ሰብልን በወቅቱ በመሰብሰብ ከብክነት መታደግ እንደሚገባ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ አሳስቧል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ታደሰ ማሙሻ ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንደገለፁት በዞኑ በ2016/2017 የምርት ዘመን 497 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 549 ሺህ ሄክታር (ከዕቅድ በላይ) በዘር ተሸፍኗል። ከዚህም 17 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
ለዕቅዱ ስኬታማነት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት ኃላፊው በዚህ ወቅትም የመኸር ሰብል እየተሰበሰበ ነው። የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ ወቅቶ ወደ ጎተራ ማስገባት እንደሚገባም አሳስበዋል። አቶ ታደሰ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት በቆላማው አካባቢ በብዛት ሰብሉ እየተሰበሰበ ነው። ስንዴ፣ ጤፍ እና የጥራጥሬ ሰብሎች ደግሞ በዋናነት ተሰብስበዋል። ደጋማ አካባቢዎች አብዛኛው ምርት ያልተሰበሰበ በመሆኑ ለመሰብሰብ ሲደርስ (ሲደርቅ) በተቀናጀ አሠራር ሰብልን በመሰብሰብ ከብክነት መታደግ እንደሚገባ መክረዋል።
እንደ መምሪያ ኃላፊው ማብራሪያ በዘር ከተሸፈነው ማሳ ውስጥ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ኅዳረ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 266 ሺህ ሄክታር መሬት ሰብል ተሰብስቧል። እየተሰበሰበ ያለውን ማሳም ለመስኖ በማዘጋጀት በዘር እየተሸፈነ ነው።
የተሻለ ምርት ለማግኘት ጊዜን እና ጉልበትን እንዲሁም የግብርና ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ያሳሰቡት መምሪያ ኃላፊው አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን በጥራት እና በፍጥነት መሰብሰብ ይጠበቅበታል። ይህን በማድረግም ምርትን ከብክነት መታደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በዘመቻ መሰብሰብ (ማጨድ)፣ በጥንቃቄ መከመር፣ ሸራ ማልበስ፣ ነፋስ እንዲያገኝ ማድረግ፣ አይጥ እና መሰል ተባይ እንዳይበላው መከታተል ይገባቸዋል ብለዋል።
ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ የምርት ብክነት እንዳይከሰት የደረሱ ሰብሎችን በደቦ (በወንፈል እና በወበራ) መሰብሰብ፣ መውቃት እና በጥንቃቄ ወደ ጎተራ ማስገበት እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም