ከትንንሽ ንግዶች ተነስተው የሪል ስቴት ግንባታ ድርጅት መሥርተዋል:: ለዚህም ጠንካራ የሥራ ባሕል እንዲያዳብሩ እና ሥራን ሳይንቁ እንዲሰሩ አድርገው ወላጆቻቸው ስላሳደጓቸው እንደሆነ ራሳቸው ይናገራሉ:: ከንግዱ ዓለም ባሻገር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በንግድ አስተዳደር ይዘዋል፡–አቶ በሱፈቃድ ተስፋዬ:: አቶ በሱፈቃድ የዚህ እትም የበኩር እንግዳችን ናቸው::
የልጅነት ጊዜ እና የትምህርት ሁኔታዎ ምን ይመስላል?
የተወለድኩት በሰሜን ሸዋ በረኸት ወረዳ 07 ቀበሌ የምትባል ቦታ ነው:: ቤተሰቦቼ በግብርና ነበር የሚተዳደሩት:: ሁለት ወንድሞች እና አራት እህቶች አሉኝ:: ወላጆቼ በትምህርቴ ጠንክሬ ደህና ደረጃ ላይ እንድደርስ ፍላጎት ነበራቸው:: በዚህም መሠረት ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በዛው በበረኸት ወረዳ ነው የተማርኩት:: ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በምንጃር ሸንኮራ አረርቲ ከተማ ተከታትያለሁ:: የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት እንደጠበኩት ሊሆን አልቻለም:: በኋላ ግን በርቀት ተምሬ በንግድ እና አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪ ይዣለሁ:: አሁን ደግሞ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪየን ለመያዝ እየተማርኩ ነው ያለሁት::
ወላጆቻችን ያልተማሩ አርሶ አደሮች ቢሆኑም ሁሉም ልጆቻቸው ትምህርታቸውን በሚገባ እንዲከታተሉ ቁጥጥር ያደርጉ ነበር:: ከትምህርት ቤት መልስ ጊዜያችንን በዋዛ ፈዛዛ እንዳናጠፋ ይከታተሉናል:: ሥራ እና የቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ እንድናተኩር ከፍተኛ ድጋፍ እና ቁጥጥር ያደርጉ ነበር::
ወደ ንግዱ ዓለም እንዴት ገቡ?
ወላጆቼ የሥራ ባሕል እንዳዳብር ብዙ ጥረዋል:: በዚህ ምክንያት ትምህርቴን እየተማርኩ ትንንሽ ንግዶችን እሞክር ነበር:: ከአራተኛ ከፍል ጀምሮ ከረሜላ፣ ሙዝ እና የመሳሰሉትን እሸጥ ነበር:: ወላጆቻችን በግ ወይም ፍየል አንድ አንድ ይሰጡናል፤ ያንን አርብተን ወደ ከተማ ወስደን እንሸጥ ነበር:: ይሄ ወረት ቋጥሬ ወደ ትንንሽ ንግዶች መግባት እንድችል አድርጎኛል:: ከዚህ በተጨማሪ እህል ከተሰበሰበ በኋላ የሚቀረው ቃርሞሽ የሚባል አለ፤ እሱን ሰብስበን እንሸጥ ነበር:: ቤተሰቦቹ ገንዘብ የመስጠት አቅም ነበራቸው። ነገር ግን በራሴ ጥረት እንድፍጨረጨር እና ጠንካራ ሠራተኛ እንድሆን ይፈልጉ ነበር:: በመሆኑም ቀጥታ በገንዘብ መደገፍን አያበረታቱም:: ሁሉም ልጅ በጥረቱ ደህና ደረጃ እንዲደርስ ነበር ፍላጎታቸው::
ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ የተለያዩ ሸቀጦችን ገዝቼ እሸጥ ነበር:: ቀጥሎ ከበረኸት ወረዳ ቦሎቄ፣ ሸንኮራ እና አትክልቶችን እየገዛን የሁለት ቀን ጉዞ ተጉዘን ምንጃር ሸንኮራ አምጥተን እንሸጥ ነበር:: የአንስሳት ነጋዴ አጎቶች ነበሩኝ። ከእነሱ ጋር ፍየል እና በግ እነግድ ነበር::
በኋላ የሶላር ኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን እና መብራቶችን መሸጥ ጀመርኩ:: ቀጥሎ ደግሞ ሞተር ሳይክል እና ባጃጆችን አስመጥቼ መሸጥ ጀመርኩ:: በኋላ ደብረ ብርሃን፣ ምንጃር ሸንኮራ እና ሸዋ ሮቢት እንዲሁም አዲስ አበባ ቅርንጫፎችን መክፈት ቻልኩ:: ከ300 ብር እስከ 50 ሺህ ብር የሚያወጡ የሶላር ኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በገጠራማ ክፍሎች ሳይቀር እሸጥ ነበር:: ሞተር ሳይክሎችን ደግሞ ለግል ድርጅቶች እና ለመንግሥት ተቋማት አቀርብ ነበር::
ንግድ ስትጀምር የነበሩ ፈተናዎች ምን ምን ናቸው?
ወደ ትንንሽ ንግዶች ስገባ ፈተና ከነበሩ ነገሮች ውስጥ አንዱ የመጓጓዣ አገልግሎት እንደልብ አለመኖር ነበር:: ከበረኸት ወረዳ ወደ ምንጃር ሸንኮራ ሸቀጦችን ይዘን ስንመጣ አብዛኛውን ጊዜ በእግር ነበር ጉዞ የምናደርገው:: ከመንገዱ ርዝመት እና አሰልቺነት ባሻገር ትርፉ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም:: ለምሳሌ አንድ ኩንታል ቦሎቄ ተሸክመህ ሁለት ቀን በእግርህ ተጉዘህ የምታተርፈው 15 ብር አካባቢ ነው:: ይህችን በላብህ ያገኘሃትን ገንዘብም ሽፍታ መንገድ ላይ አግኝቶ ሊቀማህ ይችላል:: አካላዊ ጉዳትም ሊያደርስብህ ይችላል፤ እስከ ሞትም ድረስ ያጋጥማል:: ከዚህ ውጪ ልጅነት ስለነበር ብዙ እንቅፋቶች የምላቸው የሉም:: ወደ ሪል ስቴት ዘርፍ ስገባ ብዙ ፈተናዎች ገጥመውኛል::
ወደ ሪል ስቴት ንግዱ እንዴት ገቡ?
ለረዢም ጊዜ የቆየሁት በኤሌክትሮኒክስ እና በሞተር ሳይክል ንግድ ነው፤ ይሄን ሥራ ከ2007 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ሠርቼበታለሁ:: በመሃል ግን ቦታ እየገዛሁ ቤት በመሥራት እሸጥ ነበር:: የድለላ ሥራም እሞክር ነበር:: ምንጃር ላይ ከ48 በላይ፣ በበረኸት ዘጠኝ አዲስ አበባ ሰባት፣ ደብረ ብርሃንም በተመሳሳይ ቁጥር ቤቶችን ገምብቼ ሼጫለሁ:: የቤት ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተገነዘብኩ:: በአጋጣሚ ደግሞ በሪል ስቴት ዘርፍ የተሰማራ የቤተሰብ አባል ነበረኝ፤ “እሱ ለምን ይህን ሥራ ሕጋዊ ፈቃድ አውጥተህ ወደ ሪል ስቴት ቀይረህ አታስኬደውም” ብሎ መከረኝ:: በየትኞቹ አካባቢዎች ብሠራ ውጤታማ እሆናለሁ የሚለውን አጠናሁ፤ የሌሎች ሪል ስቴት ኩባንያዎችን ተሞክሮም በደንብ ቀሰምኩ:: በ2013 ዓ.ም በ52 ሚሊየን ብር ካፒታል ወደ ሪል ስቴቱ ግንባታ ገባሁ::
ወደ ሪል ስቴት ዘርፉ ለመግባት ፈተናዎች ምን ምን ነበሩ? እንዴት አለፋችሁት?
በመጀመሪያ ደረጃ በወረዳ፣ በዞን እና በክልል ደረጃ ስለ ሪል ስቴት ዘርፍ በቂ ግንዛቤ አለመኖሩ ችግር ነበር:: እኔም ራሴ ሪል ስቴት እቅዱን ሳወጣ ከወረዳ አልፎ ዞን እና ክልል ደረጃ ቢሮክራሲው ይሄዳል ብየ አላሰብኩም ነበር:: በወረዳ ደረጃ ጉዳዩ ይፈጸማል ብየ ነበር የገመትኩት:: ሂደቱን እንደጀመርኩ በወረዳ ደረጃ አያልቅም በዞን ደረጃ ነው የሚፈጸመው ተባለ:: ያለው መረጃ እና አጠቃላይ ሂደቱ ወደ ዞን ተላከ:: በዞን ደረጃ አያልቅም ተብሎ ወደ ክልል ተላከ:: በዚያ ደግሞ ለአንድ ዓመት ሲጓተት ቆየ:: ይህ እንዲሆን ያደረገው ግልጽ መመሪያ እና አዋጅ አለመኖሩ ነው:: እኔን ጨምሮ፣ ማኅበረሰቡ፣ የመንግሥት ተቋማት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ስለ ሪል ስቴት ተገቢው ግንዛቤ ስላልነበራቸው ትልቅ ፈተና ሆኖብን ነበር::
ሌላኛው ዋና ችግር የሰላም ጉዳይ ነው:: ከህወሃት ጦርነት ጀምሮ አሁን እስካለው የክልሉ አለመረጋጋት በሥራችን ላይ አወንታዊ ተጽዕኖ ነበራቸው:: ሌሎች ፈተናዎች መቋቋም ቢቻል እንኳ ሰላም ከሌለ የተፈለገውን መሥራት አይቻልም:: አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማጓጓዝ የሰው ኃይልን እንደ ልብ ለማግኘት ሰላም ዋናው ነገር መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው::
ከላይ ከተጠቀሱት ባሻገር ለስሚንቶ ፋብሪካዎች እና ለሌሎች ግብዓት አምራች ድርጅቶች እንዲያቀርቡልን ቅድመ ክፍያ ያደረግን ቢሆንም እስካሁን ግብዓቶችን ያላደረሱን አሉ:: ለዚህም በዋነኛነት የሚያነሱት በየአካባቢው ግጭቶች መኖራቸውን ነው::
የካሳ ክፍያ ችግርም ሌላው ፈተና ነው:: መንግሥት ይህን ጉዳይ አላመቻቸልንም:: ራሳችን ነን ለአርሶ አደሩ የምንከፍለው:: ለአርሶ አደሩ ከ120 ሚልዮን ብር በላይ ከፍለናል:: ሊዝ ክፍያም አለብን:: የባንክ ብድር ስላልተመቻቸልን ችግሩን የበለጠ የከፋ ያደርገዋል:: ከዚህ በተጨማሪ ፋብሪካዎች ትክክለኛ ደረሰኝ ስለማይሰጡ ለበለጠ የግብር እዳ ዳርጎናል:: ስሚንቶ ጠጠር፣ አሸዋ እና ብረት ስንገዛ በትክክለኛው ዋጋ ከመጻፍ ይልቅ ዝቅ አድርገው ደረሰኙን ይሠሩልናል:: ይህ ደግሞ ላልተገባ የግብር እዳ ይዳርገናል:: ለምሳሌ አንድ ከረጢት ስሚንቶ በ2100 ብር ገዝተን ደረሰኝ የሚቆርጡልን በ500 ብር ነው::
ይቀጥላል
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም