ሰሞነኛዉ ጉንፋን

0
226
Just the sniffles? Could be the flu.

እ.አ.አ ከ1914 እስከ 1918 ድረስ የዘለቀውና የ15 ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ጦርነት በታሪክ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ተብሎ ይታወሳል፡፡ እልቂቱ ቆሞ የጦርነቱ ማብቂያ ሊታዎጅ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ግን የዓለም ሕዝብ ሌላ ፍዳ ማስተናገድ ግድ ሆኖበት – የዓለም ሕዝብ በኢንፍሉዌንዛ በሽታ ከዳር እስከ ዳር ተጠቃ፡፡ በተለምዶ የስፓኒሽ ፍሉ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ መነሻው ከወደ አሜሪካ እንደሆነ ይታመናል፡፡

ይህም እ.አ.አ በጥር ወር 1918 በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ዋዜማ በጦርነቱ ለመካፈል የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት ከተከሰተው ወረርሽኝ ጋር ይያያዛል፡፡

ካንሳስ በሚገኘው ወታራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የተቀሰቀሰው ወረርሽኝ በሦስት ቀናት ብቻ 45 ሺህ ወታደሮችን አጠቃ፡፡ ወታደሮች አትላንቲክን አቋርጠው አውሮፓን እንደረገጡ በሽታው አብሮ ደረሰ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየውም ፈረንሳይ ነበር፡፡

ነገር ግን የኘሮፓጋንዳ መጠቀሚያ እንዳይሆን ተደብቆ ቆይቶ  ይፋ የሆነው እ.አ.አ በሕዳር ወር በ1918 በስፔን መከሰቱን ተከትሎ ነበር፡፡ በወቅቱም ስለበሽታው በርካታ  የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ሰጡት፡፡ በዚህም ምክንያት ወረረሽኙ ስፓኒሽ ፍሉ የሚል ስያሜ ተሰጠው፡፡

በኢትዮጵያም ከዐሥር ወራት በኋላ የበሽታው ምልክት ታዬ፤ ከ40 ሺህ በላይ ዜጎችን ሕይወትም ነጠቀ፡፡ በሽታው የተከሰተበትን ወር መሠረት አድርጐ የሕዳር በሽታ የሚል ስያሜ እንደተሰጠው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ስፓኒሽ ፍሉ ወይም ኢንፍሉንዛ ይባላል፡፡

ሳል፣ ከፍተኛ ሙቀት… ዋና ምልክቱ የሆነው የጉንፋን በሽታ ዛሬም ድረስ የክረምቱን መውጣት ተከትሎ በተለይም ጥቅምት እና ሕዳር ወራት በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ከሌሎች ወራት በተለዬ ይከሰታል፡፡

በሽታው በቀላሉ ሊስፋፋ የሚችለው በጽዳት ጉድለት እንደሆነ ስለሚታወቅ በዚያን ዘመን (ወረርሽኙ ሲከሰት) በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች ሕዝብ ቆሻሻ ሰብስቦ እንዲያቃጥል የተጀመረው ተግባር ዘሬም ድረስ ዘልቆ “ሕዳር ሲታጠን” እየተባለ ቆሻሻ ይቃጠላል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ “ሰሞነኛ ጉንፋን፤ አዲሱ ጉንፋን” የሚሉ ስያሜዎች ተሰጥቶት  በከፍተኛ ደረጃ ሕዝብን እያጠቃ ይገኛል፡፡

እ.አ.አ በታኅሳስ 30 ቀን 2021 ጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለም ዙሪያ ኦሚክሮን በተባለ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የሚያዙ ስዎች ቁጥር በየሁለት ቀኑ በእጥፍ ያድጋል። በአሜሪካ ብቻ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ13 በመቶ ወደ 73 በመቶ ከፍ ብሏል። በኢትዮጵያም የኦሚክሮን ዝርያ መኖሩ በጤና ሚኒስቴር በኩል በይፋ ባይረጋገጥም   የኦሚክሮን ዝርያን የሚመስሉ ምልክቶች መታየታቸውንና በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሆነ ጤና ሚኒስቴር በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ እንደሚያመላክተው ደግሞ በተያዘው ዓመት መስከረም እና ጥቅምት ወራት ከሁሉም የቅኝት ጣቢያዎች በተሰበሰቡ ናሙናዎች በኢትዮጵያ የተከሰተው ጉንፍን መሰል በሽታ 35 በመቶ መንስኤው አር ኤስ ቪ የተባለ ቫይረስ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በዚህ ዙሪያ ባወጣው መረጃ እንዳብራራው የጉንፋን በሽታ በተፈጥሮ የላይኛውን የመተንፈሻ የሰውነት ክፍሎች አፍንጫን፣ ጉሮሮን እና የአየር መተላለፊያ ባንቧን የሚያጠቃ ተላላፊ ሕመም ነው። በርካታ ቫይረሶች ለጉንፋን መከሰት ምክንያት ቢሆኑም በጣም የተለመዱት ግን ሪኖ እና ኮሮና ቫይረስ፣ ኢንፍሉዌንዛ፣ ፓራ ኢንፍሉዌንዛ፣ አር ኤስ ቪ (RSV) ቫይረሶች ናቸው፤ ሪኖ ቫይረስ ደግሞ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ መረጃው አክሏል።

የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የመተንፈሻ አካላት ቫይረስ በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ክፍል በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተመረጡ የጤና ተቋማት የቅኝት ሥራውን በመደበኛነት ላለፉት 15 ዓመታት እየሠራ እንደሚገኝ በድረ ገጹ አመላክቷል።

የኢንስቲትዩቱ መረጃ እንደሚጠቁመው በተያዘው ዓመት መስከረም እና ጥቅምት ከሁሉም የቅኝት ጣቢያዎች ከሕሙማኑ  ከተሰበሰቡ ናሙናዎች 35 በመቶ አር ኤስ ቪ፣ ስድስት ነጥብ ሁለት በመቶ ኢንፍሉዌንዛ፣  ሁለት በመቶ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መሆናቸው ተረጋግጧል። የአር ኤስ ቪ (RSV) ቫይረስ ተጠቂዎች ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ወቅት ከሚከሰተው መጠን ከፍ ያለ ሲሆን ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሕሙማን መካከል 88 ነጥብ አምስት በመቶ  ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት ናቸው፡፡

ምልክቶች

ጤና ሚኒስቴር በድረ ገጹ እንዳሰፈረው  ሰሞነኛው ጉንፋን ከፍተኛ ትኩሳት፣ ጠንካራ ሳል፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የመገጣጠሚያ፣ የጀርባ እና የጡንቻ ሕመም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እንዲሁም ኀይለኛ የራስ ምታት ምልክቶቹ ናቸው፡፡  የትንፋሽ ማጠር ወይም ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣ ከፍተኛ ትኩሳት እና መድከም ካለ ምን አልባት በሽታው የከፋ ደረጃ መድረሱን አመላካች ሊሆን እንደሚችልም  መረጃው ይጠቁማል።

መከላከያ መንገዶች

በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪም  ዶክተር ፋሲል መንበረ በኢትዮጵያ በርካታ ሰዎች በቅርቡ በተከሰተው  ጉንፋን መሰል በሽታ ለመያዛቸው የጥንቃቄ ጉድለትን በምክንያትነት ያስቀምጡታል።  ብዙ ሰው የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ አለማድረግ፣  በአንድ ስፍራ መሰባሰብ፣ የአካባቢ ጽዳት መጓደል … ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡  የትምህርት ቤት መከፈት እና የተማሪዎች እንቅስቃሴም ሌላኛው ለሰሞነኛው ጉንፋን  ከሰዎች ወደ ሰዎች በከፍተኛ ፍጥነት እንዲዛመት ምክንያት  መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሽታውን ለመከላከልም ንክኪን በመቀነስ ወይም ጥንቃቄ በማድረግ እንዲሁም  ሲያስነጥስ እና ሲያስል አፍና አፍንጫን በአግባቡ በመሸፈን ከጉንፋን መሰሉ በሽታ ራስንና ሌሎችን መጠበቅ እንደሚቻል የጤና ባለሙያው መክረዋል፡፡

 

በሽታው በተለዬ ማንን ይጎዳል?

እድሜያቸው ከሦስት ወር በታች የሆኑ ሕጸናት እና ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው አዋቂ ሰዎች ሰሞነኛው ጉንፋን መሰል በሽታ  ክፉኛ ሊጎዳቸው እንደሚችል ዶክተር ፋሲል ጠቁመዋል፡፡  ከእነዚህም ውስጥ  ስኳር፣ የደም ግፊት እና ሌሎች ተጨማሪ ሕመም ያለባቸው ሰዎች በቀላሉ ወደ ከፋ ደረጃ ሊደርሱ ይችላሉ።

በተለይ “ከሦሰት ወር በታች ያሉ ሕጻናት  የአየር ቧንቧቸው እና አፍንጫቸው በጣም ጠባብ ስለሆነ በቀላሉ የመታፈን፣ ለመተንፈስ የመቸገር፣ የመጨናነቅ እና እስከ ሆስፒታል ደረጃ ሊያደርሳቸው ስለሚችል ለእነሱ የተለዬ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

የህጸናት ስፔሻሊስት ሐኪሙ ዶክተር ፋሲል ለቢቢሲ በሰጡት መረጃ ጨምረውም በተለይ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ሕጻናት ወደ ጨቅላዎቹ በሽታውን ወይም ቫይረሱን ይዘው እንዳይመጡ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መክረዋል።

በበሽታው የተያዙ ሕጻናትን  በቤት ውስጥ እንዴት ማከም እንደሚቻል ዶ/ር ፋሲል   እንደሚከተለው ያብራራሉ፤ በበሽታው የተያዙ ጨቅላ ሕጻናትን በቤት ውስጥ ለማከም ለብ ያለ ውኃ በጨው አድርጎ ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ በጠብታ መልክ በአፍንጫ መስጠት እንዲሁም የአፍንጫ ንጽህናቸውን በአግባቡ መጠበቅ ይገባል። ከዚህ ባለፈ ትኩስ ነገሮችን ማጠጣት፣ ንጽህናቸውን መጠበቅ እና  ተጨማሪ ፈሳሽ እንዲወስዱም መክረዋል፡፡ መድኃኒትን በተመለከተም በሐኪም ካልታዘዘ በስተቀር ፀረ ባክቴሪያዎችን (አንቲ ባዮቲክስ) መውሰድ በፍጹም ተገቢ እንዳልሆነ የጤና ባለሙያው ጠቁመዋል። ለአብነትም አሞክሳሲሊን፣ አዚትሮማይሲን፣ ኦግመንቲን የሚባሉ አንቲባዮቲክሶችን  መጠቀም እንደሌለባቸው መክረዋል፡፡  “ለምን?” ከተባለም  እነዚህ ባክቴሪያን እንጂ ቫይረስን የሚያጠፉ መድኃኒቶች ስላልሆኑ ሐኪም እስካላዘዘ ድረስ መጠቀም የተከለከለ መሆኑን አስጠንቅቀዋል፡፡

ለታዳጊዎች እና  ለአዋቂዎች ደግሞ በቂ እረፍት መውሰድን ጨምሮ እንደ ነጭ ሽንኩርት፣ ማር፣ ዝንጀብል ያላቸውን ምግቦች መመገብ የበሽታ መከላከል አቅምን በማሳደግ በሽታውን ለመቋቋም እንደሚያግዝ ተናግረዋል። “ነጭ ሽንኩርት አንዳንድ ቫይረሶችን የመቆጣጠር ባህርይ እንደሚያሳይ በሳይንስም የተረጋገጠ ነው” ሲሉም አክለዋል።

በጋንቢ ጠቅላላ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር ኃይለማርያም አደራ ለአሚኮ በሰጡት መረጃ በሽታውን ለመከላከል እጅን በሳሙና እና በውኃ በየጊዜው መታጠብ በተለይም እጅ ማንኛውንም ነገር ከነካ በኃላ በሚገባ ንጽሕናውን መጠበቅ ሁነኛ መንገድ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ጉንፋኑ ደረጃው ከፍ ብሎ ወደማያቋርጥ ሳል ሲቀየር፣ ከፍተኛ ሙቀት ሲኖር፣ ምግብ አለመውሰድ እና ትውኪያ ሲኖር ሕሙማን ወደ ሕክምና ተቋማት እንዲሄዱ ባለሙያው መክረዋል፡፡ ምክንያት ያሉት ደግሞ በተለይም እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ካሉ ከፍ ላለ ጉዳት ሊያጋልጡ ስለሚችሉ በሕክምና ባለሙያ መታየቱ ይመከራል እና ነው ፡፡

ሰዎች ጉንፋን መሰሉ በሽታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ወደ ሕክምና ጣቢያ በሚመጡበት ጊዜ በሦስት ደረጃ እንደሚታይ ዶክተር ኃይለማርያም ጠቁመዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከጉንፋን ጋር ተደርቦ ሌላም በሽታ ሊኖር ስለሚችል አጠቃላይ ምርመራ ተደርጎ አንደኛ ደረጃ ጉንፋን ከሆነ ምክር ሰጥቶ በቤት ውስጥ እንዲታከም እና እንክብካቤ ማድረግ  እደሚመከር ጠቁመዋል፡፡ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ከደረሰ ግን ሰዎች ለመተንፈስም ስለሚቸገሩ የማሽን እገዛ ስለሚያስፈልጋቸው ሕክምና እንደሚደረግ አስገንዝበዋል፡፡::

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የታኅሳስ 14  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here