ስለ አመክሮ ምን ያውቃሉ?

0
238

አመክሮ ማለት ምን ማለት ነው? ታራሚዎች በአመክሮ የሚለቀቁት ምን መስፈርቶችን ሲያሟሉ ነው?… አመክሮ የማይጠየቅባቸው የወንጀል ድርጊቶች የትኞቹ ናቸው? ለሚሉት ጥያቄዎች በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የይቅርታ ቦርድ ኃላፊ አበበች አዳነ ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ኃላፊዋ እንደሚሉት አመክሮ ማለት የሕግ ታራሚዎች በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች የተወሰነባቸውን ቅጣት በመፈፀም ላይ እያሉ  በሚያሳዩዋቸው መልካም ሥነ ምግባሮች የቅጣት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ  በሕግ መሠረት ከማረሚያ ቤት የሚለቀቁበት ሥርዓት ነው፡፡

ለመሆኑ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ውስጥ እንዲቆዩ  ከተወሰነበቸው ጊዜ ቀድመው በአመክሮ እንዲወጡ የሚያስችሏቸው መስፈርቶች ምን እንደሆኑ ለኃላፊዋ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ እንደ ኃላፊዋ ገለጻ  ታራሚዎች በአመክሮ ለመለቀቅ በክልሉ ሰላም እና ደህንነት በወጣው መመሪያ ቁጥር  1/2003 አንቀጽ 4 ላይ እንደተቀመጠው የፈፀሙት የወንጀል ድርጊት በፍርድ ቤቶች ታይቶ ከተወሰነባቸው የእስራት ቅጣት ውስጥ ሁለት  ሦስተኛውን እንዲሁም  የእድሜ ልክ ፍርደኛ ከሆኑ ደግሞ 20 ዓመት ከቆዩ በኋላ እነሱን ጨምሮ ቤተሰብ እና የሚገኙበት ማረሚያ ቤት በአመክሮ እንዲፈቱ ጥያቄ ማቅረብ ይችላል፡፡

ይሁንና ታራሚዎች ሕጉን መሰረት አድርገው የማረሚያ ቤት ቆይታቸውን ብቻ  ታሳቢ አድርገው “የአመክሮ ተጠቃሚ ልሁን?” የሚል ጥያቄ ስላቀረቡ  ብቻ የዕድሉ ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡

ታራሚዎች ጥያቄያቸው መልስ የሚያገኘው አስፈላጊ የሆነውን የነፃነት ቅጣት እና የጥንቃቄ ርምጃ በመፈፀም ላይ እያሉ በሥራቸው እና በፀባያቸው የተረጋገጠ መሻሻል ካሳዩ፣ ለደረሰው ጉዳት ካሳ እንዲከፍሉ በፍርድ ቤት የተወሰነውን  ከተበዳይ ወይም ከመንግሥት ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት ካሳ ለመክፈላቸው ማረጋገጫ ካቀረቡ፣ አመላቸው /ፀባያቸው/ በመልካም ሁኔታ ለመኖር እንደሚያስችላቸው በማረሚያ ቤት የተቋቋመው አጣሪ ቡድን ካመነበት፣ ታራሚው ከአሁን በፊት  በማረሚያ ቤት ውስጥ ከዚህ በፊት ያላመለጡ እና ለማምለጥ ያልሞከሩ፣ በፍርድ በድጋሚ ያልታሰሩ፣ ቀደም ሲል የወንጀል ድርጊት ስለመፈፀማቸው ማስረጃ  የሌለባቸው ብቻ ሲሆኑ ነው፡፡

አመክሮ ለመስጠት ከእነዚህ መስፈርቶች በዋናነት ታራሚዎች  በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የነበረው ፀባያቸው/አመላቸው/ እና ሌሎች  ተግባሮቻቸው ተገምግሞ እና ተተንትኖ ከ100 ውጤት 75 እና በላይ ካመጡ እንደሆነም ኃላፊዋ ገልፀዋል፡፡ እነዚህም፦

ታራሚው በማረሚያ ቤት ቆይታው መልካም ሥነ ምግባር ያለው  እና ምንም አይነት የዲሲኚሊን ግድፈት ያላሳዬ መሆኑ በማህበሩ ከተረጋግጠ፤

በማረሚያ ቤት ያሉ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች በሚሰጡት የጽሑፍ ማስረጃ የባህሪ ለውጥ ያመጣ መሆኑ ሲረጋገጥ፡፡

ከማረሚያ ቤት ታራሚዎችን ለማነጽ እና ለማረም ተብሎ ከሚሰጡ የቀለም፣  የሙያ… ሥልጠናዎች ቢያንስ በአንድ ሙያ ሠጥልኖ ማስረጃ ያለው፣ በሚመለከተው ክፍል ማስረጃ የተሰጠው ወይም ማረሚያ ቤቱ ምንም የሙያ ስልጠና ያልሰጠ መሆኑ ሲረጋገጥ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

እነዚህን መስፈርቶች አሟልቶ በአመክሮ ለመለቀቅ ጥያቄ መቅረብ ያለበት በመመሪያው አንቀጽ አራት ላይ አግባብ ባለው አካል ወይም ጥፋተኛ በተባለው ግለሰብ አሳሳቢነት ተብሎ መስፈሩን  ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡ ይህን ተከትሎም መስፈርቶቹን ያሟላ ታራሚ በማመልከቻው “ለአመክሮ የሚያሰጡትን ቅድመ ሁኔታዎች አሟልቻለሁ በአመክሮ ልፈታ?“ ብሎ ጥያቄ  ሲያቀርብ ወይም ማረሚያ ቤቱ “ይህ ታራሚ ከእስር ከመፈታት አኳያ  የተቀመጡትን መስፈርቶች ያሟላል፡፡ አጣሪው ቡድኑ በአመክሮ ሊለቀቅ ይገባዋል“ በማለት ማህደሩን አይቶ አመክሮ ለሚሰጠው አካል ጥያቄ ሲያቀርብ፣ የታራሚው ቤተሰብ ሲጠይቁ እንደሆነ መመሪያውን ጠቅሰው ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አመክሮ ጠይቆ የተከለከለ ታራሚ ምላሹ ወዲያውኑ ውድቅ የሆነበት ምክንያት በጽሑፍ ይሰጠዋል፡፡ አመክሮ ጠያቄው በውሳኔው ቅር ከተሰኘ ቅሬታውን በበቂ ምክንያት አስደግፎ ለማረሚያ ቤት ኃላፊው ያቀርባል፡፡ ኃላፊውም ቅሬታውን መርምሮ በሁለት ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ምላሹ ግን “ውሳኔው ውድቅ መሆኑ ተገቢነት አለው“ የሚል ከሆነ ታራሚው ፍርዱን ለሰጠው አካል ይግባኝ ማቅረብ እንደሚችል መመሪያው ላይ ሰፍሯል፡፡

ታራሚዎች በአመክሮ የሚለቀቁበት   የሕዝብን እና የመንግሥትን ጥቅም ለማስከበር/ለማስጠበቅ/፣ በፈፀሙት ድርጊት ተቆጭተው እና ተፀፅተው ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ሕግ አክባሪ እና አስከባሪ በመሆን ሠላማዊ ሕይወት እንዲመሩ ታሳቢ ተደርጎ እንደሆነ ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ታራሚዎች በአመክሮ መለቀቃቸው በቆይታቸው መንግሥት ለምግብ፣ ለመጠለያ እና ለሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ያወጣው የነበረውን ገንዘብ መቆጠብ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ታራሚውም ከማረሚያ ቤት እንደወጣ ከማህበረሰቡ ጋር በመቀላቀል አምራች በመሆን ራሱን፣ ሀገሩን እና መንግሥትን ይጠቅማል፡፡

እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ ለታራሚዎች በአመክሮ የማይፈቀዱ የወንጀል ድርጊቶችም አሉ፡፡ እነዚህም ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ  ሰውን መግደል፣ የሰው ዘር ማጥፋት፣ ሰውን መሰወር እና ማጥፋት ፣ሙስና እና አስገድዶ መድፈር  ናቸው፡፡

በወንጀል ሕጉ አመክሮን የመስጠት መብት ያለው ፍርድ ቤት እንደሆነ ተቀምጧል፤ ነገር ግን አሁን በአፈጻጸም ደረጃ አመክሮን የሚሰጠው ፍርድ ቤት ሳይሆን በመግባቢያ ስምምነት መሰረት ማረሚያ ቤቶች እንዲሰጡ መደረጉን ኃላፊዋ  ተናግረዋል፡፡

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here