ታህሳስ 21 ቀን 1949 ዓ.ም ለምዕራብ አፍሪካዋ ቡርኪናፋሶ ታሪካዊ እለት ነበረች፤ የራሷን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ጀግና ቶማስ ኢሲዶር ኖኤል ሳንካራን አስገኝታለችና፡፡
ከነፃነት በኋላ ከልጅነት እስከ ወጣትነት ዘመኑ አራት መፈንቅለ መንግሥቶች የተፈራረቁባት፣ መረጋጋት የራቃት፣ ድህነቷ የጠለቀ፣ ከድጡ ወደ ማጡ የምታዘግም የአሳዛኝ ሀገሩን፣ የአፐር ቮልታን ሁኔታ እያየ ያደገ ነገር በልጅነቱ የገባው አንድ ቀን ሊገለጥ ጊዜ የሚጠብቅ ታላቁ ሰው በደጅ ቆሞ ነበር፥ ወጣቱ ቶማስ ኢሲዶር ኖኤል ሳንካራ፡፡
በአስር ወንድሞች እና እህቶች መሀል የተገኘው ቶማስ ሳንካራ ከሁለት እህቶቹ ቀጥሎ የቤተሰቡ ሦስተኛ ልጅ ነበር። ከእርሱ ቀጥሎ ስምንት ወንድሞች እና እህቶች ተወልደዋል። ታላቅ ወንድም እንደመሆኑ ታናናሾቹን የመንከባከብ እና የመጠበቅ ኃላፊነት ይሰማው ነበር።
አባቱ ሳምቦ ጆሴፍ ሳንካራ በወቅቱ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት አስተዳደር ውስጥ በፖሊስነት ከሚያገለግሉ ጥቂት አፍሪካውያን አንዱ ነበሩ። በዚህ ምክንያት ከሌሎች አፍሪካውያን ልጆች በአንጻራዊነት የተሻለ አኗኗር ነበረው። ከሌሎች አፍሪካውያን የፖሊስ ቤተሰቦች ጋር የሳንካራ ቤተሰብ በተለየ ስፍራ በጡብ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበር። ይህ ለሳንካራ የቡርኪናፋሶን የተለያዩ አካባቢዎች በልጅነቱ ጠንቅቆ እንዲያውቅ እና ከብዙ ሰዎች ጋር እንዲተዋወቅ ረድቶታል፡፡
ሀገሩ አፐር ቮልታ ነሐሴ 5 ቀን 1960 ዓ.ም ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ተላቃ ነፃነቷን ስትቀዳጅ እርሱ ገና የአስራ ሁለት ዓመት ብላቴና ነበር። ይህን ታሪካዊ ሀቅ በዓይኑ አይቷል፡፡ አይቶም በደስታ አብሮ ከታላላቆቹ ጋር ጨፍሯል። ደግሞም በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ በተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግሥቶች የሚፈራረቁ አምባገነን መሪዎች ሀገሩን እንደ ግል ርስታቸው ሲመዘብሩና በሕዝቧ ላይ የግፍ መዓት ሲያወርዱ ተመልክቶ አዝኗል፡፡
በተለይ ደግሞ በካቶሊክ እምነቱ የታነፀው ምግባሩ ሀቀኛ የሶሻሊስት ተከታይ እንዲሆን እንዳገዘው ይታመናል። በሌላ በኩል አባቱ ሀገራቸውን በውትድርና ማገልገላቸው የሳንካራን ፖለቲካዊ አመለካከት ተራማጅ እንዲሆን ትልቅ ድርሻ ነበረው። በኑሮ መጓደል ልጆቿ እንዳይከፋቸው ሌት ተቀን ሳትሰለች ያሳደገችው እናቱም በሳንካራ ሕይወት ሰፊ ቦታ አላት።
ሳንካራ ትምህርት የጀመረው በቦብዲዮላሶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ አብዛኛውን ጊዜውን ለትምህርት ተግባራት ይሰጣል፣ በተለይ በሒሳብ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋ አቅሙን ለማሳደግ ይጥር ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱም በሒሳብና ፈረንሳይኛ ቋንቋ ይበልጥ ውጤታማነቱን አሳደገ። ትኩረቱን ትምህርቱ ላይ ያደረገው ቶማስ በትርፍ ጊዜውም ትያትር መመልከት፣ ፊልም ቤት መሄድ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግን የሕይወቱ አንድ አካል አደረገ።
በዚህ መሀከል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና ለመውሰድ ዝግጅት ላይ ሳለ ሀገሪቱ ሁከት ውስጥ ገባችና የመንግሥት ለውጥ ተደረገ። አዲሱ መንግሥት ታዲያ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የወታደራዊ አካዳሚ በመክፈት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሦስት ተማሪዎችን ለመኮንንነት ስልጠና እንደሚፈልግ በራዲዮ ሲሰማ ተወዳድሮ በላቀ ውጤት አካዳሚውን ተቀላቀለ፣ በ17 ዓመት ዕድሜው የአባቱን ሙያ ወረሰ፡፡
ከሦስት ዓመታት በኋላ ቶማስ ሳንካራ የወታደራዊ አካዳሚ ትምህርቱን አጠናቀቀ። ከዚያም ለተሻለ የመኮንንነት ስልጠና ወደ ማዳጋስካር፣ አንፅራቤ ሄደው እንዲሰለጥኑ ከተመረጡ ሁለት ብልጫ ውጤት ካላቸው ተመራቂዎች አንዱ ቶማስ ሳንካራ ነበር። ሳንካራ ጥቅምት ወር 1969 ዓ.ም ማዳጋስካር በደረሰበት ወቅት፣ እርሱ ከሚያውቃት ድሃ፣ ደረቃማ ሀገር የተለየች ሀገር አጋጠመው። ማዳጋስካር በአትክልት የተሞላች ሀገር ነበረች። ዋና ዋና ከተሞቿ በታሪካዊ ህንፃዎች፣ ሀውልቶች፣ እና በአትክልት ስፍራዎች የተሞሉ ናቸው፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ የእድገት ደረጃዋ በሚታይ ሁኔታ ከፍተኛ ነበር።
በአንትስራቤ ወታደራዊ አካዳሚ ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ከወታደራዊ ትምህርቶች በላይ ያለፈ ነበር። በተቋሙ ውስጥ ከወታደራዊ ትምህርቱ ጎን ለጎን ስለ ግብርናው የኢኮኖሚ ዘርፍ የማጥናት ዕድል አግኝቷል። በተለይም እንዴት የሰብል ምርትን መጨመር እና የገበሬዎችን ሕይወት ማሻሻል እንደሚቻል ግንዛቤ አግኝቷል። ሰራዊቱን እንዴት በልማት ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻልም ከማዳጋስካር ብሔራዊ ሰራዊት ልምድ ቀስሟል። የአካዳሚ ትምህርቱን በሚያጠናቅቅበት ዓመት በማዳጋስካር መንግሥትን ለመለወጥ የተነሱ ሕዝባዊ አመፆችን አጠቃላይ ሂደት በሚገባ ለማጤን እድል አጋጥሞታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የካርል ማርክስንና የቭላድሚር ሌኒንን መፃሕፍት በማንበቡ በአመራር ዘመኑ ላራመደው አብዮታዊ ርዕዮተ-ዓለም ፍልስፍና ተጽዕኖ አሳድሮበታል፡፡
ቶማስ ሳንካራ ከሁለት ዓመታት ስልጠና በኋላ የቡርኪናቤ ወታደራዊ ዕጩ መኮንን ማዕረግ ለብሶ ወደ ሀገሩ አፐር ቮልታ ተመልሷል፡፡ በወቅቱ እድሜው ሀያ አራት የነበረ ሲሆን የመቶ አለቅነት ማእረግ ተሰጠው። ወዲያውም አዳዲስ ምልምል ወታደሮችን እንዲያሰለጥን የመጀመሪያ ተልዕኮውን ተቀብሎ ወደ ባብዳዮሎሱ ማሰልጠኛ ሄደ። ምልምሎችን በብቃት በማሰልጠን ለማብቃት በትጋት ይሰራ ነበር። በዚህ መካከል ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ አይን ውስጥ ያስገባው ታሪካዊ ሁኔታ ተከሰተ። ነገሩ ወዲህ ነው፣ በአፐር ቮልታ እና በማሊ መካከል የወሰን ይገባኛል ውዝግብ ተነሳ፡፡ ፍጥጫው ተካርሮ በ1974 ዓ.ም ማሊ አፐር ቮልታን ለመውጋት ሰራዊቷን ወደ ድንበር አዘመተች፡፡ ለማሊ ትንኮሳ አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ቶማስ ሳንካራ ከሌሎች በርካታ መኮንኖች ጋር እንዲዘምት ተደረገ። በመሆኑም ሳንካራ አነስተኛ ጦሩን እየመራ በወሰደው እርምጃ የማሊን ግዛት ዘልቆ በመግባት የተወሰኑ የማሊ ወታደሮችን ከበርካታ የጦር መሳሪያ ጋር ማርኳል፡፡ ከቀናት በኋላ ጦርነቱን ለማቆም ስምምነት ላይ በመደረሱ ሳንካራ በድል አድራጊነት ወደ ኦጋዱጉ ሲመለስ በሕዝቡ የጀግና አቀባበል ተደረገለት፡፡
ቆራጥ ወታደርና ጀግና የጦር መሪ መሆኑን በተግባር ያስመሰከረው አብዮተኛው ቶማስ ሳንካራ በጦርነቱ ባሳየው ድንቅ ጀብዱና የመሪነት ሚና ዝናው ከፍ አለ፡፡ ሆኖም ከዓመታት በኋላ ሳንካራ ስለ ጦርነቱ ያልተጠበቀ ትችት ሰነዘረ። ጦርነቱ የመሪዎችን ስልጣን ለማስጠበቅ የተደረገ፣ ወንድማማች ጭቁን ሕዝቦችን እርስ በርስ ያጋደለ ‹‹ትርጉም የለሽ፣ አላስፈላጊ ጦርነት›› እንደነበር ተናገረ፡፡ ይህ ንግግሩም የፖለቲካ አመለካከቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የማደጉ ውጤት ተደርጎ በብዙዎች ዘንድ ታመነ፡፡
ሆኖም ሳንካራ በማሊ ጦርነት ለሰራው ጀብዱ በ1976 ዓ.ም በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ለሚገኘው “ፖ” ለተባለው የኮማንዶ ማሰልጠኛ ማዕከል ከፍተኛ የኮማንዶ አዛዥነት ሹመት ተጎናፀፈ፡፡ ሳንካራ ኃላፊነቱን ከተረከበ በኋላ በወታደሩ እና በሲቪሉ ማህበረሰብ መካከል ተፈጥሮ የቆየውን የሻከረ ግንኙነት ለማሻሻልና መግባባትን ለመፍጠር ችሏል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ወታደሩ በየአካባቢው የልማት እንቅስቃሴ ከሲቪሉ ማህበረሰብ ጎን እንዲሰለፍ አድርጓል፡፡
ሁለተኛው የውጭ እድል በ1976 ዓ.ም የአየር ወለድ ኮማንዶነት ስልጠና ለመከታተል ወደ ሞሮኮ ራባት የተጓዘበት ነበር። ይህ አጋጣሚም ከብሌስ ኮምፓዎሬና ከሌሎች ሰልጣኝ የሀገሩ ልጆች ጋር የመተዋወቅ እድል ፈጥሮለታል፡፡ በዚህ የስልጠና ወቅትም ‹‹የኮሚኒስት ጓዶች ስብስብ›› የተባለውን ግራ ዘመም ሚስጢራዊ ድርጅት ማቋቋም ችሏል፡፡ ምስጢራዊው ድርጅት ቶማስ ሳንካራን ጨምሮ ሄንሪ ዞንጎ፣ ጃ ባፕቲስ ቡካሪ ሊንጋኒ እና ብሌስ ኮምፓወሬን አካትቷል፡፡ ከዚያም ቶማስ ሳንካራ ስልጠናውን አጠናቆ በ1980 ዓ.ም ወደ አፐር ቮልታ ተመለሰ፡፡
ነገር ግን አፐር ቮልታ 1980ዎቹን የጀመረችው በመንግሥት ተቃውሞ እና አመፅ ነበር። በተለይ አምባገነን ስርዓትን የሚቃወም የላብ አደሮች ዓመፅ የተለመደ ክስተት ሆኖ ነበር፡፡ ከዚህ አይነቱ ተደጋጋሚ ተቃውሞ በኋላ ኅዳር 25 ቀን 1980 ዓ.ም በኮሎኔል የሚመራ የከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ቡድን በላሚዛና አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግሥት ፈፀሙ፡፡ ወዲያው ቡድኑን የመራው ኮሎኔል ሳይ ዜርቦ ስልጣን ላይ ወጣ፡፡ አዲሱ ወታደራዊ መንግሥት በሀገሪቱ ስርአት እንደሚያፀና እና ሙስናን ከስሩ እንደሚነቅል ቃል ገባ። ለዚህ አቋሙ መጀመሪያ ላይ ብዙ ድጋፍ ነበረው። ተራማጅ ብሔርተኛ ሲቪል ሚኒስትሮችን ለማካተት እና የንግዱን ማህበረሰብ ድጋፍ ማግኘትም ችሏል።
በዚህ መፈንቅለ መንግሥት ቶማስ ሳንካራ አልተሳተፈም። ምንም እንኳ አንዳንድ ወጣት መኮንኖች የተቃወሙ ቢሆንም እና ሳንካራ እና የቅርብ ጓደኞቹ አዲሱን ወታደራዊ አገዛዝ ለገባቸው ቃሎች ሲሉ የታገሱት ቢሆንም እንኳ፣ ስልጣን በያዘው ኮሎኔል ፖለቲካዊ ወግ አጥባቂነት ላይ ግን ጥርጣሬ ነበራቸው። ቡድኑ የዝቅተኛ መኮንኖችን ድጋፍ ለማግኘትም የማማለል ጨዋታ ጀምሮ ነበር።
በመሆኑም የቶማስ ሳንካራን አንደበተ ርዕቱነት እና በወጣቱ ዘንድ ያለውን ከፍተኛ ተደማጭነት የተረዳው ወታደራዊ መንግሥቱ ቶማስን አንድም በችሎታው ሊጠቀምበት፣ በሌላም ጎኑ ከአጠገቡ ይዞ በዓይነ ቁራኛ ለመከታተል እንዲያመቸው የተለያዩ ሹመቶችን ሰጠው።
በመጀመሪያ በወታደራዊ የአመራር ችሎታው እውቅና ለመስጠት በማሰብ ጥር 1980 ዓ.ም የካፒቴንነት ማእረግ ተሰጠው እና የሰራዊቱ የዘመቻ ክፍል ኃላፊ እንዲሆን ተሾመ። ወዲያው ብዙ ሳይቆይ ለሚንስትርነት ተጠየቀ። መስከረም 9 ቀን 1981 ዓ.ም የመረጃ ሚኒስትር እንዲሆን ሹመት ቀረበለት፡፡ ነገር ግን ቶማስ ሳንካራ አልተቀበለውም። እጅግ በጥንቃቄ በተመረጡ ቃላት ምንም አይነት የፖለቲካ ስልጣን ላለመቀበል መወሰኑን የሚገልጽ ደብዳቤ ለፕሬዚደንት ዜርቦ ፃፈ። አንዳንድ አብዮታዊ የቅርብ ጓደኞቹ እንዲገፋበት አበረታቱት፤ አንዳንድ ወዳጆቹም ነገሩን በቀጥታ መቃወም እርሱን እና ጓዶቹን ለበቀል እርምጃ እንደሚያጋልጣቸው በመግለፅ ሹመቱን እንዲቀበል ገፋፉት። በመጨረሻም እያቅማማም ቢሆን ሹመቱን ለመቀበል ተገደደ።
ቶማስ ሳንካራ በመንግሥት የመረጃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ የነበሩ የበፊት ልማዳዊ አሰራሮችን በዘመናዊ አሰራሮች ለመለወጥ ብዙ ትግል አድርጓል፡፡ የአገልግሎት ጥራትን አስጠብቋል፡፡ ዋጋቸው ውድ በሆኑ ተሽከርካሪዎች የመገልገልን አላስፈላጊነት አስገንዝቧል፡፡ ከሁሉም ይበልጥ ደግሞ በመንግሥት አስተዳደር የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ፊት ለፊት ይጋፈጥ ነበር፡፡
በተጨማሪም ሳንካራ በኃላፊነት የሚመራው መስሪያ ቤት በጋዜጦች ላይ ያደርግ የነበረውን የቅድመ ምርመራ ወይም የሳንሱር አሰራር በማስቀረት የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር ታገለ፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግል ጋዜጦች የፈለጉትን መረጃ በነፃነት እንዲፅፉ አበረታቷል፡፡ አንዳንድ የመንግሥት እና የግል ጋዜጦች ደፍረው የሙስና ቅሌቶችን ማጋለጥ ጀምረው ነበር። የተጋለጡ የአገዛዙ ባለስልጣናትም ሳንካራን ጨምሮ ሌሎች ሀላፊዎችን እስከ ማስፈራራት፣ ማሳደድ እና ማሰር ደርሰው ነበር። በዚህ እና መሰል አቋሙ ፕሬዚደንት ዜርቦ በሳናካራ ላይ ደስተኛ አልሆኑም፡፡ ቶማስ ሳንካራም እያደር ከዚህ መንግሥት ጋር አብሮ መስራት አልፈለገም፡፡
በዚህ የተነሳ ቶማስ ሳንካራ የመልቀቂያ ማመልከቻ ለፕሬዝዳንቱ አስገባ። በተጨማሪም ሚያዝያ 24 ቀን 1982 ዓ.ም በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ በነበረ የቀጥታ ስርጭት ላይ ቀርቦ ከወታደራዊው መንግሥት ጋር አለመግባባቱን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ዘወትር ሕዝብ ላይ አፈ ሙዝ ከሚደግን አምባገነን መንግሥት ጋር አብሮ መስራት እንደማይችል በመጥቀስ በገዛ ፍቃዱ ከኃላፊነቱ መልቀቁን አስታወቀ፡፡
ሆኖም ይህ ከሆነ ከወራት በኋላ ኅዳር 7 ቀን 1982 ዓ.ም ሜጀር ዶክተር ጃን ባብቲስት ኦድራጎን የሳየ ዜርቦን መንግሥት በመፈንቅለ መንግሥት አስወግዶ ስልጣን ላይ ወጣ፡፡ አዲሱ መንግሥት በሀገሪቱ ዕድገት ለማምጣት ‹‹የህዝብ ደህንነት አስጠባቂ ምክር ቤት›› በሚል ስያሜ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት አቋቋመ፡፡
ሜጀር ዶክተር ጃን ባብቲስት ኦድራጎ የሕዝብን ድጋፍ ለማግኘት በማሰብ በቀድሞው አስተዳደር የታገዱትን የመረጃ እና የማህበራት ነፃነት ፈቀዱ፡፡ በጥር 1983 ዓ.ም ሻምበል ቶማስ ሳንካራ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መሾሙ ደግሞ የለውጡ ሌላ መልክ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ፣ ሹመቱ ሁለት መልክ ያለው የመንግሥት አስተዳደር ፈጠረ፡፡ በአንድ በኩል ፕሬዚደንቱ የቀድሞውን የፖለቲካ ስርዓት ማስቀጠል የሚፈልጉ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ሳንካራ ደግሞ በአብዮታዊ አስተሳሰብ የተቃኘ አዲስ አሰራር ይዞ ብቅ አለ፡፡
አዲሱ ሳንካራ የተሾመበት ቦታ ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ጠበቆችና አብዮተኞች ጋር እንዲተዋወቅ አግዞታል፡፡ በተለይ ከኩባው ፊደል ካስትሮና ቼ ጉቬራ እንዲሁም ከሞዛምቢኩ ሳሞራ ማሸል ጋር አስተዋወቀው፡፡ ይህ ሁኔታ የግራ ዘመም ፖለቲካዊ አስተሳሰብን ሙሉ በሙሉ እንዲላበስ አግዞታል፡፡
ይሁን እንጂ፣ አብዮተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንካራ በቅኝ ተገዥነት ተመሳሳይ ታሪክ ካላቸው አልጀሪያ፣ ሊቢያ፣ ሰሜን ኮርያ፣ ጋናና ናይጀሪያ ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መፍጠሩ በሾመው የሀገሪቱ ፕሬዚደንት አልተወደደለትም፡፡ በተለይ ደግሞ በሙአማር ሞሃመድ ጋዳፊ ሙሉ ወጭ ሊቢያን መጎብኘቱ ፕሬዚደንቱ ከእኔ እውቅና ውጭ ነው በሚል ምክንያት ደስተኛ አልነበሩም፡፡
እርስ በርሱ የሚቃረን የአመራር ዘይቤ የሚታይባቸው ሳንካራና ፕሬዚደንት ባፕቲስት ኦድራጎ በሂደት በመካከላቸው ያለው ልዩነት እየሰፋ መጣ፡፡ ፕሬዚደንቱም በሳንካራ ወጣ ያለና ያልተለመደ አስተሳሰብ መስማማት አልቻሉም፡፡ በተጨማሪም ሳንካራ ፀረ-ኢምፔሪያሊዝምን ከማቀንቀኑና ከጊዜ ጊዜ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነቱ እየጨመረ ከመሄዱ ጋር ተዳምሮ በሾመው አምባገነን መንግሥት ሊወደድ አልቻለም፡፡
ኮማንደር ጃን ባፕቲስት ኦድራጎ የሀገሪቱ በሚቃረኑ ሃሳቦች መመራት ለብሔራዊ ደህንነት አደጋ መሆኑን በመግለጽ ግንቦት 17 ቀን 1983 ዓ.ም ቶማስ ሳንካራን ከስልጣን አንስቶ አሰረው፡፡ የሳንካራን አመለካከት የሚደግፉ ሄንሪ ዞንጎ እና ጃን ባፕቲስት ቡካሪ ሊንጋኒ የተባሉ የቅርብ ጓደኞቹም አብረው ወህኒ ወረዱ፡፡ የሳንካራ ዘብጥያ መውረድም በሕዝቡ በተለይም ደግሞ በተማሪዎች፣ በሰራተኛው መደብ እና በወታደሩ ዘንድ ከባድ ተቃውሞ አስነሳ፡፡ በአጋጣሚ ከእስር የተረፈው የቅርብ ጓዱ ብሌስ ኮምፓዎሬ በ “ፒኦ” ወታደራዊ ማሰልጠኛ ውስጥ የሚገኙ ወታደሮችን ለተቃውሞ ማስተባበር ጀመረ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ፕሬዚደንት ጃን ባፕቲስት እና ቶማስ ሳንካራ በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ነሐሴ 4 ቀን 1983 ዓ.ም ለውይይት ተቀመጡ፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዚህ መካከል በሳንካራ ቅርብ ጓደኛ ብሌስ ኮምፓወሬ የሚመራና ወደ ሁለት መቶ ወታደሮች የሚገኙበት ‹‹የኮሚኒስት ወጣቶች መኮንን›› የተባለ ቡድን መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡
ነገር ግን ፕሬዚደንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለስምምነት ጉባዔ በተቀመጡበት አጋጣሚ ከግቢ ውጭ የተኩስ እሩምታ ተሰማ፡፡ ተኩሱ የተከፈተው ደግሞ በሳንካራ የትግል አጋሮች በእነ ብሌስ ኮምፓዎሬ ነበር፡፡ ይህን የተገነዘበው ቶማስ ሳንካራ ከፕሬዚደንቱ ጋር ድርድር ላይ በመሆኑ ተኩሱን በፍጥነት እንዲያቆሙ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ ሆኖም ሻምበል ኮምፓዎሬ ‹‹ዘመቻውን አንዴ ጀምረነዋልና ዓላማችንን ሳናጠናቅቅ የምናቆምበት ምክንያት አይኖርም›› የሚል ምላሽ ሰጠ፡፡
ከመቅጽበት የኮምፓዎሬ ታማኞች ኦጋዱጉ የሚገኘውን ሬድዮ ጣቢያ በቀላሉ ተቆጣጠሩ፡፡ ቀጥለውም ቤተ መንግሥቱን ካለምንም ደም መፋሰስ በእጃቸው አስገቡ፡፡ ከዚህ በኋላ የትግል አጋራቸውን ካፕቴን ቶማስ ሳንካራን ከእስር ነፃ ማውጣት ነበር ዕቅዳቸው፤ ይህም ተሳካላቸው፡፡ ይህ ትዕይንት አፐር ቮልታ ነፃነቷን ከተጎናጸፈች በኋላ የገጠማት አራተኛው መፈንቅለ-መንግሥት መሆኑ ነው፡፡ ሀገሪቷን የተቆጣጠረው ቡድን አባላትም ‹‹የብሔራዊ አብዮት ምክር ቤት›› በማቋቋም ቶማስ ሳንካራ እንዲመራቸው ሀገራቸውን አስረከቡት፡፡
ይቀጥላል
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የታህሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም