት ተገኝቷል።
ባለፈው ዓመት የመኸር ወቅት 160 ሺህ 610 ሄክታር መሬት በተመሳሳይ ምርት ተሸፍኖ 1 ሚሊዮን 2 ሺህ 983 ኩንታል ተመርቷል። በማሳ ሽፋንም ሆነ በምርት የታየው መጨመር አርሶ አደሩ ማሳውን በሰሊጥ የመሸፈን ልምዱ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ ሆኖ ተመላክቷል::
ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በጥሬ እቃ ግብዓትነት የሚውለው የአኩሪ አተር ምርት በተመሳሳይ ዓመታት የማሳ መጠኑ እየጨመረ ቢመጣም የምርት መጠኑ ግን መቀነስ እንደታየበት መምሪያ ኃላፊው ገልጸዋል:: ለማሳያም በ2014/15 የምርት ዘመን በአኩሪ አተር ከተሸፈነው 127 ሺህ 417 ሄክታር መሬት 2 ሚሊዮን 899 ሺህ 270 ኩንታል ምርት ተገኝቷል። ከዓመት በኋላ የማሳ መጠኑ ወደ 135 ሺህ 426 ሄክታር ከፍ ሲል የተገኘው የምርት መጠን ደግሞ ወደ 2 ሚሊዮን 643 ሺህ 675 ኩንታል ወርዷል። ለምርት መቀነሱ ዋናው ችግር የአኩሪ አተር ሰብል የሚፈልገውን ከፍተኛ የዝናብ መጠን ማግኘት ባለመቻሉ መሆኑን ጠቁመዋል::
“ማምረት ብቻውን በቂ አይደለም” ያሉት ኃላፊው፣ በተለይ ለውጭ ገበያ ቀርበው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሆኑ እና ለፋብሪካ በጥሬ እቃ ግብዓት የሚውሉ ምርቶች ለገበያ እንዲቀርቡ በትኩረት በመሥራት አርሶ አደሩ በዘላቂነት እንዲያመርት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል::
በ2015/16 የምርት ዘመን ከተመረተው የሰሊጥ ምርት ውስጥ 987 ሺህ 759 ኩንታል ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 545 ሺህ 425 ኩንታል መላኩን ኃላፊው አስታውቀዋል። ወደ ውጭ ለመላክ የታቀደውን ሁሉንም ለማሳካትም የጸጥታ ስጋቱ ፈታኝ ሆኖ እንደሚነሳ አስታውቀዋል።
የአኩሪ አተር ምርት ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ 600 ሺህ ኩንታል ለማቅረብ ዕቅድ መያዙን፤ እስካሁንም ማሳካት የተቻለው ግን ከ454 ሺህ 870 የበለጠ አለመሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል። ከዚህም ቁጥራዊ አኃዝ መረዳት የሚቻለው በ2015/16 የመኸር ወቅት ከተመረተው አጠቃላይ የአኩሪ አተር ምርት ውስጥ 2 ሚሊዮን 188 ሺህ 805 ኩንታል ከግብይት ውጭ መሆኑን ነው::
ኃላፊው ይህን ያህል ምርት ለምን ከግብይት ውጭ እንደሆነ ሲያስረዱ፤ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ያስከተለው የመንገድ መዘጋት ቀዳሚው ችግር ነው ብለዋል:: ሌላው ችግር አኩሪ አተርን በስፋት ይጠቀማሉ የተባሉ አዳዲስ የዘይት ፋብሪካዎች ወደ ሥራ አለመግባታቸው እንደሆነ ገልጸዋል:: በጸጥታ እና በሌሎች ምክንያቶች ግንባታቸው መጓተቱ ዘርፉ ግቡን እንዳይመታ፣ አርሶ አደሩም ከአኩሪ አተር ምርት እንዲወጣ ሊያደርገው እንደሚችል ስጋት አላቸው::
በጸጥታ ችግሩ ምክንያት በቂ የአፈር ማዳበሪያ አይቀርብም፤ የሜካናይዜሽን እርሻን ተግባራዊ በማድረግ ምርት እና ምርታማነትን ለማረጋገጥም የነዳጅ አቅርቦት የዓመቱ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ከአርሶ አደሮቹ ለተነሳው ስጋት ኃላፊው ምላሽ ሰጥተዋል:: ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ለተነሳው ስጋት እስካሁን የዕቅዱ 33 በመቶ ወደ ዞኑ መግባቱን እና ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መጀመሩን አስታውቀዋል:: ቀሪውም በአጭር ጊዜ እንዲገባ ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል::
በክልሉ ካሉ አካባቢዎች ውስጥ የእርሻ ሜካናይዜሽን በስፋት የሚከናወነው በምዕራብ ጎንደር ዞን ነው። አሁንም ተጨማሪ የሜካናይዜሽን ዕድሎችን ለማስፋት እየተሠራ ነው:: ለማረስ፣ ለመውቃት፣ ምርቱን ወደ ጎተራ ለማስገባት እና በመስኖ ለማልማት የነዳጅ አቅርቦት በስፋት ስለሚያስፈልግ መምሪያው በተለይ በእርሻ ወቅት ማደያዎችን በልዩ ቁጥጥር እና ክትትል ለመምራት ትኩረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የፈጠረው ችግር ሰፊ መሆኑን የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ በጽሑፍ ያደረሰን መረጃ ያሳያል:: በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የተገደበው እንቅስቃሴ ኢንዱስትሪዎች በግብዓት አቅርቦት ክፉኛ እንዲፈተኑ አድርጓል:: በሥራ ላይ ያሉትም ቢሆን በኤሌክትሪክ ኀይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በሚደርስ ጥቃት በሚያጋጥም የኀይል መቆራረጥ በሚፈለገው መጠን እንዳያመርቱ አድርጓል:: ይህም የምርት መቀነስ የዋጋ ንረት እንዲጨምር እና የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ስለማድረጉ በቢሮው ተመላክቷል::
የሰላም መደፍረሱ ቢሮው በተፈለገው መንገድ እስከታችኛው መዋቅር በመውረድ ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ሥራዎችን ማከናወን አልቻለም፤ በሰላም መንቀሳቀስ በመገደቡ ባለሙያዎች ቀበሌ ድረስ ወርደው ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ተገቢውን የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን መስጠት አልቻሉም:: ይህም የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር ለይቶ በመፍታት የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ ሰፊ ጉድለት እንደፈጠረ ተመላክቷል:: በዚህም አዳዲሶቹን ወደ ሥራ ማስገባት፣ ነባሮቹን ማጠናከር፣ ሥራ ያቆሙትን ችግሮቻቸውን ለይቶ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ወደ ሥራ ለማስገባት የተፈጠረው የሰላም ችግር የሰፋ ተጽእኖ ማሳደሩን ቢሮው በጽሁፉ ጠቁሟል::
የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት በመጨመር የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ያለባቸውን የግብዓት ችግር በሚፈልጉት መጠን እና ጥራት ማሟላት እንደሚያስፈልግም ቢሮው በላከው የጽሑፍ መረጃ አስታውቋል::
ይሁን እንጂ የተፈጠረው የሰላም እጦት ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት በወቅቱ አሟልተው ወደ ሥራ በመግባት ገበያ የማረጋጋት ተልዕኳቸውን እንዳይወጡ ማድረጉን ጽሁፉ ቁጥራዊ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ አመላክቷል:: አምራች ኢንዱስትሪዎች በ2015 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከሀገር ውስጥ ገበያ ከ102 ሺህ 823 ቶን በላይ ግብዓት አቅርበዋል:: በ2016 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት መቅረብ ከነበረበት 27 ሺህ 568 ቶን ግብዓት ውስጥ ማቅረብ የተቻለው 5 ሺህ 91 ነጥብ 29 ቶን ብቻ ነው:: ይህም በዓመቱ ተከስቶ እስካሁን የዘለቀው የሰላም መደፍረስ ውጤት መሆኑን ጽሑፉ አመላክቷል::
ችግሩ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ሂደቱም ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል:: በ2015 ዓ.ም ግማሽ ዓመት 54 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ የተገኘ ቢሆንም በተፈጠረው ሰላም ማጣት በ2016 ግማሽ ዓመት ግን ማሳካት የተቻለው 29 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው::
በክልሉ የተከሰተው የፀጥታ ስጋት ባለሀብቶች እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ፣ ምርታቸውን ለውጭም ሆነ ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች በማቅረብ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል:: እናም መንግሥት ከክልሉ አልፎ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያሳድጋል፣ የውጭ ምንዛሬ ይፈጥራል ብሎ ተስፋ የጣለበት ዘርፍ ጭራሽ ሳይደቅ ችግሩን ከጦርነት ይልቅ በውይይት እንዲፈታ የአስተያየት ሰጭዎችን ሀሳብ እኛም አጽንኦት ሰጥተናል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም