ሰማያዊዉ ተአምር

0
29

የእግር ኳስ አማልክት ፊታቸውን ወደ ካሪቢያን ደሴት አዙረዋል:: በካርታ ላይ በአጉሊ መነጽር (Magnifying glass) ተፈልጋ የምትገኘው ኩራሳው (Curacao) ለ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች:: ኩራሳው ከጎንደር ከተማ ያነሰች ሀገር ናት። ሙሉ ከተማዋን ከጫፍ እስከ ጫፍ በመኪና ለመዞር ከሁለት ሰዓት ያነሰ ይፈጃል:: የኩራሳው ሕዝብ ብዛት 156 ሺህ ነው:: ይህም ከዚህ በፊት  በአይስላንድ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን የካሪቢያን ደሴቷ ሀገር አሻሽላለች:: “እኛ ደሴት ብቻ አይደለንም፤ እኛ አሁን የዓለም እግር ኳስ ቤተሰብ አባላት ነን” ሲል የቡድኑ አምበል ኤሎይ ሩም በደስታ እንባ ታጥቦ ሲናገር ተደምጧል::

አይስላንድ እ.እ.እ በ2018 ሩሲያ በተደረገው የዓለም ዋንጫ በመሳተፍ ትንሿ ሀገር እንደነበረች አይዘነጋም:: የአይስላንድ ሕዝብ 350 ሺህ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ:: እንደ ቻይና፣ ህንድ እና ኢንዶኔዥያ ያሉ በዓለም ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸው ሀገራት ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ሲቸገሩ በጣም ትንንሽ የሚባሉት ሀገራት ግን አቅማቸውን አሟጠው  በመስራት አዲስ ታሪክ አስመዝግበዋል፤ እያስመዘገቡም ነው::

በ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አስደናቂ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ኬፕ ቨርዴ አንዷ ነበረች:: 528 ሺህ ሕዝብ ያላት ምዕራብ አፍሪካዊት ሀገር ካሜሩንን በመብለጥ የምድቡ መሪ በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫው ማለፍ ችላለች። በምዕራብ አፍሪካ የባህር ዳርቻ ላይ የምትገኘው ይህች ደሴት ለዓለም ዋንጫው ያለፈች ሁለተኛዋ አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ትንሿ ሀገር ሆናለች::

ኩራሳው በመጨረሻው ዙር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጃማይካ ጋር ያለምንም ግብ ከተለያየች በኋላ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ትኬቷን የቆረጠች ትንሿ ሀገር ሆናለች:: እናም ኩራሳው ለትናንሽ ሀገራት አዲስ ተስፋ ፈንጥቃለች:: ጨዋታው የተካሄደው “ዘ ኦፊስ” (The Office) እየተባለ በሚጠራው እና ለተጋጣሚዎች አስፈሪ በሆነው የጃማይካ ብሔራዊ ስታዲየም ነበር:: ሙቀቱ፣ እርጥበቱ እና የደጋፊው ጩኸት ኩራሳውን ለመዋጥ ተዘጋጅቶ እንደነበር የሚታወስ ነው::

በመጀመሪያዎቹ 45 ደቂቃዎች ጃማይካ ኳሱን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥራ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ የደጋፊዎች ጭንቀት እና የጨዋታው ሙቀት ጨመረ። እናም ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ሲቀሩት የጃማይካ ብሄራዊ ቡድን በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆኖ ነበር የሚጫወተው:: ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ብቻ ሲቀረው መላው የኩራሳው ሕዝብን ልብ ቀጥ የሚያደርግ ክስተት ተፈጠረ:: ጃማይካዊው ተጫዋች ካሄም ዲክሰን በተጋጣሚያቸው የፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ወደቀ። የመሀል ዳኛው ያለምንም ማመንታት ጥፋት እንደሆነ በምልክት አሳየ::

በስታዲየሙ ውስጥ የነበሩ 30 ሺህ ጃማይካውያንም በደስታ ፈነደቁ:: የኩራሳው ተጫዋቾች ግን ክስተቱን ማመን ተስኗቸው ሜዳ ውስጥ ተዝለፍልፈው ወደቁ:: የአራት ዓመት ልፋት በሽርፍራፊ ሴኮንዶች ውስጥ ሊጠፋ ተቃረበ:: ይሁን እንጂ በቪዲዮ ረዳት ዳኛ (VAR) የታየው ክስትት ፍጹም ቅጣት ምት እንዳልሆነ አበሰረ:: በዚህ ወቅት በስታዲየሙ የነበረው ጸጥታ አስፈሪ ነበር:: ይህች ቅጽበት የኩራሳውን እጣ ፈንታ የቀየረች ክስተት ስትሆን “መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት” በማለትም ጠርተዋታል::

ከዚህ ድል ጀረባ የ78 ዓመቱ ሆላንዳዊ አሰልጣኝ አድቮካት (Advocaat) አሉ:: “ትንሹ ጄኔራል” በመባል የሚታወቁት አድቮካት የኔዘርላንድ፣ የሩሲያ፣ የቤልጂየም እና የደቡብ ኮሪያን ብሄራዊ ቡድን ያሰለጠኑ የእግር ኳስ ሊቅ ናቸው:: በጣም የሚገርመው በዚያ ታሪካዊ ቀን ግን አድቮካት በስታዲየሙ አልነበሩም።  በገጠማቸው አስቸኳይ የቤተሰብ ጉዳይ ምክንያት ወደ ሀገራቸው ኔዘርላንድ ተጉዘው ነበር::

ይሁን እንጂ ለአራት ዓመታት የደከሙበት ሥራ ሜዳ ውስጥ  ይታይ እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል:: የተከላካይ መስመሩ ጥንካሬ እና የቡድኑ ስነ-ልቦና የእሳቸው የእጅ ሥራ ውጤት መሆኑን ያሳያል:: ከጨዋታው በኋላ ምክትል አሰልጣኙ “ይህ ድል ለአለቃችን  አድቮካት ነው” ሲሉ የተናገሩትም ለዚህ ነበር:: ኩራሳው 156 ሺህ ሕዝብ ይዛ እንዴት ለዓለም ዋንጫ በቃች? መልሱ “ዲያስፖራ” ነው።

ኩራሳው የኔዘርላንድ ግዛት አካል እንደሆነች መረጃዎች ያመለክታሉ:: በኔዘርላንድ ተወልደው ያደጉ በአውሮፓ አካዳሚዎች የሰለጠኑ ነገር ግን የኩራሳው የዘር ሀረግ ያላቸውን ተጫዋቾች በማሳደድ ብሄራዊ ቡድን መሰረቱ:: እነዚህ ተጫዋቾች በልባቸው የኩራሳውን ፍቅር በእግራቸው  ደግሞ የአውሮፓን ጥበብ ይዘው ታሪክ መሥራት ችለዋል::

ወደ 2026ቱ የዓለም ዋንጫ ለመብረር ትኬት በቆረጠችበት ምሽት የሀገሪቱ ዋና ከተማ ዊለምስታድ በሰማያዊ ቀለም ተጥለቀለቀች:: ታዋቂው “የንግሥት ኤማ ድልድይ” በሰማያዊ መብራቶች አሸበረቀ። በመንገዶች ላይ ሰዎች ተቃቅፈው ሲጨፍሩ እና ፌሽታቸውን ሲያስተጋቡ አደሩ:: ቀኑም “ብሔራዊ የድል ቀን” ሆኖ ታወጀ:: በትምህርት ቤቶች፣ በቢሮዎች እና በየቤቱ የሚወራው አንድ ቋንቋ ብቻ ሆነ፤ “Nos ta bai World Cup” (ወደ ዓለም ዋንጫ እየሄድን ነው):: ኩራሳው ይህን እድል ያገኘችው በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ማሻሻያ ምክንያት እንደሆነ አያጠያይቅም::

ፊፋ (FIFA) የቡድኖችን ቁጥር ከ32 ወደ 48 ማሳደጉ ለትናንሽ ሀገራት በር ከፍቷል:: አዘጋጆቹ አሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ ያለማጣሪያ በቀጥታ ማለፋቸው ለቀሪዎቹ የኮንካካፍ ሀገራት ሰፊ እድል ሰጥቷል:: ከኩራሳው ምን እንማራለን? ይህ ድል ለኢትዮጵያ እና መሰል በእግር ኳስ ስፖርት ደካማ ለሆኑ ሀገራት ትልቅ ትምህርት ያስተምራል:: ኩራሳው ይህን ፕሮጀክት የጀመረችው ከዓመታት በፊት ነው:: የአንድ ሌሊት ሥራ አይደለም። የሕዝብ ብዛት ለእግር ኳስ ወሳኝ አይደለም፤ ልዩነቱ ጠንካራ ሥራ እንጂ።

ዓለም አሁን በካርታ ላይ ኩራሳው የት እንዳለች መፈለግ ጀምሯል። የዓለም ዋንጫው ሲጀመር የኩራሳው ብሔራዊ መዝሙር በኒውዮርክ ወይም በሎስ አንጀለስ ግዙፍ ስታዲየሞች ውስጥ ሲዘመር ያኔ ድሉ ሙሉ ይሆናል። ሰማያዊው ማዕበል ከካሪቢያን ተነስቶ ዓለምን ያጥለቀልቃል::

 

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here