ስለ መስኖ ምን እንማር?

0
177

በዓለማችን የመስኖ ልማት ከተጀመረ ከስምንት ሺህ ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ  ኦፕቲማ (www.optima.inc) ከተሰኘው እና መስኖን ትኩረት አድርጎ መረጃን የሚያስነብበው የመረጃ ምንጭ ይጠቁማል፡፡ መስኖ ልማት በተለይም በተፈጥሮ ውኃ አጠር በሆኑ ሀገራት በስፋት ይከናወናል፡፡ የመስኖ ልማት ከዝናብ  በተጨማሪ የከርሰ ምድር ውኃን እና የውኃ አካላትን በመጠቀም በተለያዩ ወራት የማምረት ዘዴ ነው፡፡

በመስኖ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ሁለት ዓይነት የመስኖ ውኃ አጠቃቀም ዘዴን ይከተላሉ፤ እነዚህም  ውኃውን  በመርጨት  እና  ወደ ማሳ በቱቦዎች አማካይነት በግፊት በማስገባት ሰብሎችን እና  አትክልቶችን የሚያጠጡበት  ዘዴ ነው፡፡ ውኃን ጠልፎ ወደ ማሳ በማስገባት የሚደረገው የመስኖ ልማት ምንም እንኳን ኋላ ቀር አሠራር  ቢሆንም በአፍሪካ የሚዘወተረው ግን ይሄው ነው፡፡

በዓለማችን ላይ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሀገራት የመስኖ ልማትን ይጠቀማሉ፡፡ ሕንድ እና ቻይና ደግሞ መስኖን በስፋት ከሚጠቀሙ ሀገራት ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የዓለማችንን ሁለት ሦስተኛ ሕዝብ በጉያቸው አቅፈው የያዙት ሀገራቱ የመስኖ ልማትን ባይጠቀሙ ኖሮ ሕዝባቸውን በምግብ ራሱን እንዲችል ማድረግ በተሳናቸው ነበር፡፡

ሀገራቱ በስፋት ሩዝ፣ በቆሎ እና ስንዴ በመስኖ እንደሚያለሙ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ ከሰብል ልማቱ በተጨማሪ የተለያዩ አትክልቶችን አልምተው ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ኑያዊ እገዛ በማድረግ አርሶ አደሮቻቸው  ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችለዋል፡፡ እነዚህ ሁለት በርካታ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ሀገራት ለመስኖ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ከመስጠታቸውም በተጨማሪ የመስኖ ልማትን የሚያግዙ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የአርሶ አደሮቻቸውን እና የሸማቾችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስለመቻላቸውም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

በዓለማችን ላይ የጠብታ መስኖን በመጠቀም ግንባር ቀደም ከሆኑ ሀገራት መካከል እስራኤል አንዷ ናት፡፡ እስራኤል የጠብታ መስኖን በዘርፉ በሰለጠኑ ኢንጂነሮቿ አማካይነት የጀመረችው ”ችግር ብልሃትን ይወልዳል” የሚለውን የኛ ሀገር ብሂል በተግባር ያሳየችበት ነው፡፡

እስራኤል በረሃማነት የሚያጠቃት ሀገር ብቻ ሳትሆን በተፈጥሮ የውኃ ሀብትን ካልታደሉ ሀገራት ውስጥ አንዷ ናት፡፡ እስራኤል ታዲያ ይህንን ችግሯን እጅ እና እግሯን አጣምራ  “አሜን!” ብላ አልተቀበለችውም፡፡ ዘርፈ ብዙ ልሂቃንን በማፍራት የታደለችው እስራኤል ኢንጂነሮቿ ያላትን አነስተኛ የውኃ ሀብት እያንዳንዷን ጠብታ ለመስኖ ልማት በማዋል እንድትጠቀም እያደረጓት ይገኛሉ፡፡

እስራኤል አግሪ (www.israelagri.com) የተሰኘው የመረጃ ምንጭ እንዳስነበበው እስራኤል አነስተኛ የውኃ ሀብቷ በምንም መልኩ እንዲባክን አትፈቅድም፡፡ አንድን የውኃ ሀብት እስከ ሦስት ጊዜ ለተለያዩ ተግባራት  በመጠቀምም እስራኤልን የሚስተካከላት ሀገር የለም፡፡ ለመጸዳጃ ቤት ግልጋሎት የዋለ የውኃ ሀብቷን ሳይቀር እያጣራች እና እያከመች ለተለያዩ አገልግሎቶች በመጠቀም የዓለማችን ግንባር ቀደሟ ሀገር ሆናለች፡፡

በተመሳሳይ አውስትራሊያም የውኃ እጥረት ባሉባት ግዛቶቿ የጠብታ መስኖን በመጠቀም ዜጎቿ በግብርና ምርታቸው ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለውጪ ገበያ እንዲያመርቱ ማድረግ የቻለች ሀገር ናት፡፡ ስፔን፣ አሜሪካ፣ ሕንድ እና ቻይናም በጠብታ መስኖ ልማት ስማቸው በግንባር ቀደምነት ከሚጠሩ ሀገራት ተርታ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ በስፋት የተለመደው የመስኖ ዓይነት ከውኃ አካላት ውኃን ጠልፎ ለመስኖ የማዋል ኋላ ቀር ዘዴ ነው፡፡ የአፍሪካን የምግብ ሥርዓት በዘላቂነት ማደግን ትኩረት አድርጎ የሚሠራው አግራ (ARGA) የተሰኘው ድርጅት ይፋ እንዳደረገው  የአፍሪካ አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች የዝናብ ውኃ ጥገኞች ናቸው፡፡ ሀገራቱ 50 ከመቶ የምግብ ሰብላቸውን የሚያመርቱትም በዝናብ ውኃ ነው፡፡

እንደ መረጃው ከሆነ በአፍሪካ መስኖ ቢያንስ 50 በመቶ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል አቅም አለው።   ይሁን እንጂ በአህጉሪቱ ያለው የምግብ ምርት በዝናብ ላይ የተመሠረተ ነው።  በአሁኑ ወቅት በመስኖ እየለማ የሚገኘውም ከስድስት በመቶው አልተሻገረም።

ከዓለም ባንክ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ደግሞ በአፍሪካ ካሉ ሀገራት ናይጄሪያ፣ ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ግብጽ እና ደቡብ አፍሪካ በመስኖም ይሁን በዝናብ የሚለማ ሰፊ መሬት ያላቸው ሀገራት ተብለው ከአንድ እስከ አምስተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡ እነዚህ ሀገራት ምንም እንኳን የሚለማ ሰፊ መሬት ቢኖራቸውም በመስኖ ከማልማት አንጻር ግብጽን የሚስተካከላት ሀገር እንደሌለ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በአፍሪካ ትልቁ የመስኖ ግድብም የግብጹ አስዋን ነው፡፡ በአስዋን ግድብ ግብጽ ከምታለማው የመስኖ ልማት ቀጥለው ደግሞ የደቡብ አፍሪካው ቫልሀርትስ እንዲሁም የዚምባቡየው ካሀራ ቦሳ የመስኖ ግድቦች ናቸው፡፡

በሀገራችንም ሆነ በክልላችን በርካታ የመስኖ ግድቦች ቢኖሩም በተለያዩ ሰበቦች በሙሉ አቅማቸው እያለሙ አይገኙም፤ እንደውም ድንበር ተሻጋሪው የዓባይ ወንዛችን የሀገራችንን ለም አፈር ጠራርጎ በመውሰድ በአስዋን ግድብ በኩል ፈርኦኖቹን (ግብጻውያንን) እያጠገበ ይገኛል፡፡

በኢትዮጰያ የግብርና ምርትን ለማሳደግና የሀገሪቱን ሕዝብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከተነደፉ ስትራቴጂዎች ውስጥ የመስኖ ልማትን ማስፋፋት ይጠቀሳል፤ ይሁን እንጂ የመስኖ ልማትን በታቀደለት ልክ ለመሥራት እንቅፋት የሆኑ በርካታ ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ይስተዋላሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቅ፣ የተጠናቀቁትም ቢሆኑ የግንባታ ችግር ያለባቸው ሆነው መገኘታቸው፣ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ብልሽት እና ሲበላሹ ለመጠገን  የሙያተኛ እጥረ፣ ለጄኔሬተሮች የነዳጅ እጥረት፣ በዘርፉ የሠለጠኑ ሙያተኞች እጥረት፣ የመስኖ ጠቀሜታን በአርሶ አደሮች ሥነ ልቦና ውስጥ ማስረጽ አለመቻል፣ በስፋት በመስኖ ለሚያለሙ አርሶ አደሮች የገበያ ትሥሥር አለመፍጠር እና ሌሎችም ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። እነዚህን ችግሮች በማንሳት የመስኖ ሥራዎችን ጎታች ናቸው ሲል የፌዴራሉ መስኖ እና ቆላማ አከባቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያ በመስኖ የሚለማ ከአምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት እንዳላት ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በክረምት እና በበጋ ያለማቋረጥ የሚፈሱ ወንዞች እና ሌሎች የውኃ ሀብት ያላት ሀገራችን በመስኖ ልማት በተፈጥሮ ውኃ ከሌላቸው እንደ እስራኤል ካሉ ሀገራት ጋር መፎካከር አለመቻሏ በእጅጉ የሚያስቆጭ ነው፡፡ ሀገራችን በአፍሪካ ካሉ በርካታ የሚታረስ መሬት ካላቸው ሀገራት ውስጥ ስሟ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ ቢሆንም የመስኖ ልማታችን ግን  በበቂ ሁኔታ ላይ የሚገኝ አይደለም፡፡

ግብጽ በአስዋን ግድብ ብቻ እያለማች በዓለም ላይ ከሚገኙ ፍራፍሬ እና አትክልት ላኪ ሀገራት ውስጥ  ስሟ በቀዳሚነት ሲጠራ፣ የዓባይ ወንዝ መነሻዋ ኢትዮጵያ እንደ አዋሽ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌ፣ ባሮ፣ አኮቦ፣ ተከዜ፣ ላንጋኖ፣  ጣና እና ሌሎችን ተፈጥሯዊ የውኃ ሀብት ይዛ ከመስኖ ልማት በብዙ ርቀት ላይ መገኘቷ ያሳዝናል፡፡

በሀገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለመስኖ ልማት እየተሰጠ ያለው ትኩረት የሚያበረታታ ቢሆንም አሁንም ብዙ ነገሮች እንደሚጎሉን ከግብርና ቢሮዎችም ሆነ ከቆላማና መስኖ ቢሮ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ በአማራ ክልል እየተገነቡ የሚገኙት እንደ ርብ እና መገጭ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደታቸውን ጨርሰው ወደ ልማት እንዲገቡ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here