ሰሞነኛዉ የእስራኤል እና የሃማስ ሁኔታ

0
231

ከሰሞኑ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስራኤል የምግብ እና የሕክምና እርዳታን ወደ ጋዛ እንድትፈቅድ ትዕዛዝ አስተላልፏል::

ቢቢሲ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስራኤል ረሃብን ለመከላከል ወደ ጋዛ ያለ ምንም እንቅፋት ዕርዳታ እንዲገባ እንድታደርግ አዝዟል። ይህ ውሳኔ የተላለፈው  በሳምንታት ውስጥ የከፋ ረሃብ በጋዛ ሊከሰት ይችላል የሚለውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ነው። እስራኤል በበኩሏ “ዕርዳታን እየከለከለች ነው” የሚባለውን ውንጀላ “ፍፁም መሠረተ ቢስ” ስትል ተቃውማለች።

እስራኤል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ለፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ምላሽ ስትሰጥ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመተባበር ወደ ጋዛ በየብስ፣ በአየር እና በባሕር ቀጣይነት ያለው ዕርዳታ እንዲገባ ለማድረግ እንዳቀደች አሳውቃለች::

ባለፈው ሳምንት በዓለም የምግብ ፕሮግራም እና በሌሎች ተቋማት የሚተዳደረው  ግሎባል ኢኒሼቲቭ ሪፖርት በጋዛ አሰቃቂ ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሆነ በመግለጽ  አስጠንቅቋል። በጋዛ ውስጥ ያሉት ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች  ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት እያጋጠማቸው እንደሆነ  እና ከግንቦት መጨረሻ በፊት  የግዛቱ ሰሜናዊ ክፍል በረሃብ እንደሚመታ ተንብዩአል።

ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እስራኤል ምንም ሳይዘገይ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ሙሉ ትብብር በማድረግ መሠረታዊ አገልግሎቶችን እና ሰብአዊ ዕርዳታን ለማረጋገጥ ሁሉንም አስፈላጊ እና ውጤታማ እርምጃዎችን መውሰድ አለባት ብሏል።

ምግብ፣ ውኃ፣ መብራት፣ ነዳጅ፣ መጠለያ፣ አልባሳት እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች እና የሕክምና ቁሶች በጣም የሚያስፈልጉ እርዳታዎች ናቸው።  በተጨማሪም ውሳኔው እስራኤል በዓለም አቀፉ የዘር ማጥፋት ስምምነት መሠረት ሠራዊቷ በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያንን መብት የሚጥስ ድርጊት እንደማይፈጽም ማረጋገጥ አለባት ብሏል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ ከግብጽ ወደ ጋዛ ለመግባት በሚጠባበቁ የዕርዳታ ተሽከርካሪዎች ረዣዥም ወረፋዎች እየታዩ ነው። እስራኤልም በዕቃዎቹ ላይ ውስብስብ እና የዘፈቀደ ፍተሻ እያደረገች ነው በሚል ውንጀላ ቀርቦባታል። ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት መክሰሷ ይታወቃል። እስራኤልም የደቡብ አፍሪካን ውንጀላ (ክስ) “መሠረተ ቢስ” ስትል ውድቅ አድርጋዋለች። ሃማስ ወደ ጋዛ ከሚገቡት ዕርዳታዎች አብዛኛውን እንደሚወስድም አስታውቃለች::

በጋዛ ሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እስራኤል ሃማስ ያደረሰባትን ትንኮሳ ተከትሎ በወሰደችው የአጸፋ ዘመቻ ቢያንስ 32 ሺህ በላይ ሰዎችን ገድላለች ብሏል። ከተገደሉት መካከል ከ25 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሴቶች እና ህጻናት ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን በጋዛ ሰባት የበጎ አድራጎት ሠራተኞች በእስራኤል የአየር ድብደባ ሕይወታቸውን ካጡ በኋላ እስራኤል ከዓለም በኩል በተለይ ከምዕራባዊያን ያልጠበቀችውን ውርጅብኝ እያስተናገደች ነው:: ወርልድ ሴንትራል ኪችን የተባለው የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ናቸው የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት:: ይህ ጥቃት  በጋዛ የሚደረገውን የዕርዳታ ሥራ እንዳቆመውም ተነግሯል::

ሲኤንኤን እንደዘገበው የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እስራኤል ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱ የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባት አሳስበዋል:: ከሟቾቹ መካከል የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የካናዳ፣ የፖላንድ እና የአውስትራሊያ ዜግነት ያለቸው ሰዎች ይገኙበታል:: ከዚህ ጋር ተያይዞ አውስትራሊያ፣ እንግሊዝ እና የአውሮፓ ሕብረት በእርዳታ ሠራተኞች ግድያ ዙሪያ ምርመራ እንዲካሄድ ፍላጎታቸው እንደሆነ አሳውቀዋል::

ይሁንና  የእስራኤል ምጣኔ ሀብት ሚኒስትር ኒር ባርካት የእስራኤል ጦር ኃይል ሆን ብሎ በጋዛ በሚገኙ የዕርዳታ ሠራተኞች ላይ ጥቃት እንዳልሰነዘረ ተናግረዋል። የጥቃቱ ሰለባ የሆነው የ”ወርልድ ሴንትራል ኪችን”  የዕርዳታ ድርጅት  መሥራች የሆኑት ሆሴ አንድሬስ “እስራኤል ሆን  ብላ በመኪናው ውስጥ በሚገኙ ሠራተኞች ላይ  ጥቃት አድርሳለች” በማለት ክስ አቅርበዋል።

ሆኖም የእስራኤሉ የምጣኔ ሀብት ሚኒስትር ኒር ባርካት ለቢቢሲ የሚስተር አንድሬስ አስተያየት “ከንቱ” ነው ብለዋል።

ሚስተር ባርካት እንዳሉት እስራኤል “ሰባቱ የዕርዳታ ሠራተኞች በመገደላቸው እጅግ አዝናለች” ብለዋል፤ “ነገር ግን በጦርነት ወዳጃዊ እሳት ይከሰታል” ብለዋል። የዕርዳታ ሠራተኞች እና የሲቪሎች ሞት የጦርነት አንዱ ክፍል እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ ከእስራኤል ተሰነዘረ በተባለ ጥቃት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እንደሞቱ ተነግሯል። ይህን ተከትሎም ውጥረት የበረታ ሲሆን ዋይት ሀውስ በደማስቆ ጥቃት ምንም አይነት ተሳትፎ እንዳልነበረው አስታውቋል:: እስራኤል በአውሮፕላን አድርሳዋለች በተባለው ጥቃት በትንሹ 13 ሰዎች ሲሞቱ ከሟቾቹ መካከል ሰባት ከፍተኛ የኢራን ጄኔራሎች ይገኙበታል::

በተያያዘ እስራኤል እየወሰደችው  ባለው እርምጃ የአል-ሺፋ ሆስፒታል ሙሉ በሙሉ አግልግሎት መስጠት በማይችልበት ሁኔታ ላይ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት  አስታውቋል::  ቢቢሲ እንደዘገበው የእስራኤል ጦር  ለሁለት ሳምንታት ያህል በጋዛው አል-ሺፋ ሆስፒታል ዘመቻ ሲያካሂድ ከቆየ  በኋላ ከሰሞኑ  ሆስፒታሉን  ለቆ መውጣቱ ተገልጿል። የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት እንደገለጸው ወታደሮቻቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሽብርተኞችን በሆስፒታሉ ገድለዋል። በርካቶችንም በቁጥጥር ሥር አውለዋል። በሆስፒታሉ ዙሪያ የጦር መሣሪያዎች እና የደኅንነት መረጃዎች ማግኘቱንም አሳውቋል። የእስራኤል ጦር “የሆስፒታሉን የሕክምና ክፍሎች ያወደምኩት ሃማስ ስለሚጠቀምበት ነው” የሚል ምላሽ ሰጥቷል። ከሰሞኑ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ አል-ሺፋ “የሽብርተኞች መሸሸጊያ” ሆኗል ብለዋል። ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከ200 በላይ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን አባላት መገደላቸውንም ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ አል-ሺፋ ጥቃት ከተከፈተበት በኋላ 20 ታካሚዎች መሞታቸውን አሳውቋል።

ይህ በእንዲህ እያለ አይሁዳዊያን በኔታኒያሁ መኖሪያ ቤት አካባቢ ተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እንዲለቁ የጠየቁት ከሰሞኑ ነበር:: በጥቅምት ወር ሀገሪቱ ወደ ጦርነት ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ ትልቁን ፀረ-መንግሥት ተቃውሞ በማድረግ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ሰልፍ ወጥተዋል። ተቃዋሚዎች በጋዛ ውስጥ በሃማስ የተያዙ ከአንድ መቶ ሠላሳ በላይ ታጋቾች እንዲለቀቁ፤ ተኩስ አቁምም እንዲደረግ ጠይቀዋል።

እንደሚታወሰው ኔታኒያሁ ሃማስን ለማጥፋት እና ሁሉንም ታጋቾች ወደ ቤታቸው ለማምጣት ቃል ገብተው ነበር፤ ሆኖም እነዚያ  ቃሎች ሃማስ ከፍተኛ ኪሳራ ቢደርስበትም እስካሁን ሊሳኩ  አልቻሉም። አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው በሰልፉ በርካቶች ከፖሊስ ኃይል ጋር ተጋጭተዋል::

በተያያዘም  የእስራኤል ፓርላማ ለሀገሪቱ  ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ናቸው የተባሉ መገናኛ ብዙሃን  በጊዜያዊነት  እንዲታገዱ  የሚፈቅደውን  መመሪያ  አጽድቋል። በዚህም  “አልጀዚራ” በእስራኤል ምድር  እንዳይዘግብ  ተከልክሏል:: አልጀዚራ  ከሃማስ  ጋር  ግንኙነት አለው በሚል  እስራኤል በተደጋጋሚ  በተቋሙ  ላይ  አቤቱታ ስታቀርብ  ቆይታለች።  አልጀዚራ ግን  የእስራኤልን  ውንጀላ  ውድቅ ሲያደርግ ነው የቆየው።

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here