ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት ነው ጉዳዩ የተከሰተው:: አንዲት ዕድሜያቸው በሃምሳዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኙ እናት ነበሩ:: በሕይዎት ዘመናቸው ከባድ ሕመም ታመው ወደ ሕክምና ተቋም ደርሰው አያውቁም ነበር:: ነገር ግን አልፎ አልፎ በሚያጋጥማቸው የሆድ ሕመም ወደ ክሊኒክ ጎራ ይሉ ነበር:: ታዲያ በወቅቱ ሀኪም አገኘሁት እሚላቸው በሽታ አሜባ እና ጃርዲያ ነበር:: ከዚህ የከፋ ሕመም አጋጥሟቸው አያውቅም::
ሆኖም በሕይዎት ከማለፋቸው አንድ ዓመት አካባቢ ሲቀራቸው በተደጋጋሚ የሆድ ሕመም እና ቶሎ ቶሎ የሚመጣ ደም የቀላቀለ ተቅማጥ ተከሰተባቸው:: ሕመሙ ፋታ የሚሰጥ አልነበረም:: እንደበፊቱ በአሜባ መድሃኒት የሚታገስም አልሆነ። በመሆኑም ሐኪሙ የኮሎኖስኮፒ ምርመራ አዘዘላቸው:: ኮሎኖስኮፒ ጫፉ ላይ ካሜራ ያለው ቀጭን ረዥም እና ተጣጣፊ ቱቦ ሲሆን በፊንጢጣ በኩል በመግባት አንጀትን የሚያሳይ መሳሪያ ነው:: በኮሎኖስኮፒው አማካኝነት ከአንጀት ዕባጩ ላይ ትንሽ ፈሳሽ በመውሰድ ምርመራ ከተደረገላቸው ከ15 ቀን በኋላም ውጤቱ ደረጃ አራት የደረሰ የትልቁ አንጀት ካንሠር ነበር የተባሉት:: በሽታው ከታወቀ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜም ሕይዎታቸውን ሊያጡ እንደቻሉ ዛሬ ልጃቸው በፀፀት የነበረውን ሁኔታ በዐይነ ህሊናዋ እያስታወሰች ነግራናለች::
ልጃቸው እንደምትለው ምናልባት የኮሎኖስኮፒ ምርመራው አስቀድሞ ቢታዘዝላቸው ኖሮ ካንሠሩ ቀድሞ ይታወቅና ሕክምና ተደርጎላቸው መዳን ይችሉ ነበር::
ይህ ታሪክ የብዙ ሰዎች ነው:: የሆድ ሕመምን ቀለል አድርጎ ማሰብ፣ የሕክምና ባለሙያውም ምልክቶችን አይቶ የኮሎኖስኮፒ ምርመራ በፍጥነት አለማድረጉ ካንሠሩ ወዲያው ላለመታከሙ ምክንያቶች ናቸው::
ስንቶቻችን ነን ስለ አንጀት ካንሠር ግንዛቤው ያለን? መልካም ግንዛቤው ካለዎት ለሌለው እንዲያደርሱ አደራ እያልን፤ ግንዛቤው ከሌለዎት ደግሞ ስለ አንጀት ካንሠር ሙያዊ ማብራሪያ ለማግኘት በእያስታ ሕክምና ማዕከል የውስጥ ደዌ፣ የጨጓራ፣ አንጀት እና የጉበት ሰብ ስፔሻሊስት ዶ/ር ክብረቴ ወልዴ ጋር ያደረግነውን ቆይታ በጽሞና ታነቡ ዘንድ ጋብዘንዎታል!
ካንሠር ማለት ምን ማለት ነው? የአንጀት ካንሠርስ? ለሚለው ጥያቄያችንም ይህንን መልስ ሰጥተውናል:: ካንሠር ሰውነታችን ማይቆጣጠረው ጤነኛ ያልሆኑ የሴሎች እድገት ማለት ነው:: ካንሠር በሁሉም የሰውነት ክፍሎች ላይ ሊከሰት ይችላል:: ካንሠር በጥቅሉ እንደ ሀገር እያደገ የመጣ ችግር ነው:: በፊት በበለጸጉ ሀገራት ላይ ነበር የሚከሰተው። አሁን ግን በታዳጊ ሀገራትም በብዛት መከሰት ጀምሯል ነው ያሉን::
የአንጀት ካንሠር ደግሞ በብዛት የትልቁ አንጀት ካንሠር ማለት እንደሆነ ነው፤ ባለሙያው ያብራሩት:: ምክንያቱም የአንጀት ካንሠር የሚነሳው ከትልቁ አንጀት እና ከፊንጢጣ አካባቢ ላይ ካለ ዕጢ ነው:: የአንጀት ካንሠር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሦስተኛ ላይ ይገኛል:: በገዳይነቱ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በሽታ እንደሆነ ነው የጠቆሙት::
ለአንጀት ካንሠር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች የመጀመሪያዉ ዕድሜ እንደሆነ የሚያብራሩት ዶ/ር ክብረቴ ፤ እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ለካንሠሩ ተጋላጭ ናቸው:: ሌላው በቤተሰብ (አባት፣ እናት፣ እህት ወንድም) የአንጀት ካንሠር ያለበት ሰው የመያዝ አጋጣሚው ይጨምራል:: ክብደት መጨመር፣ አልኮል መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ አለማዘውተር፣ ስጋን አብዝቶ መመገብ ለበሽታው እንደሚያጋልጡ ነው የተናገሩት::
የአንጀት ካንሠር መጀመሪያ ላይ ትንሽ ዕጢ ነው ሚሆነው:: ዕጢው እያደገ ሲመጣ ነው ወደ ካንሠር የሚቀየረው:: ዕጢዋ በእንግሊዘኛ ፖሊፕ ትባላለች፤ ወደ ካንሠር ለመቀየር እድገቱ እስከ 10 ዓመት ሊቆይ ይችላል:: በየጊዜው ምርመራ የምናደርግ ከሆነ ግን እብጠቱ ወደ ካንሠር ከመቀየሩ በፊት ችግሩ ሊለይ እና ሊታከም እንደሚችል ነው የተናገሩት::
ዶ/ር ክብረቴ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ካንሠር ይከሰትበታል ተብሎ ከሚጠበቀው ዕድሜ በታች እየተከሰተ ይገኛል::
እሳቸው እንደሚሉት ካንሠር የሚከሰተው ከቤተሰብ ጋር ተያይዞ የካንሠር ታሪክ ያለው ቤተሰብ ካልሆነ በቀር ብዙውን ጊዜ ዕድሜያቸው ሃምሳ ዓመት እና በላይ በሆኑ ሰዎች ነበር:: ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ቀድሞ መታየት ጀምሯል::
አብዛኛው ሰው ሆዱን ሲታመም ‘አሜባ ነው፣ የምግብ መበከል ነው …’ በሚል አመጋገቡን ለማስተካከል ይሞክራል እንጂ ወደ ሕክምና ተቋም እንደማይመጣ ነው ባለሙያው የተናገሩት:: “በየቀኑ የምናየው ነገር በመሆኑም ብዙ ታካሚ የሚመጣው ዘግይቶ ነው:: ካንሠሩ ከተሰራጨ በኋላ ነው ወደ እኛ ለሕክምና የሚመጡት ”ይላሉ::
የአንጀት ካንሠር ከአንድ እስከ አራት የሕመሙ ደረጃዎች እንዳሉት የተናገሩት ዶክተር ክብረቴ በደረጃ አንድ የካንሠር ሕመም ላይ የሚገኝ ታማሚ ካንሠሩ በመጠን ትንሽ እና ወደ ሌሎች የአካል ክፍል ያልተሰራጩበት ነው:: ደረጃ ሁለት ካንሠር ደግሞ በመጠን ትልቅ ሲሆን እሱም ልክ እንደ ደረጃ አንድ ሁሉ ካንሠሩ ወደ ሌሎች የአካል ከፍሎች ያልተሰራጨ ነው::
ደረጃ ሦስት ካንሰር የሚባለው ደግሞ ካንሠሩ በአካባቢው ወዳሉ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች (ሊምፍ ኖድስ) ተሠራጭቶ ይገኛል:: ደረጃ አራት ካንሰር የሚባለው የመጨረሻው ደረጃ ሲሆን ካንሠሩ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች በመሰራጨት ሁለተኛ ዕጢ ይፈጥራል። አንድ ሰው ደረጃ አራት የደረሰ የአንጀት ካንሠር ካለው የመዳን ዕድሉ የመነመነ እንደሆነ ነው የተናገሩት::
ዶ/ር ክብረቴ እንደሚሉት ከፍተኛ ድካም፣ ከዐይነምድር ላይ ደማቅ ቀይ ወይም ጠቆር ያለ ቀይ ደም፣ በተደጋጋሚ መፀዳጃ ቤት መጠቀም፣ ተቅማጥ ወይም ድርቀት ሲከሰት፣ መፀዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ በደንብ ያልተጻዳዱ የሚመስል ስሜት መሰማት፣ ንፍጥ የቀላቀለ ዐይነ ምድር፣ ትንሽ ከተመገቡ በኋላ ሆድ የሞላ መምሰል፣ በታችኛው የሆድ ክፍል ላይ ሕመም ወይም እብጠት ሲኖር፣ የደም ማነስ፣ ስፖርት ሳይሰሩ ወይም ለክበደት መቀነስ የሚረዳ ነገር ሳያደርጉ የክብደት መቀነስ፣ እነዚህ ምልክቶች ለሦስት ሳምንታትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ ካጋጠመዎት በፍጥነት በሐኪም መታየት ይኖርበዎታል:: ምክንያቱም እነዚህ ምልክቶች የአንጀት ካንሠር ሊሆኑ ይችላሉና::
የአንጀት ካንሠር ምልክቶች ከታዩ ፈጠን ብሎ ሐኪም ማማከር በሽታውን ለመቆጣጠር ወሳኝ ነው። ምርመራውም ቱቦ በመጠቀም ሁሉንም የአንጀት ክፍሎች በካሜራ በሚያሳይ መሣሪያ (ኮሎኖስኮፒ) በማድረግ ካንሠሩ መኖርና አለመኖሩን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።
በመጀመሪያው የአንጀት ካንሰር ደረጃ ላይ ምርመራ ያደረጉ ሰዎች በሽታውን በቶሎ በመለየት አስፈላጊው ሕክምናን በወቅቱ ማግኘት ስለሚችሉ የሚከሰተውን ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ይቻላል። የካንሠር በሽታ በብዛት የሚከሰተውና ገዳይ የሚሆነው ዕድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ በመሆኑ ልክ እንደ ሌሎች የካንሠር በሽታዎች ሁሉ በአንጀት ካንሰር የተያዙ ከ15 እስከ 40 ባለው የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች በሕይወት የመቆየታቸው ዕድል ሰፊ ነው።
ጤናማ የሕይወት ዘይቤን በመከተል፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ፣ በብዛት አሰር ያላቸውን ምግቦች በመመገብ እና ስብን በመቀነስ እንዲሁም በቀን ውስጥ ከስድስት እስከ ስምንት ብርጭቆ ውሃ በመጠጣት የአንጀት ካንሠርን ቀድሞ መከላከል እንደሚቻል ተናግረዋል:: እንዲሁም በየትኛውም የዕድሜ ክልል በበሽታው ለተያዘ ሰው ሕክምናው እንደሚሰጥ ሕክምናውም ቀዶ ሕክምና፣ ኬሞቴራፒ፣ ራዲዮቴራፒ (ጨረራ) ወይም ደግሞ እንደየግለሰቡ የካንሠር ሁኔታ ሌሎች ሕክምናዎች ሊሰጡ እንደሚችሉ ነው ያብራሩት:: የአንጀት ካንሠር ቀድሞ ተለይቶ ከታከመ ተመልሶ እንደማይከሰት ነው የተናገሩት::
በመጨረሻም ዶ/ር ክብረቴ እንደሚሉት ሕብረተሰቡ እላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ሲያጋጥሙት በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ይኖርበታል:: በባሕላዊ መንገድ አለመታከም፣ የኮሎኖስኮፒ ምርመራን አለመፍራት ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም