ሰባቱ ጨዋታዎች ምን ይነግሩናል?

0
24

በዓለማችን ተወዳጅ የሆነው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ለሀገራት ጨዋታ እረፍት አድርጓል:: ይሄው እረፍት ፕርሚየር ሊጉ ከተጀመረ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑም አይዘነጋም::

በ2024/25 እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ሊቨርፑሎችን (ቀዮቹን) ሻምፒዮን አድርጎ በተጠናቀቀው ዓመት ሊቨርፑሎች ከ38 ጨዋታዎች 84 ነጥቦችን ሠብሥበው ነው ሻምፒዮን የሆኑት::

የቀዮቹ አለቃ አርኔ ስሎት ሊቨርፑልን ከጀርገን ክሎፕ በተረከቡበት ዓመት ባለ ድል መሆናቸው በብዙዎቹ ዘንድ አስወድሷቸዋል:: አርኔ ስሎት ከክሎፕ በተረከቡት ቡድን ላይ ብዙም ተጨዋች ሳያካትቱ ባለ ድል መሆናቸውን ከእሳቸው ይልቅ ክሎፕን የሚያስመሰግን ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም በርካታ ናቸው::

ሊቨርፑሎች ሻምፒዮን በሆኑበት ዓመት ቡድኑ የተገነባው በክሎፕ ነው ቢባልም ቡድኑን አቀናጅተው የመሩት ስሎት ናቸውና ባለ ድሉም ባለ ክብሩም እሳቸው ናቸው:: ስሎት በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊጉ ፍልሚያም ከአምስት ጨዋታዎች አምስቱንም በማሸነፍ ፕሪሚየር ሊጉን በከፍታ መርተውት ነበር::

ቀዮቹ በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ፍልሚያ የመጀመሪያዎቹን አምስት ጨዋታዎች በድል ሲያጠናቅቁ ባለቀ ሰዓት የሚያስቆጥሯቸው ወሳኝ ግቦች ለከፍታቸው መሠረት ነበሩ፤ የስድስተኛ እና የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎቻቸው ግን ለቀዮቹ ቀይ መብራት ያሳዩ እንጂ በድል መንገዳቸው ያስቀጠሏቸው አይደሉም:: እነሱም በሰፈሩት ቁና ዓይነት ባለቀ ሰዓት ግብ እየተቆጠረባቸው ተሸንፈዋል::

ሊቨርፑሎች በክሪስታል ፓላሶች እና በቼልሲዎች በተከታታይ እና በተመሳሳይ የ2 ለ 1 ሽንፈትን ሲያስተናግዱ በሁለቱም ጨዋታዎች የጨዋታ ብልጫ ጭምር ተወስዶባቸው መሆኑ ደግሞ ከፊታቸው ላሉባቸው ጨዋታዎች ሥጋትን የሚደቅኑ ናቸው::

አርኔ ስሎት ለዚህኛው የውድድር ዘመን በርካታ ተጨዋቾችን (ለዚያውም በውድ ዋጋ) ወደ ክለባቸው ቢቀላቅሉም ከአዳዲሶቹ ተጨዋቾች ብዙም ግልጋሎት እያገኙ አይደለም:: አሌክሳንደር አይሳክ፣ ፍሎሪያን ዊርትዝ፣ ሁጎ ኢኪቲኬ፣ ጄርሚ ፍሪምፖንግ እና ሌሎቹም በቀዮቹ መለያ በተጠበቁት ልክ እየተንቀሳቀሱ አይደለም::

በ29 ግቦች የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪና የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ተጨዋች ግብጻዊው ሙሀመድ ሳላህም ዘንድሮ በሜዳ ላይ የሚያሳያቸው እንቅስቃሴዎች ከአምናው ጋር ለንጽጽር የሚቀርቡ አይደሉም:: ደካማ የሚባል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነው:: የዕድሜውን ከሠላሳ መሻገር ተከትሎ በአንፊልድ ድምቀቱ የሚደበዝዝ እንጂ የሚቀጥል አይሆንም የሚሉ አስተያየቶችም ተበራክተዋል::

ሳላህ “ከአዲሶቹ የሊቨርፑል ተጨዋቾች ጋር ደመ ነፍሳዊ የሆነ መናበብን መፍጠር ያልቻልነው ለእነሱ ጊዜ ስለሚያስፈልጋቸው ነው“ ብሏል:: ከአዳዲስ ተጨዋቾች ጋር በአጭር ጊዜ መዋሀድ እንደማይቻል በመጥቀስ ጭምር:: ሳላህ አስፈሪውን የሊቨርፑል የአጥቂ መስመር በቅርቡ እንደሚያሳዩም ገልጿል::

በኒውካስል ዩናይትድ ቤት ራሱን በጉልህ ያሳየው ስዊድናዊው አሌክሳንደር አይሳክ ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ወደ አንፊልድ አምርቶ እስካሁን ይሄ ነው የሚባል ተጽዕኖ መፍጠር አልቻለም:: ዘረ ኤርትራዊው አሌክሳንደር አይሳክ በቀዮቹ መለያ ለጊዜው ያልተሳካለት በክረምቱ የእረፍት ጊዜ በቂ ልምምድና ጨዋታዎችን ባለማድረጉ መሆኑን አለቃው አርኔ ስሎት መስክረውለታል::

ሊቨርፑሎች ከሰባት ጨዋታዎች በአምስቱ በማሸነፍና በሁለቱ በመሸነፍ በ15 ነጥቦች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል:: እስከ ሰባተኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሠንጠረዡን በአንደኛነት የሚመራው አርሴናል ነው:: አርሴናል በሊቨርፑል የ1 ለ 0 ሽንፈትን በማስተናገድ እና ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ነጥብ ተጋርቶ በመውጣቱ ሊጉን በ16 ነጥቦች እየመራው ይገኛል::

ቶተንሃም ሆትስፐርና በርንማውዝ ከሰባት ጨዋታዎች 14 ነጥቦችን ሠብሥበው አርሴናል እና ሊቨርፑልን በቅርብ ርቀት ይከተላሉ:: ማንቸስተር ሲቲ 13፣ ቼልሲ 11 እና ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ 10 ነጥብ መያዛቸውም ቢሆን ውድድሩ ገና በሰባተኛ ሳምንት ላይ ከመገኘቱ አንጻር የዘንድሮውን የዋንጫ ፉክክር ካለፉት ዓመታት በተሻለ የሚያጓጓ አስመስሎታል::

ኦፕታ እና ብዙ የእግር ኳስ ተንታኞች የዘንድሮውን ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አርሴናል የማሳካት የተሻለ ዕድል አለው ብለዋል:: ገማቾቹ አርሴናል ዋንጫ ያነሳል ያሉበትን ምክንያት ሲያስቀምጡ ክለቡ ላለፉት ሦስት ዓመታት በጥሩ ተፎካካሪነት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ እና ክፍተቶቹን የሚደፍኑለት ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ በመቀላቀሉ ነው ብለዋል::

አዲሱ የአርሴናል ማናጀር ጣሊያናዊው አንድሬ ቤርታ ቪክቶር ዮኮሬሽን ጨምሮ ስምንት ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ በማምጣታቸው አርሴናል ከዚህ በፊት የሚታማበትን የቡድን ጥልቀት ችግር ቀርፈውለታል:: ያም ሆኖ ግን በአርሴናል የፊት መስመር ላይ የተጨመሩት ዮኮሬሽ፣ ኤዜ እና ማዱኬ እንደሊቨርፑሎቹ አዳዲስ ተጨዋቾች ሁሉ ለስኬታማነት ጊዜ የሚፈልጉ መስለው ታይተዋል::

የአርሴናሉ አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ዘንድሮ ከቡድኑ ጋር ትልቅ ዋንጫን የማያሳካ ከሆነ ጫና እንደሚበዛበት አያጠራጥርም:: አርሴናልን ወደ ጥሩ ተፎካካሪነት የመለሰው አርቴታ ክለቡን ከትልቅ ዋንጫ ጋር የማያስታርቀው ከሆነ ጠንካራ ቡድን መገንባቱ ብቻውን በክለቡ ለመቆየት ዋስትና እንደማይሆነውም የብዙዎች ግምት ነው::

ማንቸስተር ሲቲ በፔፕ ጋርዲዮላ እየተመራ በእንግሊዝ ኃያል ክለብ መሆኑን አስመስክሯል:: ለአራት ተከታታይ ዓመታት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳት እና የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ማሳካት የአንድ ክለብና የአሠልጣኙ ጥሩ ሥራዎች መገለጫዎች ናቸው ቢባል ስህተት አይሆንም::

ፔፕ ጋርዲዮላ እንደ ዲብሮይን ያለ ምርጥ የመሀል ሞተራቸውን ወደ ናፖሊ ቢሸኙም አምና በጉዳት ምክንያት ያላገለገላቸውን ሮድሪጎን በአግባቡ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ:: በአዲስ ወደ ክለባቸው የቀላቀሏቸው ተጨዋቾችም ቢሆኑ ለቡድኑ ስኬት ቁልፍ ሚናቸውን ይወጣሉ ተብሎ የሚጠበቁ ናቸው፤ በተለይ ጣሊያናዊው የግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ዶናሩማ ብራዚላዊውን ኤድርሰን ተክቶ ኢትሀድ ከደረሰ በኋላ በማንቸስተር ሲቲ ውጤታማነት ላይ አሻራውን ማሳረፍ ጀምሯል::

ማንቸስተር ሲቲዎች ከሰባቱ ጨዋታዎች 13 ነጥቦችን ሠብሥበው ከመሪው አርሴናል በሦስት ነጥቦች ብቻ ዝቅ ያሉ በመሆናቸው ለዋንጫው ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው ክለቦች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው::

ቼልሲዎች የዓለም ክለቦች ሻምፒዮና በሆኑበት ዓመት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግም ውጤታማ ይሆናሉ ከተባሉ ክለቦች ተርታ የሚሰለፉ ናቸው:: ቼልሲዎች ምንም እንኳን በፕሪሚየር ሊጉ ከሰባት ጨዋታዎች ያገኙት 11 ነጥቦችን ብቻ ቢሆንም ይሄው ውጤታቸው ከመሪው ክለብ በአምስት ነጥብ ብቻ ዝቅ ያለ በመሆኑ ከዋንጫ ፉክክሩ ላለመራቃቸው ማሳያ ነው::

በፖርቹጋላዊው ሩበን አሞሪም የሚመሩት ማንቸስተር ዩናይትዶች የአምና ውጤታቸውን ፈጽሞ ሊያስታውሱት አይፈልጉም:: በስፖርቲንግ ሊዝበን ውጤታማ ጊዜን ያሳለፉት ሩበን አሞሪም ኤሪክ ቴን ሃግን ተክተው ኦልድትራፎርድ ከደረሱ በኋላ ውጤታማ መሆን አልቻሉም የአምናው ዩናይትድ ወደ ታችኛው ሊግ ላለመውረድ የሚጫወት ክለብ መሆኑ ብዙ ደጋፊዎቹን አሳዝኗል::

ማንቸስተር ዩናይትድ ለዘንድሮው ፉክክር ቤንጃሚን ሴስኮ፣ ማቲያስ ኩኛ፣ ብሪያን ምቤሞ፣ ግብ ጠባቂውን ሴኔ ላሚንስን እና ሌሎችንም ወደ ክለቡ በመቀላቀሉ ክለቡና አሠልጣኙ ወደ ውጤታማነታቸው ይመለሳሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር፤ እስካሁን ባለው ሂደት ግን ቀያይ ሰይጣኖቹ በታችኛው ሊግ በሚጫወተው ግሪምብስ ታውን ከካራባው ውድድር ገና ከወዲሁ ተሰናብተዋል::

ዩናይትዶች በፕሪሚየር ሊጉ ከሰባቱ ጨዋታዎች በሦስቱ አሸንፈው፣ በአንዱ አቻ ወጥተው እና በሦስቱ ደግሞ ተሸንፈው ከ21 ነጥብ ማሳካት የቻሉት 10 ብቻ ነው:: የአውሮፓ ውድድር የሌለባቸው ዩናይትዶች ጉልበታቸውን ለፕሪሚየር ሊጉ አሟጠው ይጠቀማሉ ቢባልም እስካሁን ያስመዘገቡት ውጤት ግን ያንን የሚያመላክት አይደለም::

ማንቸስተር ዩናይትዶች አሠልጣኝ የሚቀያይሩት ወደ  ታላቁ አሠልጣኝ ሰር ቻፕማን አሌክስ ፈርጉሰን መንገድ የሚወስዳቸውን ሰው ለማግኘት ነው:: እስካሁን ግን ይህንን ምኞታቸውን የሚያሳካ አሠልጣኝ ማግኘት አልቻሉም:: ሩበን አሞሪም ከሰባት ጨዋታዎች 10 ነጥቦችን ይዘው ከመሪው አርሴናል በስድስት ነጥቦች ብቻ ዝቅ ብለው በዋንጫ ተፎካካሪነት ውስጥ ይገኛሉ:: ይሄንን ነጥብ አጥብቦ ወደ ላይ ከፍ ለማለት ደግሞ 31 ቀሪ ጨዋታዎች ከፊታቸው ይገኛሉ::

የማንቸስተር ሲቲው አለቃ ፔፕ ጋርዲዮላ ስለ ዘንድሮው ውድድር ከስካይ ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ “ከሦስት ሳምንት በፊት ሁሉም ሰው ሊቨርፑል በድጋሚ ሻምፒዮን እንደሚሆን ሲናገሩ ነበር፤ አሁን የተፈጠረው ግን ያያችሁት ነው:: የሊጉን ሻምፒዮን እንኳን በሰባት ጨዋታ ከ30 በላይ ጨዋታዎችን አድርገንም መገመት ያዳግታል:: በኔ አስተያየት በርንማውዝ እና ብራይተንን ጨምሮ ብዙ ክለቦች ለዋንጫው ይፋለማሉ” ብለዋል::

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከሀገራት ውድድር በኋላ በስምንተኛ ሳምንቱ ይመለሳል፤ የትኛው ክለብ ጥንካሬውን እንደሚያስመለክተን እና የትኛው ክለብስ የውጤት ቀውስ ይገጥመዋል? የሚለውን ጥያቄ ቀጣዮቹ ጨዋታዎች ምላሽ ይሰጡናል:: የእናንተስ አስተያየት ምንድነው?

 

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here