ሰላም የሰፈነበት አካባቢን በመፍጠር ሁለንተናዊ ልማትን ለማፋጠን ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተጠቆመ፤ ለዚህ ደግሞ ሴቶች ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ ነው የተጠየቀው።
“የሴቶች የተደራጀና ሁለንተናዊ ተሳትፎ፤ ለዘላቂ ሰላምና ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ የሴት አደረጃጀቶች አመራርና አባላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል፤ በውይይቱም የሰላም አስፈላጊነትን አጽንኦት በመስጠት ሴቶችም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ መቅረቡን ከመምሪያው ኮሙኒኬሽን የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ግጭት በሌለበት ጊዜ መንግሥታት ከወታደራዊ ወጪዎች ይልቅ ለጤና አጠባበቅ፣ ለትምህርትና ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና ለመሳሰሉት አስፈላጊ አገልግሎቶች ተጨማሪ ገንዘብ መመደብ ይችላሉ። ለዚህ ዋስትናው ሰላም ሲሆን ሴቶች ደግሞ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሰፍን ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። በሰላማዊ ሂደቶች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎም ግጭት ውስጥ የገቡ አካላትን ወደ ተሻለ የሰላም ስምምነቶች እና ከፍተኛ የፖለቲካ አፈፃፀም ደረጃዎች እንዲመጡ ያደርጋሉ።
በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው ውይይት የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ህጻናትና ማሕበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ሰብለ ዘውዱ የከተማዋና አካባቢዋ ሰላም ተጠብቆ እንዲቆይ የሴቶች ሚና የላቀ ነው ብለዋል፤ ኃላፊዋ እንዳሉት በከተማዋ አሁን ለተገኘው ሰላም የተከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሴቶች በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ተንቀሳቅሰዋል። በቀጣይም ሴቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማፋጠን የአካባባያቸውን ሰላምን በዘላቂነት በማስጠበቅ የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም