ሱዳን ከ40 ዓመታት በፊት በአፍሪካ ከታየው ወዲህ ዓለማችን ከተመለከተው የከፋ ሊሆን የሚችል የረሃብ አደጋ እንደተጋረጠባት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ነው። ይህ ማስጠንቀቂያ የተሰማው የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች እርዳታ እንዳይገባ ከልክለው ነገር ግን ለሁለቱም ወገኖች የሚደረገው የጦር መሳሪያ እርዳታ ፍሰት በቀጠለበት አጋጣሚ ነው። በተመሳሳይ በሱዳን ከ25 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለረሃብና ቸነፈር መዳረጋቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።
የእርስ በርስ ጦርነት መገለጫዋ የሆነችው ሱዳን ከቀድሞው አምባገነን መሪዋ ኦማር ሐሰን አልበሽር ከመንበረ ሥልጣን መውረድ በኋላ የሰነቀችው ተስፋ ህልም ሆኖ ቀርቷል። የሱዳናዉያንን ህልም በማምከን የመከራ ኑሮ እንዲገፉ ያደረገው ደግሞ በሀገሪቱ ወታደራዊ አገዛዝ መሪ አልቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ ሃምዳን ዳጋሎ መካከል ጦርነት በመቀስቀሱ ነው።
ጦርነቱ ተባብሶ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ታዲያ በሀገሪቱ ያንዣበበው ረሃብ የሱዳንን መከራ እንዲከፋ እያደረገው ነው። የሀገሪቱ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ “በሱዳን ከጥይት በበለጠ ረሃብ በርካቶችን ለሞት እየዳረገ ነው” ብለዋል።
አብደላ ሃምዶክ ከዘናሽናል ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ በጦርነቱ ምክንያት በረሃብ የሚያልቀው ሱዳናውያን ቁጥር አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል። የሱዳናውያንን አሁናዊ የመከራ ኑሮም “ከሚታሰበው በላይ ስቃይ ውስጥ ይገኛሉ” ነው ያሉት።
የዓለም ትኩረት፣ ሰው ሠራሽ ረሃብ ወዳገረሸበት የጋዛ ጦርነት ላይ ሆኗል፤ አነስተኛ የሚዲያ ሽፋን እና ዓለም አቀፋዊ ትኩረት የተሰጣት ሱዳን ታዲያ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ አንዣብቦባታል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሰብአዊ እርዳታ ካደረገው ጥሪ ዐሥራ ስድስት በመቶ የሚያክለውን የገንዘብ እርዳታ ብቻ ነው ያገኘው።
በሱዳን ያለውን ችግር አሳሳቢነትም “በቅርብ በዓይናችን በብረቱ ለምናየው፣ በደጅ ላለው አደጋ ዓለምን ማንቃት እንፈልጋለን” በማለት በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪን ፊልድ ተናግረዋል።
በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና በአልቡርሃን ወታደራዊ አስተዳደር መካከል ከሚያዚያ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ግጭቱ በመባባሱ ሀገሪቱን ለሁለት ከፍሏታል። የርስ በርስ ግጭቱ 14 ሺህ ሰዎችን ለሞት የዳረገ እና ከ10 ሚለዮን በላይ ዜጎችን ቤት ንብረታቸውን አስለቅቆ እዲሰደዱ አድርጓል።
የውጪ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ጦርነቱን አባብሶታል፤ የሱዳናዊያንን ሰቆቃም ጨምሮታል:: የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የጦር አውድማ በመሆኗ ወደ ፍርስራሽነት እየተቀየረች ነው። እንደ አልጀዚራ ዘገባ የሀገራት ጣልቃ መግባት የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማድረግ ጦርነቱን እዲባባስ፣ የሱዳናዊያን ሰቆቃም እንዲከፋ እንዳደረገው ነው ዘገባው ያስነበበው:: ክስተቱም በእጅጉ እንዳሳሰበው የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።
ዘ ኢንዲፐንደንት የዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) የጥናት ቡድንን ጠቅሶ እንደዘገበው ደግሞ በሱዳን ከፍተኛ የሚባል በሰብዓዊነት ላይ የተቀናጀ፣ ስልታዊ እና መሰረታዊ የሆነ ጥቃት ተፈጽሟል። የዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ የሆኑት ከሪም ካሃን ይፋ ባደረጉት የቪዲዮ መግለጫ ከግጭቱ በኋላ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አስገዳጅነት በምዕራብ ዳርፉር ክልል የሚገኘው አንድ ትልቅ ሆስፒታል እንዲዘጋ መደረጉን አስታውቀዋል። በአል ፋሸር ሆስፒታል ግድያ እና ዝርፊያ መፈፀሙን ደግሞ ድንበር የለሽ የዶክተሮች ቡድን ሪፖርት አድርጓል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤል ፋሸር መከበብ እንዲያበቃ የእንግሊዝ መንግሥት ያቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ የፀጥታው ምክር ቤት ቢያፀድቀውም ጠርነቱ ግን እንደተባባሰ መቀጠሉን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል። የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ኃላፊዋ ሳማንታ ፓወር የኤል ፋሸር ከተማ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እጅ የሚወድቅ ከሆነ እዚያው ተጠልለው በሚገኙ ስደተኞች ላይ የሚደርሰው ጉዳት አሳሳቢ ነው።
ሳማንታ ፓወር እንዳሉት ከ315 ሚሊዮን ዶላር (19 ቢሊዮን ብር ገደማ) በላይ ለሱዳን ተጨማሪ የሰብዓዊ እርዳታ በአዲስ ተዘጋጅቷል፤ ነገር ግን በጦርነት ተከበው ለሚገኙት ሰዎች መድረስ የቻለ ምንም አይነት እርዳታ አለመኖሩን ተናግረዋል። ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በምግብ ላይ ክልከላ ማድረግን እንደመሣሪያ እየተጠቀሙበት እንደሆነ በማንሳትም ወቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በእርዳታ እህል መጋዝኖች ላይ ዝርፊያ እያካሄደ፣ ምግብ እና የቀንድ ከብቶችን በመስረቅ፣ የእህል መጋዝን ቁሶችን እና የውኃ ጉድጓዶችን በማውደም ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ሳማንታ ፓወር አክለዋል። “የሱዳን ሠራዊት ኃይል ወደ ዳርፉር እርዳታ ለማስገባት የሚያስችለውን መስመር በመዝጋቱ ለሱዳን ህዝብ የገባውን ቃሉን ባለማክበሩ ከኃላፊነቱ ጋር ሙሉ ለሙሉ ይጋጫል” ብለዋል።
አምባሳደር ግሪን ፊልድ በበኩላቸው በዳርፉር እና በኮርዶፋን የሚኖሩ በርካታ ሱዳናዊያን ሊሞቱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል። ይህም በምድራችን ከታዩት ሰብዓዊ ቀውሶች እጅግ የከፋው እንደሚሆን ጠቁመዋል።
አሶሴትድ ፕሬስ (AP) የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው ጦርነቱ ከዐሥር ሚሊዮን በላይ ሱዳናዊያንን አፈናቅሏል፤ ይህም በዓለም ትልቁ መፈናቀል ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ናቸው።
በሌላ በኩል ሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን የአረብ ኢሚሬትስ ከጦርነቱ መነሳት ጀምሮ እስካሁን እያገዘች ሲሆን ይህም ለጎሳ ጦርነት በመዳረጉ ክስ እንደሚጠብቃት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሱዳን አምባሳደር ተናግረዋል። ይህም መነጋገሪያ ሆኗል። አምባሳደሩ የአረብ ኢሚሬትስ የጦር መሣሪያ ስለመርቷዳ “ካርቱም በቂ ማስረጃ አላት” ብለዋል። ማስረጃውንም ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። የአረብ ኢሚሬትስን ተግባርም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንዲያወግዝ፣ ድርጊቱንም አሳፋሪ አድርጎ እንዲሰይመው ግፊት ለማድረግ ተጨማሪ ርቀት እንደሚሄዱ ተናግረዋል።
በመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ መሰረት ረጅም እና አሰቃቂ መልክ ይዞ የቀጠለው ጦርነት ባለፈው ዓመት የለየለት ጦርነት ሆኗል:: እስካሁን ባለው ሁኔታ 14 ሺህ ሰዎች እንደሞቱና 33ሺ እንደቆሰሉ፤ አስር ሚሊዮን ሱዳናውያንም ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል:: በመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ረዳት ሊቀመንበር ማርታ ፖቤ ጎሳን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በምዕራብ ዳርፉር ክልል መፈጸሙን በመግለጽ የድርጊቱን አስከፊነት አስጠንቅቀዋል። ፖቤ እንዳሳሰቡት በኤል ፋሸር አስቸኳይ ተኩስ አቁም በማድረግ ተጨማሪ ጥፋትን መከላከል፤ የንጹኃን አበሳ መቀነስ እንዲሁም ወሳኝ የመሰረተ ልማት ተቋማትን መታደግ ይገባል።
ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት የነፈጉት እና ሰሚ ጆሮ ያጣው የሱዳኑ ጦርነት በፕላኔታችን አስከፊውን ሰብዓዊ ውድመት ሳያስከትል ርብርብ በማድረግ ማስቆም እንደሚገባ የተባበሩት መንግሥት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገራት አሳስበዋል፣ ማስጠንቀቂያም ሰጥተዋል::
ይህ በእንዲህ እያለ የአውረፓ ህብረት በስድስት የሱዳን ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሉን ሮይተርስ ዘግቧል። ከሱዳኑ የርስ በርስ ጎሳ ተኮር ግጭት ጋር በተያያዘ ከሁለቱም ተፋላሚዎች ስድስት ያህል ባለስልጣናት ያካተተ ሲሆን የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ያካተተ መሆኑን ዘገባው ያስረዳል።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም