“ሰው ስትሆን እንዳትረሳ!… ”

0
70

“ቃል የእምነት እዳ ነው” ይላሉ አበው ሲተርቱ፡፡ ቃል የገባ ሰው ያንን የማድረግ ህሊናዊ ግዴታ እንዳለበት የሚያስበው ራሱ ነው፡፡ “አስቀረህ” ብሎ ማንም ላይከሰው  እና ላይወቅሰው የፈቀደውን ያደርጋል፡፡

በሌላ በኩል ሌሎች የሚሰጡንና እኛም የምንቀበለው አደራ ይኖራል፡፡ በዕውቀትም ሆነ በሀብት አቅም ስንፈጥር ሌላ ሰው ማሻገር የምንችልበትን አደራ የትውልድን መሻገር ከሚሹ አባቶች ቃል ይሰጠናል፡፡ ያ ቃል እስኪፈጸም ድረስም የእምነት እዳችን ሆኖ ይቆያል፡፡

ለማድረግ የምንሻው ተግባር ወይም ከሌሎች የሚሰጠን አደራ ታዲያ የራሱ የሆነ መነሻ ይኖረዋል፡፡ ጉዳዩ እንደ ማኅበረሰብና እንደ ሕዝብ ሲሆን ደግሞ ሃሳቡ ይገዝፍና ውጤቱም የጎመራ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕዝባዊ አደራ ተጥሎባቸው ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ሰዎችም ብዙዎች ናቸው፡፡

እኛም በቅርቡ ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ተግባር  ለመዘገብ ወደ በሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ቀጣና አቅንተን ነበር፡፡  መንዝ የሚባለው አካባቢ መንዝ ማማ ፣ መንዝ ላሎ ፣ መንዝ ጌራ፣ መንዝ ቀያ…ናቸው፡፡ ወረዳዎቹ በስም አምስት ይሁኑ እንጅ  ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች በዘለለ በባህላዊ ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች የተሳሰሩ ናቸው፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች ዘመናትን የተሻገረ የመሰረተ ልማት ችግር በመኖሩ ማኅበረሰቡ ዘወትር ጥያቄ ያነሳል፡፡ በነዋሪው ዘንድ ዘወትር የሚነሳው ችግር ደግሞ ከሁሉ በላይ የከፋ የጤና ችግር የሚያጋጥማቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚታከሙበትና ለቀጣናው የተሻለ ነው የሚባለው የመሃል ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል የቁሳቁስ እጥረት   ነው ::ከሆስፒታሉ በላይ የሆነ ችግር  ሲያጋጥም ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለተጨማሪ ህክምና የሚላኩ ህሙማን ሲኖሩ የመንገድ መሰረተ ልማቱ አመቺ ባለመሆኑ ለሌላ ስቃይ ይዳረጋሉ፡፡ እንዲህ አይነት ችግሮች በመኖራቸው ከዚያ አካባቢ ተምረው ከወጡ ምሁራን ባልተናነሰ መንገድ ገፈት ቀማሽ የሆነው ነዋሪው ያለማቋረጥ የቻለውን እየሠራ ጥያቄውን ሲያቀርብ፤  ይረዳናል  ለሚለው የአካባቢው ተወላጅም አደራውን ሲሰጥ ቆይቷል::የዚያን አካባቢ ማህበረሰብ አደራ ተቀብለው ለማገልገል አበርክቶ ካላቸው ሰዎች መካከል አቶ ልኡልሰገድ እርገጤ ቀዳሚው ናቸው፡፡ የተወለዱት በመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ መሃል ሜዳ ከተማ ነው፡፡ አቶ ልኡልሰገድ እንደሚሉት አካባቢውን ለቀው ወደ አዲስ አበባ የሄዱት በሕጻንነታቸው ነው፡፡ ከዚያም ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ወደ አውስትራሊያ የመውጣት አጋጣሚ አግኝተው በዛው እየኖሩ ናቸው፡፡

ከአባታቸው ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎች የአባትና ልጅ ወግ ሲያወጉ አባታቸውን የተወለዱበት  አካባቢ ማኅበረሰብ የመሰረተ ልማትና የትምህርት ቤት ችግር ሲያሳስባቸው እንደነበር ገና በለጋ እድሚያቸው ያስተውሉ ነበር፡፡ ይህ ቁጭት ይሉት ሃሳብ ውስጣቸው አደረ፡፡ ማህረሰቡንና ወላጅ አባታቸውን ሲያሳስባቸው የነበረው ጉዳይም አብሯቸው አደገ፡፡ ኋላም ሀሳቡ ነፍስ ዘርቶ ፣ ቁጭቱም ወደ እልህ አድጎ አበው ”ጋን በጠጠር ይደጋፋል” እንዲሉ  ለዚህ አካባቢ ተቋም አንድ ነገር ለማድረግ ወሰኑ፡፡

ከብዙ  ውጣ  ውረድ  በኋላ  ተሳካላቸው፡፡ ያ  ያበረታቸው  ብርቱ  ቃል  ወሳኝ  የሚባሉ ቁሳቁሶችን ለማሰባሰብ ምክንያት ሆነ፡፡  ካሉበት አውስትራሊያ በገንዘብ እና በተለያዩ መንገዶች 217 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሃብት ማግኘት ቻሉ፡፡

ወደ ልጅነት ጊዚያቸው ስንመለስ ያ በጎ የሃሳብ ጥንስስ ለዛሬ ማንነታቸው መሰረት ነበር፡፡ “ለምን?” ብሎ ለሚጠይቅም ቁም ነገሩ የሚጀምረውም ከዚህ  እንደሆነ ይረዳል::“ድጋፍ ለማድረግ ያነሳሳቸው ነገር ምንድን ነው?” ስንል ጠይቀን፤ ከሰጡን መልስ ያገኘነው “ሰው ስትሆን የመሃል ሜዳ ሆስፒታልን እና የስረ ደጅ ትምህርት ቤትን እንዳትረሳ!” የሚለው የአባታቸውን ቃል ነበር፡፡ ያ የአደራ ቃል አቶ ልኡልሰገድ ዓመታትን እንዲያስቡ ብቻ ሳይሆን ያንንም ወደ ውጤት እንዲቀይሩት አድርጓቸዋል::ኃላፊነት ከባድ ነውና አቶ ልኡልሰገድ ለአምስት ዓመታት ያህል በባእድ ሀገር የህክምናና የትምህርት ቁሳቁስ ሲያሰባስቡ ቆይተዋል፡፡ ይህንን ሲያደርጉም በሀገር ውስጥ ከተለያዩ የሙያው ባለቤቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ስለ እቃዎቹ ጥራትና ዓይነት እየተወያዩ ነበር፡፡ እናም የማኅበረሰቡን የጤና አገልግሎትና የትውልድን ቀጣይ እድል ለማቃናት የሚያስችሉ ቁሳቁሶች ለወረዳው አበርክተዋል፡፡ የአንድ ሰው የአደራ ቃል ፣ የአንድ ሰው የገዘፈ ኃላፊነት ፣ ውጣ ውረድ ያላጣው ጉዞ ፍሬው ለብዙዎች የተረፈ ለመሆን በቃ፡፡

የድጋፉ ተቋዳሽ የሆነው የመሃል ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ከሦስት ነጥብ አምስት ሚሊየን በላይ ተገልጋዮችን ማስተናገድ እንዳለበት ታሳቢ ተደርጎ በ1991 ዓ.ም የተሠራ ነው፡፡ ይህንን የኅብረተሰብ ክፍል ለማስተናገድ የሚያስችል የሰው ኀይልና የቁሳቁስ አቅም ግን አልተሟላለትም ነበር::“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በሰሜኑ ጦርነት ደግሞ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት ደርሶበታል፡፡ ከወድመቱ እንዲያንሰራራና በመጠኑም ቢሆን አገልግሎቱን እየሰጠ ባለበት ሁኔታ የአቶ ልኡልሰገድ ድጋፍ ወደ ተሻለ ምእራፍ እንደሚያሸጋግር የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ወርቅነህ ዘውዴ ነግረውናል፡፡

አቶ ልኡልሰገድ የአባታቸውን አደራ በመወጣት ሆስፒታሉን ስር ከሰደደ የህክምና ቁሳቁስ ችግር እንዲወጣ በማድረጋቸው ሥራ አስኪያጁ አመስግነዋል፡፡  የተደረገው ድጋፍ ለማኅበረሰቡ ተስፋ የፈነጠቀ፣ የባለሙያዎችን የሥራ ተነሳሽነት ከፍ የሚያደረግ ነው ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ላይ የኩላሊት እጥበት ማሽኖች፣ ዘመናዊ አልጋዎች፣ ዲጅታል የራጅ/ኤክስሬይ/ ማሽን እና ሌሎች ዘመናዊ ህክምናዎችን ለመስጠት የሚያስችሉ ግዙፍ የህክምና መሣሪያዎች በአቶ ልኡልሰገድ መበርከታቸውን አረጋግጠዋል:: በርክክብ ሥነ ሥርአቱ “ለተወለድንበት አካባቢ ያለብንን አደራ መወጣት አለብን!” የሚሉት አቶ ልኡልሰገድ፤ የህክምና መሳሪያዎቹ ጥራታቸው የጠበቁ  እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ “ቃል ሳይረሳ ሲፈጸም፣ አደራ ተበልቶ ሳይቀር ሲመለስ፣ የትውልድ ተስፋ ሲለመልም ከዚህ በላይ ደስታ የለም! ይህ ድጋፍ በተደረገበት አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም እንዲህ አይነት ልምድ ቢኖር” በሚል ለሌሎች ወገኖች አቶ ልኡልሰገድ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ይህን ለማድረግ ሂደቱ ቀላል እንዳልነበር የጠቀሱት አቶ ልኡልሰገድ፤ ቁሳቁሶችን ለማሰባሰብ ደርሶ መልስ እስክ 3 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር ድረስ በመኪና የተጓዙበትን ጊዜ ያስታውሳሉ፡፡ አንዳንዶቹንም በከባድ ተሽካርካሪ በውድ ዋጋ አጓጉዘዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የተሰባሰበው የህክምናና የትምህርት ቁሳቁሱን ከቦታው ለማድረስ ከሰባት ወራት በላይ ወስዷል፡፡ ውጣ ውረዱ ከባድ ቢሆንም ግን ከልብ የነበራቸው መሻት ፣ ያንን ለመፈጸም ያደረጉት ትጋት ጠንካራ ስለነበር ለውጤት በቅቶላቸዋል፡፡ ውጥን የነበረው ህልም ፍሬ ከዓመታት በኋላ እውን በመሆን  ከአንድም ለሁለት የሚበቃ ሆነ፡፡

በመንዝ ጌራ ወረዳ ለሚገኝ ስረ ደጅ ለተሰኘ ትምህርት ቤትም ዲጂታል ቤተመጽሐፍት ለማስጀመር የሚያስችሉ የጸሐይ ኀይል ፓኔል ፣ ዴስክቶፕ ኮምፒተሮችና ሌሎች የትምህርት መስጫ ቁሳቁሶች ከኝህ ምስጉን የአካባቢው ተወላጅ ተበርክቷል፡፡

ለግል ጥቅም ሲባል የሆነ ያልሆነውን ሃብት በሚቃረምበት ዓለም ውስጥ ከራስ በላይ ለሌላ ሰው ፣ ከጥቂቶች በላይ ለሕዝብና ለሀገር አስቦ መሥራትና በቦታው ተገኝቶ  ማስረከብ የሚችሉ ወገኖች ከብዙዎች ውስጥ የሚገኙ እድለኞች ናቸው፡፡ ለዚያም ነው አቶ ልኡልሰገድ “ይህ የተሰጠሁትን አደራ ጀመርሁ እንጂ የመጨረሻዬ አይደለም” የሚሉት፡፡ ለዚህም ነው በቀጣይም ሌላ ኃላፊነት እንዳለባቸው የነገሩን፡፡ ከተቀባዮች ይልቅ ትጉህ ሰዎች ለሌሎች ማድረግን እንደ እድል ነው የሚቆጥሩት፡፡ እናም ይላሉ አቶ ልኡልሰገድ “ሁሉም ሰው ቢያንስ ለተወለደበት አካባቢ የሚችለውን ቢያደርግ መልካም ነው” በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል::እኛም ሠርተው ላላለፉ ቁጭትን ፣ ዛሬ ላይ ለሚገኙ እድል መስጠትን ፣ ለቀጣይ ትውልድ ደግሞ ሰው ሆኖ አደራ ተቀባይ መሆንን ለማሳየት እንደ አቶ ልኡልሰገድ  ዓይነት መልካም ሰዎች ያስፈልጋሉ! እንላለን::

(በላይ ተስፋዬ)

በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here