በዓለም የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ስማቸው በደማቁ ከተጻፈ ጥቂት ከዋክብት መካከል የሴሊን ዲዮን በቀዳሚነት ይጠቀሳል:: በኃይለኛው ድምጿ፣ ልብ በሚነኩ ዜማዎቿና መድረክ ላይ በምታሳየው አስደናቂ ብቃት የምትታወቀው ይህች ካናዳዊት ድምፃዊት፣ ከሙዚቃው ዓለም ባሻገር በፍቅር፣ በእናትነትና በፅናት የተሞላ ሕይወቷ ብዙዎችን የሚያበረታታ ነው።
በአንዲት ትንሽ ከተማ ያደገች ሕጻን ልጅ ዘፋኝ መሆን እንደምትፈልግ ወሰነች። እናም ሁሉንም ነገር አደጋ ላይ ጥሎ ኮከብ የሚያደርጋት ታላቅ አዘጋጅ አገኛት። አጀማመሯ ቀልድ መስሎ በካናዳ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ታላቅ እና ተወዳጅ ከሆኑት ዘፋኞች አንዷ ለመሆን በቅታለች።
ሴሊን ዲዮን የተወለደችው እ.አ.አ 1968 በካናዳ ከሞንትሪያል ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው ሻርለማኝ፣ ኩቤክ ዳርቻ ነው። እ.ኤ.አ. በ2016 ከተማዋ ስድስት ሺህ ነዋሪዎች የነበሯት ሲሆን በዋነኝነት ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነበሩ።
አስተዳደጓ በትልቅ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ዲዮን ከ14 ልጆች ታናሿ ነበረች። አባቷ ሥጋ ሻጭ ነበሩ። እናቷ ተሬዝ ደግሞ የቤት እመቤት። ሙዚቃ በዲዮን ቤተሰብ ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው።
የመጀመሪያው የህዝብ ትርኢቷ አምስት ዓመቷ ላይ በወንድሟ ሚሼል ሰርግ ላይ በመዝፈን ነበር የተጀመረው። በ12 ዓመቷ ዲዮን የመጀመሪያዋ ዘፈን (ሴ ኔታይ ኩን ሬቭ) ህልም ብቻ ነበር የሚል መጠሪያ ነበረው።
“እስከ ዛሬ የነበረኝ ብቸኛ ህልም ዝነኛ መሆን እና ሙሉ ህይወቴን መዝፈን እና ለመጫዎት በመላው ዓለም መጓዝ ነበር” ስትል ለምንትሪያል ጋዜጣ እ.አ.አ በ1991 ተናግራ ነበር። እናም ያ ሁሉ ሕልሟ እውን ሆኖ ዓለምን ዞራለች። በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ ነግሳለች።
የሴሊን ዲዮን እናት ሕልም ብቻ ነበር የሚለውን የመጀመሪያውን የዘፈን ቅጂን ለታዋቂው የሙዚቃ ሥራ አስኪያጅ ረኔ አንጀሊል ላከችለት። እሱም የዘፋኟን እምቅ ችሎታ አይቶ ወደ ቢሮው ጋበዛት።
ከዚያም እርሳስ ይዛ እንደ ማይክሮፎን አስመስላ መዝፈን ጀመረች። “የሰማሁት ነገር እንድስቅ በቂ ነበር። ከዚህ በፊት ሰምቼ የማላውቀው ልዩ ድምፅ ሰማሁ” ሲል ድምጿን አድንቆላት ነበር።
የሴሊን ዲዮን ሕይወት የተለወጠው እና ዓለም ስሟን በልቡ ያተመው ከ ረኔ አንጀሊል ጋር መገናኘት ነበር። ከዚህ ሰው ጋር ባትገናኝ ኖሮ ምናልባትም ስሟን ላናውቀው እንችል ነበር። ረኔ አንጀሊል በኋላ የሴሊን ዲዮን ባል ሆኖ ልጆች ወልደው ሕይወቱ በ2016 እ.አ.አ በካንሰር ሕመም እስኪያልፍ ድረስ የፊትም፣ የጀርባም አጥንቷ ነበር።
ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት እንደተመለከታት ያስታውሳል። “ሴሊን ዲዮን ትሑት ትንሽ ልጅ ነበረች። እናቲቱ ሁሉንም ነገር ትናገራለች፣ ልጅቷ ግን አንድም ቃል አትናገርም ነበር” ሲል አንጀሊል ተናግሯል።
“ከዚህ በፊት ሰምቼ የማላውቀው ልዩ ድምፅ ሰማሁ” ያለው አንጀሊል የዲዮንን ተሰጥኦ በጣም አመነው። የመጀመሪያ አልበሟን ለማዘጋጀት ገንዘብ ማሰባሰብ አቃተው። የራሱን ቤት ብድር አስይዞ የሪከርድ ድርጅት መሰረተ። ሁለቱ በጋራ በዓለም የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጎልቶ የሚጠቀስበትን ጉዞ ጀመሩ።
የሴሊን ዲዮን የሙዚቃ ሕይወት በቁጥሮች ሲለካ አእምሮን በሚያስደንቅ ደረጃ ላይ ይገኛል:: እስከ ዛሬ ድረስ 27 የስቱዲዮ አልበሞችን (15 በፈረንሳይኛ እና 12 በእንግሊዝኛ) ለአድማጮቿ አበርክታለች:: በርካታ የኮንሰርት አልበሞችም አሏት። በዓለም ዙሪያ ከ220 ሚሊዮን በላይ የአልበም ቅጂዎችን በመሸጥ ከምንጊዜውም ከፍተኛ ሽያጭ ካስመዘገቡ አርቲስቶች አንዷ እንድትሆን አስችሏታል:: ለዚህም ስኬቷ ማሳያ የሚሆኑ ከ1000 በላይ ሽልማቶችን ተቀብላለች:: ከእነዚህም መካከል 5 የግራሚ ሽልማቶች፣ 2 የአካዳሚ (ኦስካር) ሽልማቶች (ለፊልም ማጀቢያ ሙዚቃዎች) እና በርካታ የቢልቦርድና የአሜሪካ የሙዚቃ ሽልማቶች ይገኙበታል::
በፈረንጆች በ1991 የወጣው የዲስኒ አኒሜሽን ፊልም (ቢዊቲ ኤንድ ዘ ቢስት) ማጀቢያ ዘፈን መጀመሪያውን ትልቅ ተወዳጅነት እና የግራሚ ሽልማት አሰጥቷታል። እ.ኤ.አ. በ1995 የወጣው ዲዩክስ የተሰኘው አልበሟ በፈረንሳይኛ ቋንቋ እስከ ዛሬ ከተሸጡት አልበሞች አንዱ ሆኖ ተመዝግቦላታል።
እ.ኤ.አ. በ1997 የጀምስ ካሜሮን ታይታኒክ ፊልም ሲወጣጣ በከፍተኛ ደረጃ ዓለም አቀፍ ዝናዋ ከፍ አለ። በዲዮን የተዘፈነው የፊልሙ ማጀቢያ ማይ ኸርት ዊል ጎ ኦን ዘፈን የእሷ መለያ ሆነ። በምርጥ ኦሪጅናል ዘፈን ኦስካርን ሽልማት አስገኝቶላታል። የግራሚ ሽልማቶችን በጅምላ አግኝቷል። ጎልደን ግሎብ ሽልማትን ተቀብሏል። እስከ ዛሬ ከታዩት እጅግ በጣም ከተሸጡ የሙዚቃ ነጠላ ዜማዎች አንዱ ሆኗል። በኋላም እንደተናገረችው መጀመሪያ ዘፈኑን አልወደደችውም ነበር። ግን የስሟ መጠሪያ ሆነላት።
በዓለም ሙዚቃ ላይ ያስቀመጠችው አሻራ በቀላሉ የሚገመት አይደለም:: እንደ ማይ ኸርት ዊል ጎ ኦን፣ ዘ ፖወር ኦፍ ላቭ” እና ቢኮዝ ዩ ላቭድ ሚ ያሉ ዜማዎቿ በክብ ልብ ውስጥ የታተሙ አሻራዎቿ ናቸው። በተለይም በላስ ቬጋስ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የመድረክ ትርኢት (ሬዚደንሲ ሾው) በማስተዋወቅ የከተማዋን የመዝናኛ ገጽታ የቀየረች ፈር ቀዳጅ ነች:: ለስኬቷ ዋናው ምስጢር ተፈጥሮ የቸራት ድንቅ የድምፅ ችሎታዋ ቢሆንም፣ ከጀርባዋ እንደ ጥላ ሆኖ ይመራት የነበረው ባለቤቷና ስራ አስኪያጇ ሬኔ አንጀሊል ድርሻ እጅግ ከፍተኛ ነበር::
የሴሊንና የሬኔ ታሪክ ከስራ ግንኙነት የዘለለ ጥልቅ የፍቅር ተምሳሌት ነበር:: በ12 ዓመቷ ድምጿን ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ በችሎታዋ ያመነባት ሬኔ፣ ቤቱን አስይዞ የመጀመሪያ አልበሟን ሰርቶላታል:: በመካከላቸው የነበረው የ26 ዓመት የእድሜ ልዩነት ሳይገድባቸው፣ ፍቅራቸው አብቦ በ1994 በደማቅ ስነስርዓት ተጋቡ:: ሬኔ ለሴሊን የሕይወት አጋር ብቻ ሳይሆን፣ የሙያዋ መሀንዲስና የቅርብ ወዳጇም ነበር::
ሴሊን በሙያዋ ላይ በነበረችበት ወቅት፣ እናት ለመሆን የነበራትን ጥልቅ ፍላጎት ለማሳካት ስራዋን ለሁለት ዓመታት አቋርጣለች:: በተደጋጋሚ የህክምና ሙከራዎች ካደረገች በኋላ የመጀመሪያ ልጇን ሬኔ ቻርልስን ወለደች:: ከዓመታት በኋላም መንታ ልጆቿን ኤዲ እና ኔልሰንን ስትወልድ፣ ለቤተሰቧ ቅድሚያ እንደምትሰጥ በተግባር አሳይታለች:: ይህ ውሳኔዋ በዝናና በገንዘብ ሊለካ የማይችል የእናትነት ጥሪ ምን ያህል የበላይ እንደሆነባት ያሳያል:: እ.ኤ.አ በ2016 ሬኔ በካንሰር ሕመም ሲሞት፣ የሕይወቷን ትልቁን ምሰሶ ብታጣም ለልጆቿ ስትል በፅናት ቆማለች:: ባሏ በታመመ ጊዜ ስራዋን አቋርጣ አስታማዋለች።
“የጥንካሬዬንና የኃይሌን እያንዳንዱን ክፍል ለባለቤቴ ፈውስ መስጠት እፈልጋለሁ፣ እናም ይህንን ለማድረግ ይህን ጊዜ ለእርሱና ለልጆቻችን መስጠት አስፈላጊ ነው” ስትል ነበር ያስታወቀችው። እንዲሁም “በመላው ዓለም የሚገኙትን አድናቂዎቼን በሙሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ፣ ስላስቸገርኳቸው፣ እና ለፍቅራቸውና ድጋፋቸው በጣም አመሰግናለሁ” ብላም ነበር። ባለቤቷ ከሞተ ከሁለት ቀናት በኋላ፣ ዲዮን ወንድሟን ዳንኤልን በካንሰር አጣች።
ከባለቤቷ መሞት በኋላ ሁሉም ነገር የተስተካከለ በሚመስልበት ወቅት፤ እ.አ.አ በታሕሳስ ወር 2022 ሴሊን ከባድ የጤና መቃወስ ገጠማት:: ስቲፍ ፐርሰን ሲንድረም በተባለ የነርቭ በሽታ እንደተያዘች በይፋ አስታወቀች:: ይህ በሽታ ጡንቻዎችን በማጠንከርና በማቆራጠጥ እንቅስቃሴን የሚገድብ ነው። ድምፅን ጨምሮ የሰውነትን አጠቃላይ ቁጥጥር ያሳጣል:: በሽታው ለመራመድ እንድትቸገር ከማድረጉም በላይ፤ ሕይወቷ የሆነውን የመዝፈን ችሎታዋን አደጋ ላይ ጥሎታል::
ይህ ፈተና ግን የሴሊንን የትግል መንፈስ ሊሰብረው አልቻለም:: ህመሟን በይፋ ለዓለም በማሳወቅ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመሳሳይ ፈተና ውስጥ ያሉ ሰዎችን አስተምራለች:: ከምርጥ የህክምና ባለሙያዎች ጋር በመስራት፤ በየቀኑ ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችንና ህክምናዎችን በመውሰድ በሽታውን እየተዋጋች ትገኛለች:: በቅርቡ በለቀቀችው “እኔ ሴሊን ዲዮን ነኝ” (አይ አም ሴሊን ዲዮን) በተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ላይ፣ ከህመሙ ጋር የምታደርገውን እውነተኛ ትግል ሳትደብቅ በማሳየት፣ ተጋላጭነት ኃይል መሆኑን አስተምራለች:: ወደ መድረክ ተመልሳ ለአድናቂዎቿ ለመዝፈን ያላትን ጥልቅ ጉጉት ደጋግማ ትናገራለች::
የሴሊን ዲዮን ታሪክ የላቀ የሙዚቃ ችሎታ ታሪክ ብቻ አይደለም:: ይልቁንም፣ አንድ ሰው በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ እንዴት በፍቅር፣ በቤተሰብ ፍቅርና በማይናወጥ ፅናት ማለፍ እንደሚችል የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው:: ድምጿ ለጊዜው ቢታፈንም፣ የሕይወት ዜማዋ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ አስተማሪና አነቃቂ ሆኖ ይደመጣል::
ማረፊያ
ከአንገቱ ስር ልዋል
በእቅፌ ታቅፌ …..
አይኖቼን ጨፍኜ ስሩ ተለጥፌ፣
ነፍስ ያውም ነፍሴ
ሀሴት ለመንፈሴ፣
ጠረኑን እየማግኩ
ምጌም እያጣጣምኩ፣
በእርካታ መንፈስ ሽምጥ ጋልቤ
በሀሴታ እርካብ ላይ ኩታዬን ደርቤ፣
በፍቅሩ ቀልጫ አቅሌን ሳትኩለታ
በአንገቱ ስር ሽታ፡፡
በሱራፌል ጌትነት
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የህዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


