በአፍሪካ ግዙፉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 04 ቀን 2017 ዓ.ም የፍጻሜው ብሥራት ተነግሮ ተመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል። የኬንያ፣ የጅቡቲ፣ የሶማሊያ፣ የደቡብ ሱዳን እና የቤርባዶስ መሪዎችን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአፍሪካ ኩራት፣ ለቀጣናው ታሪካዊ ቀን፣ ለአህጉሪቱ ራስን የመቻል ማሳያ ስለመሆኑ ነው የተናገሩት።
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካ የራሷን መዳረሻ የመወሰን አቅም እንዳላት ያሳየ ነው” ብለዋል። የምረቃ ሥርዓቱን በፕሬዚዳንቱ እና በሀገሪቱ ስቴት ሀውስ ትስስር ገጾች በቀጥታ ተሰራጭቷል።
በአፍሪካ በአሁኑ ወቅት ከ600 ሚሊየን በላይ ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንደማያገኙ ያነሱት ፕሬዚዳንት ሩቶ ይህም በአህጉሪቱ ልማት ላይ እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዋል።
“ግድቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፕሮጀከት ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካ መገለጫ ነው”ም ብለዋል። እ.አ.አ በ2022 ኬንያ ከኢትዮጵያ ለ25 ዓመታት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት መፈራረሟን አስታውሰው 200 ሜጋ ዋት እየገዛች ስለመሆኑ ነው የጠቆሙት።
ከታለቁ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ለማግኘት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር መነጋገራቸውንና ሌሎች ውይይቶች እንደሚኖሩም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ሩቶ በመጨረሻም “የሕዳሴው ግድብ መቶ በመቶ በኢትዮጵያውያን መሠራቱ ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት በራስ አቅም መሥራት እንደምንችል ያሳየ ነው” ብለዋል፤ አካባቢውን ለመለወጥም አብሮ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሙሐመድ በበኩላቸው “ቀኑ ለመላው የቀጣናው ሕዝብ ታሪካዊ ነው” በማለት ነው የግድቡን መመረቅ የገለጹት። ፕሬዚዳንቱ አክለውም በቀጣናው ያለው ውኃ እና ሃብት በድንበር የተገደበ ሳይሆን የጋራ መፃኢያችንን የሚወስን እንደሆነ ተናግረዋል።
በቀጣናው ልማትን ለማምጣት ከፉክክር በመውጣት በትብብር መሆን እንዳለበት ነው የተናገሩት።
“ዛሬ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለቀጣናችን የኩራት ቀን ነው” ያሉት ደግሞ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪየር ናቸው። ሀገራቸው ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ለማግኘት የሚያስችል ስምምነት መፈራረም እንደምትፈልግም አስታውዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ግድቡ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የመስዋዕትነት፣ የአንድነትና የቆራጥነት ምልክት ነው፤ ግድቡ ሕዝብ በአንድ ራዕይ ላይ በአንድነት ከቆመ ሃገር ምን መሥራት እንደምትችል ያሳዬ ነው” ብለዋል።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም