ሰሜን ዋልታ በአዛውንት ሲረታ

0
48

አሜሪካዊው አዛውንት ግግር በረዶ የተነጠፈበትን ሰሜን ዋልታ ጫፍ የመርገጥ ህልማቸውን በ95 ዓመታቸው አሳክተው ክብረወሰን መያዛቸውን የዓለም አቀፉ የድንቃድንቅ መዝገብ ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት አስነብቧል::አዛውንቱ ንቁ፣ በበረዶ ላይ መንሸራተትን የሚወዱ እና የቴኒስ ስፖርት  ያዘወትሩ እንደነበርም ነው ለንባብ የበቃው፡፡

በጐልማሳ እድሜያቸው ካቀዷቸው ግቦች ያላሳኩት  ነገር ግን በማስታወሻ ደብተር ከትበው ከያዙት የቀረ አንድ ብቻ መሆኑን አረጋግጠዋል ቤተሰቦቻቸው፡፡ ህልማቸውንም የሰሜን ዋልታን ጫፍ መርገጥ በሚል አስፍረዋል- ሪቻርድ ዲክ:: የአዛውንቱ ሪቻርድ ዲክ አምስት የቤተሰብ አባላት የልጅ ልጃቸውን ጨምሮ የጉዞ እቅድ ነድፈው፣ አስፈላጊ ቁሳቁስ አሟልተው፣ የደህንነት ጥንቃቄዎችን ሳይቀር የሚቻላቸውን ሁሉ በቅደም ተከተል አደራጅተዋል- የመጨረሻ ህልማቸው ከግብ እንዲደርስ::የ95 ዓመቱ ሪቻርድ ዲክ በቤተሰብ ታጅበው ወደ ሰሜን ዋልታ በምታመራው መርከብ ተጉዘው እግራቸው በረዶ ሲረግጥ የመጨረሻ ፎቶ ግራፍ ተነስተው ለበረዷማ ቀጣናው አስፈላጊውን አልባሳት እና ምርኩዛቸውን ይዘው መንሸራተታቸውን ቀጠሉ:: አካልን ሰርስሮ የሚገባው የሰሜን ዋልታ ቅዝቃዜ አልበገራቸውም- አዛውንቱን፡፡

ለዚህም በጉጉት የሚጠብቋቸው የቤተሰባቸው አባላት እና በጉልምስና እድሜ ያለሙት ህልማቸው ብርታት ጥንካሬን ለግሷቸዋል::በመጨረሻም አዛውንቱ ሪቻርድ ዲክ በማስታወሻ ደብተራቸው ለማየት እንደሚጓጉ፣ በህይወታቸው ቢፈፅሙት ከፍ ያለ ሀሴት እንደሚፈጥርላቸው ያሰፈሩትን ሰሜን ዋልታን የመመልከት እቅዳቸውን በአስራ አንደኛው ሰዓት አሳክተዋል፤ ለክብወረስን መብቃታቸውም በማደማደሚያነት ለንባብ በቅቷል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here